Monday 15 May 2017

ዘፈን - የወደቀው መልአክ እንጉርጉሮ (ክፍል 2)

Please read in PDF
በመጽሐፍ ቅዱስ “ዘፈን” የተገለጠበት አገላለጥ
   በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ በተለይም በአማርኛው በተመሳሳይ ቃል ወይም ሐረግ ተጠቅሶ የተለያየ ፍቺ ያለው ቃል ብዙ ቦታ ይገኛል፡፡[1] ስለዚህ ቅዱሳት መጻሕፍትን ስናጠና የቃሉን መመሳሰል ሳይሆን ቃሉ ያለበትን ወይም የተነገረበትን ዓውድ በትክክል ማጥናትና መስተዋል ይገባናል፡፡ “ዘፈን”ም ለተለያየ ሃሳብ፤ በተለያየ ዓውድ ተነግሯል፡፡ እናም እንደየተነገረበት ዓውዱ የተለያየ ትርጉሞችና ሰፊ ሃሳቦችን ይዟል ማለት ነው፡፡ ጥቂቱን ብንመለከት እንኳ፦
1.    “ዘፈን” በቅዱስ አምልኮ ውስጥ ሲጠቀስ፤
    በብሉይ ኪዳን የእስራኤል ልጆች በዘፈን ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ አምልኮን ያቀርቡ ነበር፡፡ የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር፤ ከባርነት ቤት ሲወጡ፣ ፈርዖንንና ሠረገላውን ሁሉ በባሕር አስጥሞ፣ ለእነርሱ ግን ሞገስንና ግርማን ሰጥቶ፣ የኤርትራን ባሕር በድል ሲሻገሩ በዝማሬ አመሰገኑ፤ (ዘጸ.15፥1)፡፡ በሌላ ሥፍራ፣ “ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር፤ … የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፤ በልብዋም ናቀችው፡፡ … በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ፤” (2ሳሙ.6፥14-16 ፤ 21) በማለት ራሱም ገልጦታል፡፡

    የዳዊት ተግባራት መዝፈን[2]ና መዝለል(በዕብራይስጥ ፋዛዝ)፣ መጫወት(በዕብራይስጥ ሳ[ጻ]ኸቅ) ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ የለበሰውም የኤፉድ በፍታው ሙሉ ለሙሉ ከሰውነቱ ላይ እስኪወድቅ ድረስ በምስክሩ ታቦት ፊት በአምልኮ መንፈስ ምስጋና ማቅረቡን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ ዘፈን  ከመንፈሳዊነት ጋር የተያያዘ ድርጊትን የሚያመለክት ነው፡፡ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት “መዝፈኑ”[መዝለልና ማሸብሸቡ] ከመንፈሳዊ ምስጋና በተቃርኖ ለሆነ ሃሳብ ፈጽሞ መቅረብ አይችልም፡፡
    በእስራኤል ልጆች ታሪክ ዜማና ቅዱስ “ዘፈን” የተለመደና ተወዳጅ ነበር፡፡ “ዩባል በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት የነበረ፣ ከዚያም በኋላ በገና ደርዳሪው ንጉሥ ዳዊት ዜመኞች እንዲሾሙ ሌዋውያንን አዝዞ ነበር፡፡
   “ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ … በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር፡፡ … በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር፡፡ … ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር … ” (1ዜና.15፥16-21)
      አሁንም በሌላ ሥፍራ፣ እነሆ፥ የያዕቆብን ድንኳን ምርኮ እመልሳለሁ፥ ለማደሪያውም እራራለሁ፤ ከተማይቱም በጉብታዋ ላይ ትሠራለች፥ አዳራሹም እንደ ዱሮው የሰው መኖሪያ ይሆናል፡፡ ከእርሱም ዘንድ የምስጋናና የዘፋኞች ድምፅ ይወጣል፤ እኔም አበዛቸዋለሁ አያንሱምም፥ እኔም አከብራቸዋለሁ ታናሽም አይሆኑም፡፡” … “ … እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፦ በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ፡፡ የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ …” (ኤር.30፥19-20) በማለት፣ በባርነት ሕይወት ውስጥ ለነበሩትና፣ በባቢሎን ምድር ሳሉ በኃጢአታቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቅዱሱን ኪዳን በመተላለፋቸውና በማፍረሳቸው በፍጹም መከራ ውስጥ ለወደቁት የእስራኤል ልጆች፣ ጌታ እግዚአብሔር አሁን ካሉበት ጥፋትና ባርነት ነጻ ወጥተው በደስታ የሚኖሩትን ዘመን በማስታወስ የተናገራቸው ትንቢት ነው፡፡  
     ቃሉ ይሁዳ ሁሉ ከምርኮ ነጻ ወጥተው ወደምድራቸው በተመለሱ ጊዜ የሚያደርጉትን ታላቅ ሐሴትና ደስታን የሚያመለክት ነው፡፡ ደስታውም ሳቅ የመላበትና ከደስተኞች የሚወጣ ፍጹም ደስታና ዜማን አመልካች ነው፡፡   
   ከባቢሎን ምርኮ በኋላም በቤተ መቅደሱ “ሁለት መቶም ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ”፤ (ዕዝ.2፥65)፡፡ ስለዚህ ለየትኛውም አይሁድ ዘፈን፣ ዜማ፣ ዝማሬ ከብዙ ነገሩ ጋር የተቆራኘ ነገር እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡ በተለይም በመንፈሳዊው ረገድ፡፡ ዳዊትም ይህን እውነት በማጽናት፣ ስሙን በዘፈን ያመስግኑ፥ በከበሮና በመሰንቆም ይዘምሩለት”፤ “በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት” (መዝ.149፥3 ፤ 150፥4) ብሏል፡፡ በዚህም በዘፈን [በምስጋናና በዝማሬ] ለእግዚአብሔር ማቅረብ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

2.   ዘፈን በጣዖት አምልኮ ውስጥ፤
    የእስራኤል ልጆች በምርኮ ምድር በነበሩባቸው ወራት፣ ከማረኳቸው አሕዛብ ብዙ እንግዳና ለእግዚአብሔር ቅዱስ አምልኮ የማይመች ነገሮችን ወርሰዋል፡፡ ከእኒህም መካከል ጣዖት አምልኮና ከእርሱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን በቀጥታ ከአሕዛብ ወርሰዋል፡፡
    የእስራኤል ልጆች የጥጃውን ምስያ ጣዖት በማምለካቸው ፍጹም እግዚአብሔርን በደሉ፡፡[3] ሁኔታውን ቅዱስ ሙሴ ሲጽፈው፣ “ … በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ፤” (ዘጸ.32፥6) በማለት ገልጦታል፡፡ በዚህ ንባብ ውስጥ ፈንጠዝያ፣ ስላቅ፣ ፌሽታ፣ ጩኸት፣ ጨዋታ፣ ጭፈራ የበዛበትን ድርጊት የሚያመለክት ርኩስ ተግባርን ነው፡፡ ቃሉ በዕብራይስጥ “ማኾል” ተብሎ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በጣዖት ፊት የሚደረግን ዘፈናዊ አካላዊ እንቅስቃሴን ሁሉ የሚያመለክት ነው፡፡ ሶምሶን እንዲህ ያለ ተግባር እንዲፈጽም ተጠይቆም ነበር፤ (መሳ.16፥25)፡፡

    በመሳፍንት ዘመንም፣ “የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው፦ ሂዱ በወይኑ ስፍራ ተደበቁ፤ ተመልከቱም፥ እነሆም፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፥ ከሴሎም ሴቶች ልጆች ለየራሳችሁ ሚስት ንጠቁ፥ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ፡፡ … የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፥ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስት ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፥ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው፤” (መሳ.21፥21 ፤ 23)፡፡

  ቃሉ በቀጥታ የተጻፈው ከእግዚአብሔር ሕግ በተቃራኒው መንገድ ይሄዱ በነበሩት አካላት ለመሆናቸው፣ የሰዎችን “ሚስት በመንጠቅ” መሰማራታቸው ያጎላዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመሳፍንትን ዘመንና የዚህን ምዕራፍ መጨረሻ ቃል ስናስተውል፣ “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር”(ቁ.25) በሚል መደምደሚያ ቃል ታስሯል፡፡ ስለዚህ ቃሉ በተነገረበት ዓውድ ውስጥ ሆነን ስንተረጉመው፣ ዘፈን[4] ተብሎ የተጠቀሰው ሴቶቹ ያመልኩት ከነበረው ጣዖት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ማስተዋል ይቻላል፡፡

     ጣዖትን ማምለክ በቀጥታ ዝሙትን ከመፈጸም ጋር ይያያዛል፤ (1ነገ.15፥12 ፤ ሮሜ.1፥23-25)፡፡ ስለዚህም ጣዖት ማምለክም፤ ማመንዘርም ያስነውራል፤ (ኢሳ.44፥18)፤ ከአጋንንትም ጋር አንድ ያደርጋል፤ (1ቆሮ.10፥20)፡፡ ይህንን ሃሳብ ከዘፈን ጋር እናያይዘው ብንል ደግሞ፣ የአጋንንትን ዘፋኝነት በግልጥ ማንሳት እንችላለን፤ (ኢሳ.13፥2)[5]፡፡
   በሌላ እይታ፣ ዘፈን ከጣዖት አምልኮ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው፡፡ ሁሉም ጣዖታት በራሳቸው የሚቀርብላቸው የዜማ “መሥዋዕት” አላቸው፡፡ በአብዛኛውም ቅጥ ካጣ ደስታ፣ ፌሽታና ጩኸት፣ ግርግርና ጭፈራ የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡ በአገራችን ያለውን የጠንቋይ ቤት ትእይቶችን ማየት ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡

3.   በዘፈን ሌላውን መተረብ ወይም በሌላው ላይ ማፌዝ፤

     እስራኤላውያን በባህላቸው ዘፈንን በሌላው ላይ ለማፌዝና ሌላውን ለመተረብ፣ እንዲሁም ከዕለት ተእለት ኑሯቸውም ጋር በማያያዝ አንዳንዱን ሊያኮስሱበት ሌላውን ደግሞ ሊያሞግሱ[ለዳዊትና ለሳዖል የተዘፈነውን እናስታውስ፤ 1ሳሙ.18፥6] ይጠቀሙበት ነበር፡፡ ለዚህም ኢዮብና ዳዊት በእነርሱ ላይ የደረሰውን ነገር፣ “አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው፤” … “በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ” (ኢዮ.30፥9 ፤ መዝ.69፥12)፡፡
   ትዕግስተኛው ኢዮብ በአከባቢው ሰዎችና ዘፋኞች፤ በተራቾችም ጭምር መናቁን፤ እንደተፌዘበትም ጭምር በግልጥ ይናገራል፡፡ ዘፈኑ የሰውን ስሜትና ክብር ዝቅ ለማድረግና ለማዋረድ የሚደረግ ዜማዊና ንግርታዊ አድራጎትን ማካተቱን ከዓውዱ ማስተዋል ይቻላል፡፡ በዕብራይስጥ ቃሉ “ንጊናህ” የሚል ሲሆን፣ በዘፈንና በተረት ለመንደሩ ሰውና ለሰካራሞች መዘበቻና መቀለጃ፣ መተረቻም መሆንን የሚያሳይ ቃል ነው፡፡
    በአገራችንም ቢሆን በዘፈን የጠሉትን ማናናቅና ማጣጣል፣ መተረብ፤ የወደዱትን ደግሞ ማሞካሸትና ማወደስ፣ ለጠብና ለጦርነት በሽለላና በተለያየ መንገድ መቀስቀስ  እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በየመሸታው ቤት ያሉትን ባለጠጋና ሴሰኛ አወዳሽ አዝማሪዎችና ንጉሥና  መስፍን፤ መኮንን አሟካሽ ዘፈኖች ለእኛ ሩቅና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡
4.   ዘፋኝነትና ስካር የተቆራኙ ስለመሆኑ፤

    “ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ፤” (መዝ.69፥12) የሚለው ቃል፣ በቀጥታ ዘፈን አንዱ የስካር ውጤት መሆኑን ይነግረናል፡፡ ጠቢቡ፣ “ዋይታ ለማን ነው? ኀዘን ለማን ነው? ጠብ ለማን ነው? ጩኸት ለማን ነው? ያለ ምክንያት መቍሰል ለማን ነው?” (ምሳ.23፥29) በማለት ዋይታና ጩኸትን ከስካር ጋር ማያያዙ ይኸንኑ ለማጽናት ይሆንን?!
    ነቢዩ ኢሳይያስም፣ “ስካርን ለመከተል በጥዋት ለሚማልዱ፥ የወይን ጠጅም እስኪያቃጥላቸው እስከ ሌሊት ድረስ ለሚዘገዩ ወዮላቸው! መሰንቆና በገና ከበሮና እምቢልታም የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የእግዚአብሔርን ሥራ ግን አልተመለከቱም፥ እጁም ያደረገችውን አላስተዋሉም”፣ “እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤” (ኢሳ.5፥11-12 ፤ 28፥7)፡፡

    ጠጥቶ በመስከርና ቅጥ የለሽ ፈንጠዝያ፣ ቅምጥልነት የበዛበት ሕይወት ራስን አለልክ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ለእግዚአብሔር ላልሆነ ዘፈንም ይዳርጋል፤ (አሞ.6፥6)[6]፡፡ ኢ ሥነ ምግባራዊም ነውና በእግዚአብሔር ዘንድ አጸያፊ ነው፤ “ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፤ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ” (መክ.2፥8) በማለት፣ ጠቢቡ ሰሎሞን ደስታን ኢ ሥነ ምግባራዊ በሆነ መንገድ መፈለጉንና ማከማቸቱን፤ ነገር ግን ፈጽሞ አለማግኘቱን በግልጥ ይመሰክራል፡፡ ሥጋዊ ተድላና ፌሽታ መንፈሳዊ ደስታን ማግኘት እንደሚቻል በትክክል ያሳያል፡፡

   የአዲስ ኪዳን ንባባት ሁሉ ዘፋኝነትን በቀጥታ ከዘፋኝነት ጋር አያይዘውታል፤ “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥”…” (ሮሜ.13፥13)፤ “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው … ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው” (ገላ.5፥21)፤ “የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት …” (1ጴጥ.4፥3) በማለት፣ ዘፋኝነት የስካር ውጤት አንዱ መገለጫ መሆኑን አያይዘው አስቀምጠውታል፡፡ በእርግጥም ዘፈን ከስካር መያያዙ እጅግ አደገኛነቱን ያጎላልናል፡፡ ምክንያቱም መዘዙ እጅግ የከፋ ነውና፡፡

    ስለዚህ ዘፈን ከተለያየ ዓውድ አንጻር የተለያዩ ትርጓሜዎች እንዳሉት ከዚህ ጥቂት ማሳያ መመልከት ይቻላል፡፡ በዋናነት ግን መዘንጋት የሌለብን ነገር ለእግዚአብሔር ክብርና ቅድስና ከተጠቀሰው በቀር፣ በአዲስ ኪዳን እኛን በቀጥታ የሚመለከተን ነገር እንደሌለ ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ምንባባትም የእስራኤልን ባህልና ወግ እንድንከተል ያስተማሩን ነገር የላቸውም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለአምላካቸው “መዝፈናቸው” እኛ ለጾታዊ ፍቅርና ለቅጥ የለሽ ፈንጠዝያና ጭፈራ፣ ዳንስ፣ ጩኸት እንድንዘፍን የሚጋብዘን ምንም ዓይነት ፍንጭ አልተተወልንም፤ ምንም ማስረጃ የለንምም፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ያብዛልን፡፡ አሜን፡፡

ይቀጥላል…





    [1] ለምሳሌ፦ “ፍቅር” የሚለው የአማርኛው ቃል፣ አንድ ቃል ቢሆንም፣ በእናት ቋንቋው ኮይኔ ግሪክ ግን እንደዓውዱ የተለያዩ ስያሜያትና ፍቺዎች አሉት፡፡ “አጋፔ” የሚለው ቃል ቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን አምላካዊ ፍቅርን ሲያመለክት፣ “ፊልዮ” የሚለው ደግሞ የወንድማማችነትን ፍቅር፣ “ኤሮስ” ደግሞ የባልና ሚስትን እና “ኤሮቲክ” የሚለው ደግሞ ከዝሙት፣ ከመዳራት፣ ከርኩሰትና ከሴሰኝነት ሁሉ ጋር የሚያያዝ እድፈት ያለበትን የዝሙትን ሃሳብ ሁሉ ያመለክታል፡፡ ቃል፣ ነፋስ፣ ነፍስ፣ መንፈስ፣ ዓለም ... የሚሉትንም ቃላት እንደዓውዳቸው የተለያዩ ፍቺዎች ሊኖራቸው ይችላል፡፡
[2] በሌላ ትርጉም ካራር ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ትርጉሙም በጨዋታ ውስጥ በፍጥነት መሽከርከር ያለበትን የሰውነት እንቅስቃሴን የሚያመለክት ነው፡፡
   [3] በእስራኤል ልጆች ታሪክ ይህ ክፍል አሳፋሪው ክፍል  ነው፡፡ ምክንያቱም በብዙ ተአምርና ድንቅ ያወጣቸው እግዚአብሔርን ፍጹም ረስተው፣ በዚያው ቅጽበት የጥጃ ምስያን አምልከዋል፡፡ ያመልኩም የነበረው ራሳቸውን ስድ በመልቀቅ(ዘጸ.32፥25-26) ማለትም ሙሉ ለሙሉ መረን በመልቀቅና ጣዖትን በማምለካቸው በእግዚአብሔር ላይ በማመንዘር ነበር፡፡
   [4] በሕብረት በመሰባሰብ ክብ ሰርቶ መወዛወዝና መጨፈርን የሚያመለክት ሃሳበ በውስጡ የያዘ ነው፡፡
    [5] ኢሳይያስ የባቢሎንን በእግዚአብሔር ፍርድ መጥፋትና መውደም፤ ወደፍጹም ወናነትም ተቀይራ የአራዊትና የእንግዳ ፍጡራን መሆኗን በግልጥ የተናገረበት ክፍል ነው፡፡ ባድማ፣ ውድማ፣ ወና በመሆኗ ምክንያትም የአራዊት መዝፈኛ መሆኗንና አጋንንትም በዚያ የሚዘፍኑባት መሆኑን ያመለክታል፡፡ በዚህ ሥፍራ ዘፈን ተብሎ የተጠቀሰው በዕብራይስጡ “ራቃድ” ተብሏል፡፤ ይኸውም እጅግ የበዛና ጩኸቱ የተደባለቀ ድምጽን ያመለክታል፡፡ አንዳንዶች የዚህ ክፍል ሲያብራሩ ዘፈኑ የሰውን ዘፈን እንደማይመስል ተናግረዋል፤ ዳሩ አጋንንት ቅጥ ያጣ ፈንጠዝያንና ሁከትን በመፍጠር ማሳት እንደሚቻላቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡
    [6] በዚህ ሥፍራ የተጠቀሰው የዕብራይስጡ ቃል “ሚርዛኽ” ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ዓውዳዊው ፍቺም መጠጥና ምግብ የተቀላቀለበት ግብዣና ዘፈንን የሚያካትት ነው፡፡ ይህ አባባል ግን ለዘፈን ፈቃድን የሚሰጥ አይደለም፡፡ ተዘልላ ለተቀመጠችው እስራኤል የተሰጠ ብርቱ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡ ምክንያቱም በከንቱነት ተቀማጥላ ራሷን እያሞጋገሰች በትእቢት ጸንታ ነበርና፡፡

1 comment:

  1. hulum slezefen ante yemitasbewn biyasb melkam neber ... gn Kristos kalabera sew mayet aychilm

    ReplyDelete