Sunday, 14 February 2016

ቲያንስ - የማይዋደዱትንና ባላንጣዎቹን “አገልጋዮች” እንዴት አፋቀረ?

  
Please read in PDF
 መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሥጋ ከተገለጠበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ዘመን የመጨረሻው ዘመን በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ የጌታን መምጣት ቶሎ እንደሚሆንና የቀረበ መሆኑን ደጋግሞ የሚናገረው፡፡ (ሐዋ.2፥17 ፤ 1ጢሞ.4፥1 ፤ ዕብ.1፥1 ፤ 1ዮሐ.2፥18 ፤ ራእ.1፥1 ፤ 3 ፤ 22፥6-7 ፤ 10 ፤ 20)በዚህ የመሲሑ ዘመን በሆነው በዘመን መጨረሻ ከሚሆኑት ነገሮች አንዱ ገንዘብ የሚያመልኩና የሚያፈቅሩ ሰዎች የሚበዙ መሆናቸውን ታላቁ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡
    የእግዚአብሔር መንፈስ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለዚህ ነው ከዘመናት በፊት ሐዋርያትን አንቅቶ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጽፋቸው የአገልጋይን ዋና መመዘኛ፥ “ራሱን የሚገዛ (1ጢሞ.3፥2 ፤ ቲቶ.1፥8 ፤ 2፥2 … ገንዘብን የማይወድ ፣ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የማይሮጥ(ረብ የማይወድ) [1] (1ጢሞ.3፥3 ፤ 8 ፤ ቲቶ.1፥7) በማለት የጠቀሰው፡፡ ጌታችንም ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ባሠማራበት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውም ነገር ሁሉ፥ የሚመሰክሩላቸው ሰዎች በሚያደርጉላቸው ልከኛ እርዳታ ላይ ፍጹም መደገፍ እንዳለባቸው እንጂ የራሳቸውን ነገር መያዝ እንደሌለባቸው አስጠንቅቋቸዋል፡፡ (ማቴ.10፥8-11)


    እንዲያውም እጅግ ብርቱ በሆነ ቃል፥ “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ካለ በኋላ፥ ከእርሱ የምናስበልጠው ማናቸውም ነገር ከእርሱ ሊለየን እንደሚችል በግልጥ ቃል ተናግሯል፡፡ (ማቴ.6፥24 ፤ 10፥35-39) ስለዚህም ጌታ ኢየሱስን እንደወንጌሉ ቅዱስ ቃል ሊያገለግል የተጠራ ቅዱስ አገልጋይ ዘወትር ራሱን በመግዛት ሊኖር ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ራስን መግዛት የራስን የውስጥ ፍላጐትና ስሜትን መቆጣጠር የሚያመለክት ፤ ለምናገለግለው ለቅዱስ ወንጌሉ ክብር ራስን በንጽዕና መጠበቅን የሚያካትት ነው፡፡
    ራስን አለመግዛት የመርከብን ጉዞ በአግባቡ ከማይመራ የመርከብ መሪ ጋር ማመሳሰል እንችላለን፡፡ በትግባራዊ ምልከታ ብናቀራርበው ጸጥና ዝግ ባለው ባሕር ላይ ብቻ ሳይሆን ማዕበልና ወጀብ ፤ ነፋስም በበረታበትና ባየለበት ሥፍራ መርከቢቱን የመምራት ሥራ የመርከቢቱ መሪ ዋናውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ርኩሰትና ኃጢአት በበዛባትና የአጋንንት ውጊያ ባለባት በዚህችም ምድር ላይም ራሱን በመግዛትም ይሁን ባለመግዛት አገልጋይ በራሱ ላይ ለሚያደርገው የትኛውም ነገሩ ኃላፊነቱን ወሳጁ ያው እሱና እሱ ብቻ ነው፡፡
    ራሳቸውን የማይገዙ አገልጋዮች ከጌታ ጋር ለብዙ ዘመናት ቢያሳልፉም፥ የሚፈልጉትን እስኪያገኙ እንጂ የሚፈልጉትን ሲያገኙ ዘወር ማለታቸው አይቀርም፡፡ ዛሬ ላይ የምናያቸው ብዙ አገልጋዮች እንዲህ ባለው ነገር ሰለባ ሲሆኑ ማየታችን ነው፡፡ በብዙዎቻችን ዘንድ የምናውቃቸውና ትምህርታቸው “ደስ ደስ” የሚያሰኝ የነበሩና በአሳማጸኝነትና በአሳዳሚነት ፤ እንዲሁም በፌስ ቡክና በግል ድኅረ ገጻቸው በስድብ ፣ በዘለፋ ፣ በንቀት ፣ ብዕራቸውና እጃቸው ለወንጌል ጠላት በመሆን ያገለግሉ የነበሩት አገልጋዮች በአንድነት ቲያንስ በሚባለው የንግድ ማኅበር ጎጆ ሥር ተስማምተው ተዳብለዋል፡፡
    ሁለቱም አይነት አገልጋዮች በእግዚአብሔር ሕዝብ ፊት ሲመላለሱ ወንጌሉን ጨብጠው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ በቅንነት ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከቅንነት ጎድለው ቢሆንም፡፡ ሁለቱም ዕውቅናንና መወደስን ያገኙት በእግዚአብሔር ቤት አደባባዮች ነበር፡፡ ብዙዎች ወደው፥ ከፍ ከፍ ያደረጓቸውና ያንቆለጳጰሷቸው በእግዚአብሔር ቤት ባላቸው “ትጋታቸው” ነበር፡፡ እኒህ ሁለት ወገኖች በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሳሉ የማይዋደዱ ፣ የማይቀራረቡ ፣ እንደደመኛ የሚፈላለጉ ፣ አንዱ ባለበት ጉባኤ ጨርሰው የማይደርሱ፤ የማይገኙ ፣በብዕር ስም የሃይማኖት ካባ አልብሰው የሚወራረፉ ፣ የሚነቃቀፉ ነበሩ፡፡
     እኒህ ሁለት ባላንጣዎች እጅግ በሚያስደንቅ (ወንጌሉን በእውነት የሚመረምሩ ምንም ባይደነቁም) ሁኔታ ፍጹም አንድ ሆነው ለወንጌሉ አንድ መሆን አቅቷቸው እንዳልተበላሉ ፣ እንዳልተነካከሱ ፣ እንዳልተጠፋፉ ፣ በአንዱ ጉባኤ ላለመገኘት እንዳልተጠነቀቁ ቲያንስ ግን “ያገለግሉት ከነበረው አምላካቸው እግዚአብሔር ይልቅ በልጦ” አስተሳስሯቸዋል ፤ አፋቅሯቸዋል ፤ አዋህዷቸዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ መልኩ ጎልድ ኩዌስትን ይመሩ የነበሩት የተለያዩ እንደባላንጣ ይተያዩ የነበሩ ሃይማኖት ነክ ቡድኖች ናቸው፡፡
    ዛሬም እኒህ “ነበር አገልጋዮች” በወንጌልና በጌታ ኢየሱስ ስም ያገኙትን ዝናና መታወቅ፥ ለአንድ ምድራዊ የንግድ ተቋም ሲጠቀሙበት ምንም አልሰቀጠጣቸውም ፤ ወንጌልን ከሰበኳቸው ወዳጆቻቸው ገንዘብን ሰብስበው፥ ለግል ጥቅማቸውና ለአንድ የንግድ ተቋም ሰብስበው ሲያከማቹ፥ “ይህን አስነዋሪ ነገር ለምን አደረጋችሁ?” ለሚሏቸው፥ የሚሰጡት ምክንያት ርካሽና ከአንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ ከሚል የማይጠበቅ ነው፡፡ በእርግጥ ግን፥ በእግዚአብሔር ስምና በወንጌሉ እየሸቀጡ እግዚአብሔርንና ቅዱስ አገልግሎቱን ከሚያሰድቡ በገዛ ወዝና ጥሪት ለፍቶ ፤ ግሮ ባዕለጠጋ መሆን ሲቻል ይህን አጸያፊ መንገድ ለምን ይሆን መረጡት?
    ጌታ ኢየሱስ ገንዘብን ለምን ጌታ ብሎ እንደጠራው የተረዳሁት ዘግይቼ ነው፡፡ ገንዘብ ሁለንተናን የመግዛት ኃይል እንዳለው ብዙዎቻችን አንረዳም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፥ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር እንደሆነና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን የወጉበት” ክፉ ነገር፥ ገንዘብ እንደሆነ ብዙም አናስተውልም፡፡ (1ጢሞ.6፥10) በጌታ ወንጌል እንደደመኛ ተጠላልተው በነጋዴ ማኅበር ፤ ስለገንዘብ መስማማታቸው ቀድሞውኑ የወንጌል ልብ ያላቸው ነበሩን? ያሰኛል፡፡ ለክርስቶስ ወንጌል ከአዲስ አበባ የማይወጡቱ ለንግዳቸው ግን ክፍለ ሀገርን ከማካለል አልፈው በወንጌል የሚያውቋቸውን ሁሉ ወደእነርሱ ኅብረት በማስቸኮል የሚያስገቡበት ሁኔታ እጅግ ያሳዝናል፡፡
    በእውኑ ግን እንዴት ተፋቀሩ? የኢየሱስን አዳኝነትና ጌትነት ለመመስከር የተሳሰረ አፍ፥ ግና ቲያንስን ተአምራዊ የብእልጥግና መንገድ አድርጎ በድፍረት መመስከር እውን የማደግ ምልክት ነውን? ጌታ ያላፋቀራቸው፥ ሎሌው ብርናወርቅ ያፋቀራቸው እኒህ “ግብዝ ወዳጆች” ይህ መንገዳቸው እስከየት ያደርሳቸው ይሆን? እውነት ለብርና ወርቅ እዚህ ደረጃ ድረስ መውረድ ነበረብን? ኢየሱስን ከስረን የምድሩ ብእል ሁሉ ከእኛ ጋር ከሚሆን፥ ከጌታ ጋር ሆነን ምንም ብዕል ባይኖረን እንደሚሻል የሰበካችሁን ቃል ወዴት አለ? … የጌታ ቃል ትዝ ካላችሁ እንዲህ ብሏል፥ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” (ሉቃ.12፥15)
   አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ሆይ!  ለሕዝብህና ለአገልጋዮችህ ማስተዋልን አብዛ፡፡ አሜን፡፡






   [1] እኒህን ብቻ የጠቀስነው ከርዕሳችን ጋር ለማዛመድ ነው እንጂ በክፍሉ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎችም አሉ፡፡ 

No comments:

Post a Comment