Tuesday 9 February 2016

ክርስቲያን ያልሆኑት ኦርቶክሳውያን ወይስ ምህረተ አብ?! (ክፍል ሁለት)

Please read in PDF
እግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” ማለት ምን ማለት ነው?
    የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ “ነገር ግን” በዚህ ሥፍራ ተጠቅሷል፡፡ “የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር።” በሚለው ቃል፥ “የእግዚአብሔርም” በሚለው ቃል ውስጥ “ም”፥ ነገር ግን ተብላ ልትጠቀስ ትችላለች፡፡ ምክንያቱም ፍጥረት ገና ሲፈጠር የነበረው ገጽታ አስፈሪና እጅግ ውስብስብ ነበር፡፡ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ መጥቶ በውኃ ላይ በረበበ ጊዜ ይህ አስፈሪ ገጽታ ተወገደ፡፡ ስለዚህም የምድርን ጥልቅ ሥፍራ ሁሉ ውጦት የነበረው ጨለማ የሥርዓት ባለቤት የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ፍጹም በመጠባበቅ ላይ መሆኑን ገላጭ ሃሳብ እንደሆነ እናምናለን፡፡

   የእግዚአብሔር መንፈስ ረብቦ የነበረው ባልተፈጸመና ሕልውናው በትክክል ባልተለየ ፍጥረት ላይ ነው፡፡ መርበቡ እንደእግዚአብሔር አብ ዕቅድ ታስቦ ፣ በእግዚአብሔር ወልድ ቃልነት ተፈጥሮ ያለውን ፍጥረት ሊያደራጅና ሥርዓት በማስያዝ ሊፈጽም መሆኑን ማስተዋል ይገባል፡፡ ይህን በትክክል ለመረዳት ቅዱስና ድንቅ የሆነውን የሥላሴን ትምህርት በሚገባ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡
   በእስራኤል ታሪክ እንዲህ ተፈጸመ፦
     እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ አውጥቶ በምድረ በዳ በመራ ጊዜ ንስር በጫጩቶቿ ላይ እንደምትረብብ (እንደምትሰፍፍ)፥ ሰፍፋም እንዴት እንደምትጠብቃቸውና እንደምታሳድጋቸው ባለ ምሳሌ ራሱን ገልጧል፡፡ (ዘዳግ.32፥11-12) እንዲሁ በፍጥረትና በመቤዠትም ሥራ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም በአምላክነቱ ሥራ መሥራቱን እናያለን፡፡ “የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጠኝ።” (ኢዮ.33፥4) “መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም፥ የምድርንም ፊት ታድሳለህ።” (መዝ.104፥30) የሚሉት ጥቅሶች የመንፈስ ቅዱስን ፈጣሪነት በትክክል ሲያሳዩ ፤ “እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል ይከልላታል፥ ይታደጋታል፥ አልፎም ያድናታል።” (ኢሳ.31፥5) የሚለው ደግሞ እንዴት ባለ መስፈፍ ሕዝቡን እንደሚጠብቅና እንደሚመግብ ፍጹም የሚያሳይ ነው፡፡
     ምህረተ አብ፥ እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አውድ ይህ ሆኖ ሳለ እርሱ አዲስ ትምህርት ማምጣት ለምን አስፈለገው? ምናልባት አያታችን ውኃ ነው እንዳለው ቅድመ አያታችን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው ብሎ፥ “እኛ ከመንፈስ ቅዱስ የሆንን መንፈስ ቅዱሳውያን ወይም መንፈስ ነን” የሚለውን የ“Faith Movt.”  ወይም የ“New age movt.” ትምህርት ሊያመጣ አስቦ ይሆንን?! በእርግጥም “አያቱ” ዘንድ ደርሶ ምነው ተመለሰ?
በእውኑ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን አይደለምን?!
     ክርስቲያን የሚለው ስም በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ (ሐዋ.11፥26 ፤ 26፥28 ፤ 1ጴጥ.4፥16) ቃሉ የተጠራው ለመጀመርያ ጊዜ በሶርያ አንጾኪያ ሲሆን፥ ስያሜውን ደቀ መዛሙርት የጌታ አማኞች ራሳቸው ለራሳቸው ያውጡት፥ ሌሎች የክርስትና ትምህርት ተጻራሪዎች ለመዘባበት ያወጡት ስም ይሁን ታላቁ መጽሐፍ የሚነግረን ነገር የለም፡፡
     ክርስቲያን የሚለው ቃል ትርጉም የግሪኩን “ክርስቲያኖስ” የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ “የክርስቶስ ተከታይ” የሚለውን ትርጉም ይሰጠናል፡፡ በእርግጥም ስሙ ለክርስቶስ የተለዩትና በእርሱም ብቻ የሚያምኑ ወገኖች የተጠሩበት ስያሜ ነው፡፡
     አንድ ግምት ማስቀመጥ እንችላለን ፤ ንጉሥ አግሪጳ ቅዱስ ጳውሎስን “በጥቂት ክርስቲያን ልታደርገኝ ትወዳለህ?” (ሐዋ.26፥228) ሲለው ስያሜውን ጠላት ለመዘባበት እንዳላወጣውና እንዲሁም በሶርያ አንጾኪያ ጠንካራ ከአህዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ (ሐዋ.13፥1) ስለዚህ በደፈናው “ክርስቲያን የሚለውን ስም ጠላት አውጥቶታል” ለማለት፥ ማስረጃ ካለማግኘታችንም በላይ ከጉንጭ አልፋ ክርክር ያለፈ ነገር አይኖረውም፡፡ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ካለ አብሮ ዝም ማለት ሲገባ፥ መጽሐፉን በግድ ማናገር ወይም ያልተናገረውን በግድ ለማናገር ስንፈልግ ብዙ ጊዜ ክህደት እንጂ አንዳች ትምህርት አናመጣም፡፡ እኛ በእግዚአብሔር ቦታ ካልሆንን መንፈስ ቅዱስ ዝም ማለቱ እጅግ መልካም ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ፥ “በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን” እንዲል፥ ክርስቲያን የሚለው ስም እጅግ የሚስማማንና የወደድነው ስማችን ነው፡፡ ምክንያቱም ስሙ የሚያመለክተው ተከታይ መሆናችንን ብቻ ሳይሆን የክርስቶስንም ስም የሚያመለክት እንደመሆኑ መጠን ፦
1.    ቤዛነቱን እናውጅበታለን ፤
    የቤዛነታችን መሠረትና ክርስቲያን የመባላችን እውነት ኢየሱስ ክርስቶስነው፡፡ (ሮሜ.3፥24) ተቤዥቶ የገዛን በወርቀ ደሙ ነው፡፡ (1ቆሮ.6፥19 ፤ 7፥23) ክርስቲያን የሚለውን ስም ከክርስቶስ ስንወርስ በእርሱ በመስቀል ሞትና ውድ ፍቅሩ ተማርከን የፈቃድ ባርያዎች ለመሆን በመውደድ ነው፡፡ ክርስቲያን ነን ስንል በእርሱ ቤዛነትን ያገኘን ነን ፤ ስለወደደንም ከአሸናፊዎች ሁሉ በእርሱ እንበልጣለን ማለታችን ነው፡፡ (ሮሜ.8፥38)
    ጠላት ለዘመናት የተዋጋው፥ ነገር ግን የተሸነፈበትና ያልቻለው ስም ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለውን ስም ነው፡፡ በዚሁ ልክ ለሁለት ሺህ ዓመታት በግልጥ የተሰበከው ፤ የታወጀው ሰማዕታትና ቅዱሳን ዋጋ የከፈሉበት ስም ፤ ኃጥአንንም በቤዛነቱ የቀደሰና ማርኮ ያሸነፈ ስም ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም ነው፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም የዲያብሎስ ሥራው የፈረሰበት ስምና ትውልድ ሁሉ ያጌጠበት የጽድቅና የቅድስና ስም ነው፡፡ ክርስቲያን የተባልነውም በዚህ ውድ ስም ነው! ታዲያ በዚህ ውድ ስም ላለመጠራት ማሰብ ምን ማለት ነው!?
     አንድ ነገር አምናለሁ ፤ በአለም ላይ ክርስቲያን በሚለው ስም የሚጠሩ በቢሊየን የሚቆጠሩ አማኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እኒህ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ አካላት ግን ለቁጥር የሚታክቱት ስሙን እንጂ ስሙን እንድንጠራበት ከወደደን ጌታ ጋር ምንም አይነት ዝምድናና ትስስር የሌላቸው በመሆኑ ምክንያት ክርስቲያን የሚለው ስም በሃይማኖተኞች ደብዝዟል ፤ የታለመለትንና መጽሐፍ ቅዱሱ የሚፈልገውን አማኝም ሊያፈራ “አልተቻለውም”፡፡
2.   ክርስቲያን ነን ስንል የክርስቶስን ሥልጣን አምነን መቀበላችን ነው!
    ክርስቲያን የተባልነው ክርስቶስን ስለተከተልን በእርሱም ስላመንን ነው፡፡ እርሱን የተከተልነው ደግሞ “የሃይማኖታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት” (ዕብ.3፥1) ፤ “የእምነታችን ራስና ፈጻሚው” (ዕብ.12፥2) ስለሆነና የቤተ ክርስቲያን ሁሉ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ስለሆነ ነው፡፡ (ራዕ.1፥20 ፤ 2፥23)
    እርሱ የክርስቲያን ማሕበረሰብ ሁሉ የበላይና ቀዳሚ ነው፡፡ እኔ ክርስቲያን ነኝ ስል ክርስቶስንና ቃሉን በላዬ ላይ መሾሜን ተቀብዬና አምኜ ነው፡፡ የትኛውም አማኝ ክርስቲያን ፤ ክርስቲያን ነኝ ሲል በራሱ ላይ የሾመው ክርስቶስን ስለመሆኑ ምንም ምስክር አያሻም፡፡ በስሙ እየተጠራ ሃይማኖተኛ ሆኖ የተቀመጠውን ግን እዚህ ውስጥ ማካተት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የክርስቶስን ሥልጣን የማይቀበሉ ፤ አምነውም በስሙ ያልዳኑ ብዙዎች ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩ አሉና፡፡
    ክርስቲያን ሆነው በመገኘታቸው ብቻ እልፍ አዕላፍ መከራን በመቀበል የኖሩትን የአላውያን ዘመን ሰማዕታት ክርስቲያኖች ምን ሊባሉ ይሆን? ለመሆኑ ከዲዮቅልጥያኖስ ሰባቱ የመከራ አዋጆች አምስተኛውና ስድስተኛው ምን የሚል ነበር? ማንኛውም ሮማዊ የመንግሥት ሠራተኛ ክርስቲያን ከሆነ ከሥራው እንዲባረር የሚልና ባሮች ክርስቲያን ከሆኑ ነጻ የመውጣት መብታቸው እንዲገፈፍ የሚል አይደለምን? አህዛብ እንኳ ክርስቲያን በሚለው ስም የክርስቶስ የሆኑትን መቃወማቸው ምን ያሳየናል?
     ደግሜ እላለሁ ፤ በእርግጥ ዛሬ ላይ ክርስቲያን የሚለው ስም ሃይማኖት በሚባል ነቀዝ ተበልቶ ሁሉ የሚጠራበት ሆኗል፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያን የተባሉት ምርጦቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ ናቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ቆመን የምንናገረው አንድ የተገለጠ እውነት ፤ እውነተኛ ክርስቲያን በክርስቶስ ያመነና ቤዛነቱንም አምኖ የተቀበለ ብቻ ነው፡፡ በሌላ ንግግር ኦርቶክሳዊ የሃይማኖት ተከታይ ሁሉ እውነተኛ ክርስቲያን ሊሆን ይገባዋል እንጂ ኦርቶክሳዊ ክርስቲያን አይደለም ማለት ከከባድ የስንፍና ንግግር የመነጨ ከመሆን አይዘልም፡፡
    ለኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምንጩ ክርስቶስ ነው ካልን፥ ለኦርቶክሳዊነት መመዘኛው የክርስቶስ ትምህርት ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ነው ማለታችን ነው፡፡ ኦርቶዶክሳዊነት ያለክርስቶስ ትምህርት ሕልው ሆኖ መኖር አይችልም፡፡ ኦርቶክሳዊ አማኝም የሚመዘነው ክርስቶስን አምኖ በሚኖረው ክርስቲያናዊ ቅዱስ ኑሮ እንጂ፥ ከክርስቲያንነት በተለየ ኦርቶዶክሳዊ “መልክ” ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥም፥ ምሕረተ አብ ክርስቲያን ስላልሆነ ኦርቶክሳዊነት ከክርስትናና ከክርስቶስ ሕይወት ጋር ምን ያህል ተዛምዶ እንዳለው ባያስተውል አይደንቅም፡፡
     ስለዚህ እውነተኛ ኦርቶክሳዊ፥ “በክርስቶስ ክርስቲያን ነኝ” ለማለት ያንገራግራል የሚል እምነት ፈጽሞ የለኝም፡፡ በሌላ ንግግር ክርስቲያን ክርስቶሳዊ ሲሆን፥ ክርስትና ደግሞ ክርስቶሳዊነት ነው ማለትን እንደፍራለን፡፡ ኑሮአችንና የሕይወታችን ለዛ ክርስቶስ ፤ ክርስቶስን ካልሸተተ ክርስቲያን አይደለንም ብንል ሐሰት አይደለም፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ኦርቶክሳዊነት ክርስቶሳዊ ከሆነ ክርስቲያንና ክርስቶሳዊነትን ከተዋሐደ እውነተኛ የክርስትና ምንጭ እንዲቀዳ እናምናለን ፤ እንታመናለንም፡፡ ኦርቶክሳዊነት ከዚህ ውጭ ሌላ የሚቀዳበት ምንጭ የለውም!!!
    አቤቱ ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ማስተዋልን ለሕዝብህ አብዛ፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል …



2 comments: