ምንም እንኳ ቀን ሰባራ ሆኖ ካርታና ድንበር ቢለያየንም፥ መሳ ለመሳ ሆነን
ባንተያይም አንድ ወንዝ አብረን ጠጥተናል ፣ ተጋብተናል ፣ ተዋልደናል ፣ ግማሽ እናቶቻችን እዚያ ግማሽ እናቶቻቸው እዚህ ፣ ግምሽ
ወንድሞቻችን እዚያ ግማሽ ወንድሞቻቸው እዚህ ፣ ግማሽ ልጆቻችን እዚያ ግማሽ ልጆቻቸው እዚህ አሉ ፤ የጋራ መልካም እሴቶች ፤ የሃይማኖት
አሻራዎች አሉን ፤ ተመሳሳይ መልክና ተመሳሳይ ታሪክ ፤ ተመሳሳይ ድኅነትና ቀና የማያስብልና የሚያሳፍር አስቀያሚ የጦርነት ገጽታዎች
አሉን፡፡ ኤርትራውያን ከኢትዮጲያውያን ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ብቻ ሳይሆኑ ምናልባት እንደጀርመን የልዩነት ግንቦቻቸውን
አፍርሰው “ወደፊት አንድ ሊሆኑ ከሚችሉ ሕዝቦች መካከል” አንዱ ሊሆኑም ይችላሉ፡፡
ይህች ወንድሞቻችንን ፣ እህቶቻችንን ፣ አባቶቻችንና እናቶቻችንን የያዘች
አገር አንድ ከባድ ነገር ከሰሞኑ አሰምታናለች፡፡ በአዲሱ የቤተሰብ ሕጓ፥ “አንድ ወንድ ሁለት ሚስቶች እንዲያገባ አስገዳጅ ሕግ
በመደንገግ” እጅግ አስቀያሚና ቅዱሱን የጋብቻ ኪዳን የሚሽር ሕግ አውጥታለች፡፡ ሰምቼ እውነታውን ባረጋገጥኩ ጊዜ ባለማመን ተደንቄ
አመላልሼዋለሁ፡፡ በእርግጥ ሕጐች ብዙ ጊዜ የሚቀረጹትና የሚደነገጉት ማኅበረሰቡ ከኖረባቸውና ካዳበራቸው መልካም እሴቶች ፣ አለም
አቀፍ ስምምነቶችንና ሌሎችንም ጠንካራ ምክንያቶች መሠረት በማድረግ ነው፡፡
ኤርትራ ከኢትዮጲያ ጋር አንድ የሚያደርጋት ሥነ ማኅበረሰባዊ እሴትና ባህል
፤ ሃይማኖታዊ ዳራ እንጂ ሁለት ሚስትን ሊፈቅድ የሚችል ማኅበረሰብን ማፍራት ደረጃ እንዳልደረሰች ወይም እንዳላፈራች ማስተዋል አያዳግትም፡፡
ባልተጠበቀ ሁኔታ ግን መልካም ማኅበረሰባዊ እሴት ያላቸውና ጋብቻ በቅድስናና በክብሩ ተከብሮ በሚኖርባቸው አገራት ላይ የምናያቸው
“ቅጽበታዊ ውሳኔዎች” የነገሮች መልክ ሲለዋውጣቸው እናያለን፡፡ ግብረ ሰዶማዊነትን ያጸደቀችውን ተመሳሳይ አገር አየርላንድን ማንሳት
ይቻላል፡፡
ኢትዮጲያውያንና ኤርትራውያን በየአገራቸው እንጂ ከአገራቸው ውጪ በጋራ
በሚኖሩባቸው “የስደት ምድር” በአንድነት እንደሚኖሩ የሚያሳዩ ብዙ መድረኮች አሉ፡፡ እንደቅርበታችንና አብሮ እንደሚኖር ማኅበረሰብ
አንዱ ባንዱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ እንኳን እንዲህ “በአንድነት እየኖርን” አይደለም፥ ጥቂት ዓመት በዲያስፖራነት ቆይተው
የሚመጡት ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ይዘው የሚመጡት መርዛዊ መዘዝ እንደዋዛ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡
እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባሉትን እስራኤልን ከአህዛብ
ጋር እንዳይጋቡ በተደጋጋሚ የከለከለው አህዛባዊ ልማድንም ጭምር አንዳይወርሱና እንግዶች አማልክትንም እንዳያመልኩም ለማስጠንቀቅም
ነበር፡፡ (ዘፍ.24፥2 ፤37 ፤ 27፥46 ፤ 28፥1 ፤ 34፥14 ፤ ዘጸ.34፥16 ፤ ዘዳግ.7፥3 ፤ 17፥17 ፤ 20፥17 ፤
ኢያ.23፥12-13 ፤ መሳ.3፥6 ፤ 14፥2 ፤ ዕዝ.9፥2 ፤ 10፥2
፤ ነህ.10፥30) በጥቂቱ እኒህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እስራኤል ከአህዛብ ጋር በማናቸውም መልኩ መጋባትም፤ መዛመድም እንደሌለባቸው
ከነውጤቱ ጭምር ይነግራቸዋል፡፡ ከዚህ ላቅ ባለ ትርጉም እግዚአብሔር እስራኤልን እንደሚስት ራሱን እንደባል ያቀረበበትንም ምሳሌ
ብናይ፥ (ኤር.3፥14 ፤ ሆሴ.2፥21) ጋብቻ የሁለት አካላትን ፍጹም ትስስርና ታማኝነትን የሚገልጥ ሥነ ሥርዓት መሆኑን ነው፡፡
ጋብቻ በአለማችን ላይ ባሉ እጅግ ብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ በአንድ ወንድና
በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጸም ቅዱስና የተከበረ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ እግዚአብሔርም ሲመሠርተው በአንድ ወንድ በአዳምና በአንዲት
ሴት ሔዋን መካከል በፍጥረት መፈጠር ጊዜ መሥርቶታል፡፡ በኋለኛው ዘመን በመጣ ጊዜም በትምህርቱ አጽንቶታል፡፡ (ዘፍ.2፥18-25
፤ ማቴ.19፥3-6)ሞት ካልለያያቸው በቀርም ሊለያዩና ወደሌላ ማየት እንደማይገባቸው ነገራቸው፡፡ (ዘፍ.2፥24)
ወንዶች ክርስቲያኖች ክርስቲያን ሳሉ አንዲት ሴት ብቻ እንዲያገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
(1ቆሮ.7፥2-3) ከአህዛብ የተመለሱ ክርስቲያን ወንዶች ግን ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ሁለት ሚስት ቢያገቡና ክርስቲያን ቢሆኑ፥
ሚስቶቹን ምን ማድረግ አለባቸው? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ የምላሽ አቋሞች ቢኖሩም፥ ወደመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስናደላ ለጋብቻ ቅድስናና
ክብር፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ሊሰጠው ካለው አገልግሎት አንጻር (1ጢሞ.3፥2 ፤ ቲቶ.1፥6) ከአንዲቱ ጋር ብቻ እንዲኖር
ይገደዳል፡፡ ይህን ባያደርግ ግን እንዲያገለግል አልተባለለትም፡፡ አሁንም በአዲስ ኪዳን ሙሽሪት ቤተክርስቲያን ለሙሽራዋ ኢየሱስ
ክርስቶስ የታጨችና የተለየች ናት፡፡ (ኤፌ.5፥26 ፤ 32)ክርስቶስ አንዲት ቤተክርስቲያን እንዳለው ሁሉ ቤተክርሰቲያንም ከእርሱ
በቀር ልታመልከውና ልትገዛለት የሚገባት አንዳች ሌላ የለም፡፡
ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ውጪ ብታመልክ፥ ልክ ቤተ እስራኤል ጣዖትን በማምለክ
በእግዚአብሔር ላይ እንዳመነዘረችው (ኤር.3፥9) ቤተ ክርስቲያንም በክርስቶስ ላይ ታመነዝራለች፡፡ (ማቴ.12፥39) አንድ ባልም
ከአንዲት ሚስቱ ውጪ የሌላይቱን ሴት ገላ አይቶ አብሮ ቢተኛ ብቻ ሳይሆን በልቡ ቢመኛት ያመነዝራል፡፡(ማቴ.5፥27-28)
ከአንድ በላይ ሚስትን ማግባት፥
1. ለእግዚአብሔርና ለቃሉ ታማኝ አለመሆንን
፤
2. የገዛ ቅድስናን በገዛ እጅ መጣልን
፤
3. ክርስቲያናዊ ባልሆነና ኢ ግብረ
ገባዊ በሆነ አህዛባዊ ርኩሰት መጠመድን በትክክል ያሣያል፡፡ ይህ ደግሞ ፍጹም አመንዝራነት ነውና ከሕይወት መጽሐፍ ከማስደምሰሱም
ባሻገር ከመንግሥቱ ውጪ የሚያስቀር መሆኑን መጽሐፉ በማያሻማ ቃል አስቀምጦታል፡፡ (1ቆሮ.6፥9 ፤ ገላ.5፥22 ራዕ.21፥8 ፤
22፥15)
ታዲያ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፤ አባቶቻችንና እናቶቻችን ኤርትራውያን!
ይህ እውነት ተሰውሮአቸዋልን?! ጠንካራ ሰንበት ትምህርት ቤትና ብዙ መነኮሳትና ጳጳሳት ያላት ኤርትራ ምን ነክቷት ይሆን የገዛ
ምድሯን በዝሙት ለማንደድ የታጠቀችው? ምነው ጋብቻን አክባሪና አስከባሪ ተቆርቋሪ የባህል መሪዎቿ ወዴት አሉ? (በታሪክ እስከቅርብ
ድረስ እንደምናውቀው ኤርትራ ብዙ ጠንካራ አባቶች ፣ እናቶች ፣ ወንድሞችና እህቶች ነበራት)
ወደእኛ ስመለስ፥ መቼም እንዳለመታደል ለእኛ እፈራለሁ ፤ መልካሙን
ነገር ቶሎ ከጎረቤት የመቅዳትና የመውሰድ ልማድ የለንም ፤ ክፉና አጸያፊው ላይ ከመቸኮልና ከመረባረብ በቀር፡፡ የእኛ ቤት ጭስስ
ምን ምን ይሸታል? የሐረሪ ክልል ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት እንደሚፈቅድ በቤተሠብ ሕጉ አስፍሯል፡፡ ነገ ወደሌሎች ላለመዛመቱ
ምን ማስተማመኛ ይኖረን ይሆን? ጋብቻን የሚያከብርና የሚወድድም ትውልድ እንዲመጣ አብዝቶ የመጸለዩ ጊዜ በእውነት አሁን ፤ አሁኑኑ
ነው፡፡
No comments:
Post a Comment