Monday 1 February 2016

ደሙን ካንተ ይሻል!


እንሰሳት አራዊት ፤
አዋቂ ሕጻናት ፤
ምድር ተገልብጣ ፣ ልትተኮስ በʼሳት ፤
አመድ ብናኝ ልትሆን ፣ በፍህም ቀጠሮ ፤
ደስታዋ ሊሰበር ፣ በዋይታና ሮሮ …

ሞት በደጇ አድብቶ ፤
 ኃጢአት ሕዝቧን ገዝቶ ፤
ጎብጣ ለምትሄድ ፣ ለነነዌ ምድር ፤
ዮናስ ስበክ እንጂ ፣ ተርሴስ አትሻገር፡፡

ተመለሱ! ተዉ! ኃጢአታችሁ ይብቃ ፤
ለምን ልብሱ ብቻ? ልባችሁም ይጽዳ ፤
ጮኸኽ  ይህን እውነት ፣ ደፍረህ ብታስረዳ ፤
ነቢዩ ዮናስ ሆይ! ምንህ ነው ሚጎዳ!?

የበደለን ወቅሶ ፣ ለንስሐ ማብቃት ፤
በቃለ እግዚአብሔር ፣ ከርኩሰቱ ማንጻት ፤
እውነት ለመናገር …
አክሊል አለው ዋጋ ፣ የበዛ መቶ እጥፍ ፤
በሰማይ አባት ፊት ፣ ክብር የሚያጎናጽፍ፡፡

ዳሩ!
ሕዝብን ለʼሳት ጥሎ ለእሾኽ አሜከላ
ለራስ ብቻ ብʼኖር በቅምጥል ተድላ…
ሰባኪ ሆይ ስማ!
የሟቹን ሞት መሞት የማይፈቅደው ጌታ

ደሙን ካንተ ይሻል ላልጮኽከው ዝምታ፡፡

No comments:

Post a Comment