Friday 19 February 2016

“እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ” (ዮና.3፥10)

   
    ታላቂቱን የአሦርን መናገሻ ከተማ ነነዌን የመሠረተው፥ በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ አዳኝ የነበረው የኩሽ ልጅ ናምሩድ ነው፡፡ (ዘፍጥ.10፥11) የከተሞች መመሥረት የክፋትና የኃጢአት ዝንባሌዎችና ተጽዕኖዎች ሁሉ በአንድነት ለመገኘት ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያለብን የከተማ ችግር ሰዎች በብዛት ሆነው በአንድ ላይ በመኖራቸው ምክንያት ሳይሆን፥ በአእስራኤልና በአህዛብ ከተሞች እናይ እንደነበረው የጦርነት ምሽጎችና መሣሪያዎች፥ እንዲሁም ያለእግዚአብሔር ከመኖር ዐመጸኝነትና አለመታዘዝ ማዕከልነት ውስጥ መመንጨቱ ነው፡፡ ነቢዩ አሞጽ፥ “በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና ፦ በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ፡፡ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥  … ” (አሞ.3፥9-10) በማለት በከተማ የሚሠራውን ነገር በግልጥ ያስቀምጣል፡፡

      ነቢዩ አሞጽ በሰማርያ ምሽጎች ውስጥ አግባብነት የጎደለውን ሃብት ባከማቹት ላይ እግዚአብሔር ላቀረበው ብርቱ ወቀሳና ክስ ምስክር ይሆኑ ዘንድ የፍልስጥኤምንና የግብጽን ባዕለጠጎች ይጠራል፡፡  ሰማርያ ሃብትን አለአግባብ ማከማቸቷ ብቻ በውሰጧ ታላቅ ሁከት ነበረባት፡፡ ይህንን በአውዱ ካየነው ከግል ጥቅም የተነሳ የሚደረግን የሥልጣን ተዋረድ ፣ በግድ የለሽነት ያለመታዘዝንና ዐመጸኝነትን ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ አስጨናቂውና ልብ የሚነካው ነገር የእስራኤል ብልጥግና መነሻው በጭቆናና በዝርፊያ ፤ በቅሚያ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም ነውርና ዕድፈት ፤ ድሃ ለተበደለበት ፍጹም ኃጢአት ፍርዱ፥ “እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቆችም ቤቶች ይፈርሳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (ቁ.14-15) በማለት ተገልጧል፡፡
    በሌላ ሥፍራም፥ “ይህ ሁሉ ስለ ያዕቆብ በደልና ስለ እስራኤል ቤት ኃጢአት ነው። የያዕቆብም በደል ምንድር ነው? ሰማርያ አይደለችምን? የይሁዳስ የኮረብታው መስገጃ ምንድር ነው? ኢየሩሳሌም አይደለችምን? ስለዚህ ሰማርያን በሜዳ እንደሚገኝ የድንጋይ ክምር፥ ወይን እንደሚተከልበትም ስፍራ አደርጋታለሁ ድንጋዮችዋንም ወደ ሸለቆ እወረውራለሁ፥ መሠረቶችዋንም እገልጣለሁ።” (ሚክ.1፥5-6) ድርጊቱና ፍርዱ በአንድነት ተገልጦ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህም ለእስራኤል መቤዠት የሚሆነው በከተማ ሳይሆን ከከተማ ውጪ ሊሆን እንዳለ ቁርጥ ቃል በነቢዩ አንደበት ተገለጠ፡፡ (ሚክ.4፥9-10)
     ነቢያት ባለጠግነት በራሱ ኃጢአት ነው ብለው አያስተምሩም ፤ አላስተማሩምም ፤ “ባለጠጋና ድሀ ተገናኙ እግዚአብሔር የሁላቸው ፈጣሪ ነው።” እንዲል ፥(ምሳ.22፥2) ዳሩ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፦“ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ።” (1ጢሞ.6፥9) እንዳለው በምኞት ሲጠመድና ሃብትን ለማግኘት ሲያስብና የሚገባውን ሳያደርግ ሲቀር የዚያኔ ኃጢአት ይሆናል፡፡ 
     ከተማይቱ ነነዌም ማኅበራዊ ኃጢአትን በከተማዋ ያበዛችና እንደሰዶምና ገሞራ ክፋቷ በእግዚአብሔር ፊት የወጣ ነበረች፡፡ (ዘፍጥ.18፥20-22 ፤ ዮና.1፥2) በእግዚአብሔር ፊት የወጣው የነነዌ የክፋት ኃጢአት በነቢዩ ዮናስ ውስጥ ተጽፎ ባናገኘውም ነቢዩ ናሆም በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ (ናሆ.1፥11 ፤ 2፥12 ፤ 3፥1-4 ፤ 16) እኒህ ኃጢአቶች እግዚአብሔርን ፍጹም አስቆጥተውታል፡፡
    በዘመናት እርጅና የሌለበት እግዚአብሔር፥ ዛሬም በዚህ ቃል መነጽርነት ከተሞቻችንን ፣ የ“ባለጠግነታችንን ምንጭ” ፣ ሥልጣንን የያዝንበትን መንገድ ይመረምራል፡፡ የእኛ ከተሞች ምን ይመስላሉ? ኃጢአት አልገነነባቸውም ይሆን? እስኪ እንዲህ ብለን ስለራሳችን እንጠይቅ፥ በመዲናችን “Rainbow” የሚባለው የግብረ ሰዶማውያን ማኅበር ምን እያደረገ ይሆን?! በእውኑ ለጎዳና ተዳዳሪ ልጆች ጎጆ እየቀለሰ ነው ወይስ … ? አዳሪ ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ ምን እየተደረገ ነው? ልጆቻችንን እያስተዋልናቸው ነውን? አዲስ አበባ ውስጥ ከሚደረጉት አስገድዶ መደፈሮች 22% የሚሸፍነው ከአሥራ አራት ዓመት በታች በሆኑ ወንዶች ላይ ነው የሚለው ጥናት ምንን ነው የሚያሳየው? ያውም ከዚህ ውስጥ43.7% የሚሆኑት በቅርብ ዘመዶቻቸው መደፈራቸው ምንን ያሳስበናል? በአገራችን በሚገኝ በአንድ የታወቀ ዩንቨርሲቲ በሴቶች ማደርያ(ዶርም) ክፍል በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 130(አንድ መቶ ሠላሳ) አርተፊሻል ወሲብ መፈጸሚያ ቁሳቁሶች መገኘታቸው ምን ጠቆመን ይሆን? ቦሌ ፍሬንድ ሺፕ ፣ ድልድዩ ፣ ሸዋ ዳቦ አከባቢ ፣ ፒያሣ ዘ ኬቭ (ግብረ ሰዶማውያኑ ለመጀመርያ ጊዜ ተመሠረቱ ተብሎ በሚነገርበት) ፣ በአንዳንድ ጥንታውያን ሆቴሎቻችን ግብረ ሰዶማውያን ምን እየሠሩ ነው? … የወንጀል ሕግ አን.629-631 ያሉት ሕጎች እኛ ሳናውቃቸው ተሰርዘው ይሆንን? ትምክህተኛይቱ አገር ኢትዮጲያዬ ሆይ! የት ነው ያለሽው? መዲናሽና ከተሞችሽ ምን እያደረጉ ነው?[1]
     ሃብታሞችሽ ምን እየሠሩ ነው? ጭቆናና ዝርፊያ ፤ ቅሚያ ላይ አልተሠማሩ ይሆን? ድሃ አደጉን አልበደሉት ፣ አልገፉት ይሆን? በአሥርት ሚሊየን የሚቆጠሩ ልጆችሽ በረሃብ አንጀታቸው አሮ ፤ ፊታቸው በጥማት ሲከስል የደነገጠላት ሃብታም ማን ነበር? ሃብታሞችሽ ከኮረዳዎችና ከመጠጥ ጭን ሥር ወጥተው ይሆን? ቢራ ፋብሪካና ሆቴል ፤ ሞቴል ከመክፈት ባለፈ መች ይሆን የዳቦና የመድኃኒት ፋብሪካ ፤ ቤተ መጻሕፍትና ጥራት ያላቸውን ትምህርታዊ ተቋማትን መመሥረት የሚታያቸው?  ይህን የምለው በታማኝነት እግዚአብሔርን በመፍራትና አገራቸውንና ወገናቸውን በመውደድ የሚያገለግሉ እጅግ በጣም ፤ በጣም ጥቂት ባዕለጠጎችን አይመለከትም፡፡
     ባዕለሥልጣኖችሽስ ከግለኝነትና ከዘረኝነት አዚም ተላቀውልሽ ይሆን? ሥልጣናቸውን ለተራበውና ለድሃው ሕዝባቸው አውለውት ይሆን? ዳኛሽ ምን እያደረገ ነው? ለተጠቃውና ለተበደለው አድልቶ ይሆን? ፖሊሶችሽ ምን እየሠሩ ነው? ያልተያዘውን ንጹሕ እያሳደዱ የተያዘውን ሌባ እየለቀቁ ይሆን? ሃብታሙን ፈርተው ድሃውን አንጠልጥለው ከጨለማው እስር ቤት እየወረወሩ ይሆን? ኢትዮጲያዬ ሆይ! ከወዴት ነው የወደቅሽው? ይህ ሁሉ ሲሆን የሃይማኖት መሪዎችሽ የት ያሉት? በየከተሞችሽ የሚሰማው ጩኸት ፤ የሚፈሰው ደም ፤ የሚቃጠለውና የሚወድመው ሃብት ምንድር ነው? እንዲህ ለማቃጠልም የሚበቃ ሃብትና ንብረት ተርፎሻልን? አንድ ማኅበር እንደቅርጫ ሥጋ ከፋፍሎ የሚያናትፋቸዋል እኒህ የኃይማኖት መሪዎችሽ ምንድር ናቸው?! እናቴ ኢትዮጲያ ሆይ! ማነው ወዳጅሽ? ማነው የራራልሽ ፤ ያዘነልሽስ?
     ነነዌ ከዚያ ሁሉ ክፋቷ የዮናስን ስብከት በሰማች ጊዜ፥ ወዲያው አዋጃዊና ብሔራዊ ንስሐን በአገሩ ሁሉ አስነገረች፡፡ ከንጉሡ እስከ ምዕመኑ ሁሉም በአንድነት ፤ እንሰሳትም ጭምር ሁሉም “ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ።” (ቁ.9) የሚል ጽኑዕ ቃል ከቤተ መንግሥቱ ወጣ፡፡ አዋጁን የሰማ ሁሉ ግፍንና ክፋትን ያደርግ ከነበረበት መንገዱ በፍጹም ልቡ ተመለሰ፡፡ “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ፥ እግዚአብሔርም ያደርግባቸው ዘንድ በተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም።” (ቁ.10)
     በኃጢአታችን ሁሉ ለሚመጣብን የእግዚአብሔር ቁጣ መመለሻው መንገድ አንድ ብቻ ነው ፤ እርሱም ፍጹም በሆነ ልባዊ ንስሐ ከክፉ መንገዳችንና ግፋችን ሁሉ ወደእግዚአብሔር መመለስ ብቻ ነው፡፡ “ቅድስት አገር” በሚል ከንቱ ትምክህት ስንመካ፥ ኢትዮጲያን የ“Sex tourism” ለማድረግ በውጪና በአገር ቤት ተደራጅተው የሚሠሩ ብዙ አካላት ተነስተዋል፡፡ የዚህ ሁሉ ክፋት ተጠናቆ ሳናይና፥ ነውርን እንደውኃ ጭልጥ አድረግን ጠጥተን ሳንዋሃዳት ጭልጥ ብለን ከተኛንበት ማንነታችን በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት እንነሳ፡፡ ጾሙን በልማድ ሳይሆን ርዕስ አበጅተንለት ፤ በፍጹም የይቅርታ ልብ በመሆን ሁላችን ልንጾም ይገባናል፡፡ አልያ በርቀት ያየነውና የሰማነው በማጀታችን ሊሆን እነሆ በደጅ አለ!!! በእነትና ከልብ የሆነውን የልባችንን ንስሐ አይቶ ይቅር ይለን ዘንድ በእምነት ንስሐ በመግባት እንመለስ፡፡
     አቤቱ ሕዝብህን አድን ፤ ርስትህን ባርክ ፤ ካህናትህንም አክብር፡፡ አሜን፡፡





    [1] ስለግብረ ሰዶማውያን ይህንን የማነሳው ለማሸማቀቅና እንዲገለሉ ለማድረግ አይደለም፡፡ ከኃጢአታቸው ጋር ግን ፈጽሞ እንደማንደራደር ማሳየት ፤ ነውርና ርኩሰት መሆኑን ማሳየት ግና እዳው አለብን፡፡ ከክፋታቸው ተመልሰው በክርስቶስ ደም ታጥበውና ነጽተው ፤ ነጩን የቅድስና ልብስ ለመልበስ መሻቱ በውስጣቸው ካለ ልንረዳቸው መቼም ዝግጁዎች ነን ፤ እንዲሁ በእልኸኝነት ተነሳስተው ትውልድን ለመመረዝ ሲነሳሱ ደግሞ ሌሎች ከክፋታቸው እንዲርቁ ይህን ማለት ግድ ይለናል፡፡

No comments:

Post a Comment