Saturday, 29 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት (ክፍል - 3)

1.    ምስጋና
       ለምስጋና የተሟሸ ቃል የምናወጣው፥ መንፈስ ቅዱስ አንደበታችንን ሲቃኘውና እኛም ቃሉን ከጸሎት ጋር በማጥናት የበሰለ ማንነትን መያዝ ሲቻለን ነው፡፡ እንዳንዶች ተአምራቱን አይተው ድንቅ መዝሙርን (ዘጸ.15፥1-21) ፤ አንዳንዶች በፊቱ ራሳቸውን በማፍሰስ ላደረሱት ጸሎት ምለሹን ከለመኑት ጌታ ባገኙ ጊዜ (1ሳሙ.2፥1-10) ፤ ሌሎች ደግሞ ድልን በፊቱ ባገኙ ጊዜ (መሳ.5፥1-31 ፤ 16፥24) ፤ የበረቱቱ ደግሞ ሙሉ ተስፋቸው እግዚአብሔር መሆኑን በመታመን (ዕን.3፥1-19) በእግዚአብሔር ፊት እንደዘመሩ ድንግል ማርያምም ልዩና ድንቅ ነገር በእርሷ እንደተደረገ ባመነች ጊዜ በቃሉ መሞላት ውስጥ ሆና የዘመረችው መዝሙር እጅጉን ልብ የሚነካ ነው፡፡
      አባቷ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት (ማቴ.1፥20 ፤ ሉቃ.1፥27 ፤ 32) በገና እየደረደረ መልካም አድርጎ ይዘምር የነበረ መዝሙረኛ (1ሳሙ.16፥18-23 ፤ መዝ.33፥2) ፤ የመዝሙር መጽሐፎቹም በምስጋናና በውዳሴ እጅግ የተመሉ ነበሩ፡፡ (መዝ.111-117) ድንግል ማርያምም ከእርሱም ተምራለችና በምስጋና ተመልታ ስታመሰግን እናያታለን፡፡ ቃሉም ፥ “… በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (1ተሰ.5፥17-18) እንዲል፡፡
       ምስጋና የማጉረምረም ፤ የሽንገላ ፤ የሐሰተኝነት ፤ የስድብና ያለማመስገን ተቃራኒ ነው፡፡ (ዘጸ.16፥2 ፤ ዘኊል.14፥26-30) ዲያብሎስ ዘማሪ ስለነበር ፥ ከዚህ ክብሩ በገዛ ትዕቢቱ ሲዋረድና ሲወርድ ሸንጋይ (ኤፌ.4፥14 ፤ 6፥11) ፣ የእግዚአብሔርን ክብርና ሥራ በመንቀፍ የሚሳደብ (መዝ.74፥10 ፤ ኢሳ.52፥5 ፤ ራዕ.13፥5) ፣ በድምጹ ብቻ እያገሳ የሚያስፈራራ (1ጴጥ.5፥8) ፣ ሐሰተኛ (ዮሐ.8፥44) ሆነ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔርን (ዘሌ.24፥16 ፤ 1ነገ.20፥10) ፤ እናትና አባቱን የሚሰድብ (ዘጸ.21፥17 ፤ ምሳ.20፥20) እንዲገደል ፍርዱ እንዲሆን በሕግ የተደነገገው፡፡

      ድንግል ማርያም የዚህ ተቃራኒ አንደበቷን በምስጋና መልታ እናያታለን፡፡ በእርግጥም ከእግዚአብሔር የሆነ የቃሉ ሙላት ያለው ሰው ፈጽሞ የመሳደብ አቅም አይኖረውም፡፡ (ማቴ.5፥22 ፤ 7፥22 ፤ ኤፌ.4፥31 ፤ ይሁ.8-9) “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።” እንዲል ስድብ የሥጋ ፈቃድ ሲያይልና ሲያሸነፍ ከአንደበትና ከልብ መዝገብ የሚወጣ እንጂ ከቅዱስ ቃሉ ምንጭነት የሚፈልቅ አይደለም፡፡
     እኛ ከክርስቶስ የተማርነው መራርነትና የስድብ አንደበትን አይደለም ፤ እርሱ መብቱን መናገር በሚችልበት ቦታ እንኳ የዝምታን ኃይል ብቻ ነው የተጠቀመው፡፡ (ማቴ.27፥12) ድንግል ማርያምንም ያየን እንደሆን እንኳ ብዙ መለኮታዊ ምስጢሮችን አይታ እንኳ “ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር።” (ሉቃ.2፥19 ፤ 51) የሚል ድንቅ ቃል እንጂ ማጉረምረምም ሆነ ሌላን ነገር ስትናገርም አንሰማም፡፡ በተለይም አረጋዊው ስምዖን “በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል” (ሉቃ.2፥35) ያላትንም ቃል አስበን በመከራው ዘመንም በዝምታ የተከተለች እናት መሆኗን ማስተዋል እንችላለን፡፡ (ዮሐ.19፥26)
     በተለይ በዛሬ ዘመን በግልጥ “ለእግዚአብሔር ቀንተናል የሚሉ ክርስቲያኖች” እየፈጸሙት ያሉት ነገር ቢኖር ስድብ ፣ አሽሙር ፣ ሐሰት ፣ ሽንገላ ፣ … ከምንም ጊዜ በላቀ ሲፈጸም እያየን ነው፡፡ ብዙ ጊዜም የተፈቀደ እስኪመስለን ሲሆን እያየን ያለነው ነገር እጅግ የሚሰቀጥጥ ነው፡፡ በእርግጥም “ለመልካም እየቀናን ነው” ብሎ ስድብ ከየት ነው ይሆን ምንጩ? ድንግል ማርያምን እንወዳለን ካልን እንዴትስ ነው ለእርሷ በስድብ መንፈስ የምንሟገተው? ለምንስ ይሆን በስሟ ቃሉ የማይለውን ነገር ስናደርግ የማናፍረው?

2.   ትህትና

      የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና በጸሎት ላይ ሳለች በፍጹም ትህትና ራሷን በማፍሰስና በማዋረድ ውስጥ ነበረች፡፡ ካህኑ ዔሊ ግን  በእርሷ በእግዚአብሔር መሠጠትና መዋረድ ላይ ያፌዝና ይሳለቅም ነበር፡፡ (1ሳሙ.1፥13-14)
      ትህትና ባዶ ዝቅታ ሳይሆን ሙሉ ዝቅታ ነው ፤ ማለትም ሁሉን ስለማክበርና በውጣችን ካለው ፍሬ የተነሳ እንጂ በባዶ ማጎንበስ ፤ ለማስመሰልም የምናደርገው የሽንገላ መንገድ አይደለም፡፡ በሥልጣን እንዳላቸውና አዋቂ ነን ብለው የሚያስቡ ናቸው የሚፈተኑባት መንገድ የትህትና መንገድ ናት፡፡ ትሁት ለመሆን ሁሉ እያለን በመንፈስ ድኃ ሆኖ ዝቅ ማለትን ይጠይቃል፡፡
    ትህትና ጉልበት ዝቅ ብሎ የመሳምና አንገትን ሰብሮ የመስማት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ትህትና የልብ ጉልበት መስበርን ይጠይቃል፡፡ጌታችን ከሳምራዊቷ ሴት ጋር ደቀ መዛሙርቱ እስኪደነቁ እንዴት እንደተነጋገረ አስተውሉ! (ዮሐ.4፥27) ጌታችን እንዴት የደቀ መዛሙርቱን እግር እንዳጠበ አስተውሉ! (ዮሐ.13፥4-5) እግዚአብሔር አብ ልጁ ወልድ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት አለልክ ዝቅ ዝቅ ብሎ በትሁት ልብና መንፈስ እንደተመላለሰ አይቶ እንዴት በጌትነት ዙፋን አለልክ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አስተውሉ! (ፊልጵ.2፥6-11)
      ድንግል ማርያም የመልአኩን ብስራት እያደመጠች ትመስል የነበረው እጅግ በትሁት መንፈስ ፤ ራስዋን እንደአገልጋይ አቅርባ ከመልአኩ ጋር ትወያይ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት በሰማች ጊዜ “እነሆኝ የጌታ ባሪያ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” (ሉቃ.1፥38) ፤ “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና።” (ሉቃ.1፥48) በማለትም ራስዋን እንደባርያ የቆጠረችው፡፡ የተመረጠችው ለትልቅ አላማ እንደሆነ ብታምንም ፤ ለእግዚአብሔር ባቀረበችው ምስጋናዋ ላይ ግን ራስዋን እንደአገልጋይ ባርያ ነው የምትቆጥረው፡፡
       በእውኑ ዛሬ ማን ነው ራሱን በቤቱ እንደአገልጋይ የሚቆጥር? አስተውሉ! እያልኳችሁ ያለሁት አገልጋይ ስለሚባለው ዘማሪ ፣ ዲያቆን ፣ ቄስ ፣ ሰባኪ ፣ ጳጳስ ፣ … ስለነዚህ አይደለም፡፡ ልላችሁ የምወደው ማን ነው ዝቅ ብሎ ሊያገለግል የአገልጋይ መንፈስና ልብ ያለው? ነው የምላችሁ፡፡ ማን ነው ለሕዝቡ እንደባርያ ሊያገለግል የተነሳ? ማን ነው እኔ ልታዘዝ ፤ ላገልግል እንጂ ላዝዝ ፤ ልገለገል አይገባኝም የሚል? እንዲህ ማሰብ መበለጥ ፤ ሞኝነትም አይደለም፡፡ አዎ! አለልክ በትሁት መንፈስ ዝቅ ዝቅ ካላልን አለልክ ከፍ ከፍ የምንል እንዳይመስለን፡፡
ክብር ይብዛላችሁ፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment