የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ (ገላ.4፥4) በገሊላ ግዛት
ናዝሬት በምትባለው ከተማ፥ የሚያስደንቅ የምሥራች ዜና ተሰማ፡፡ ምሥራቹም
በኃጢአት የተበከለው ዓለም ሊቀደስ ፣ ለዓለሙ ሁሉ የሚሆን ምሥራችና መድኃኒት ሕጻኑ ኢየሱስ ሊወለድ እንዳለ ፣ መልአኩ ገብርኤል ከመለኮት ዙፋን ችሎት የተቆረጠውን ውሳኔ ሊያሰማ ወደምድር
መጣ፡፡ (ሉቃ.1፥26) ናዝሬት በሰው ሕሊና “መልካም ሰው አይወጣባትም ወይም አይገኝባትም” (ዮሐ.1፥47) ብትባልም፥ ዛሬ ግን
መልካም ሰው ድንግል ማርያም ተገኝቶባታል፡፡
ናዝሬት የክፉ ነገር ሁሉ መገለጫ ሆና በመጽሐፍ
ቅዱስ ተገልጣ ሳለ፥ ድንግል ማርያምን የምታህል ብላቴና ተገኝታባታለችና ፥ “ያለቀ የተቈረጠ ነገርን በምድር ሁሉ መካከል የሚፈጽመው ጌታ
እግዚአብሔር” (ኢሳ.10፥23) በሰው ሕሊና መልካም አይገኝብሽም ከተባለችው ናዝሬት፥
የኢየሱስ እናት ድንግል ማርያም ተገኘችባት፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የናዝሬትን ስም በመቀየር “የናዝሬቱ ኢየሱስ” ወደር ያልተገኘለት
ሆነ፡፡ ሰዎች ሰው አይወጣባትም ካሏት ከተማ መልካምነቱ ዳርቻ የማይወስነው ጌታ ተወልዶ አደገባት ፤ “የናዝሬቱ ኢየሱስ” ተብሎም
ሊጠራባት አላፈረም፡፡ (ሐዋ.22፥8) ሰው ተስፋ የቆረጠባችሁ ብትኖሩ እግዚአብሔር በእናንተ ሊሠራ የታመነ ነውና ባላችሁበት ለታመነው
ጌታ ታመኑለት፡፡
ድንግል ማርያም ምግባራቸው እንደእሾህ ወደእግዚአብሔር
በማያቀርቡ ሰዎች መካከል የጸደቀችና አብባም በፍሬዋ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘች ፤ “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና”
እንዲል በፊቱም ሞገስ ያገኘች እናት ነች፡፡ (ሉቃ.1፥30) በፊቱ ሞገስ የማግኘትዋንና በጌታ
ዘንድ የመመረጧን ነገር ድንግል ማርያም እንዲህ በማለት በጸሎቷ ተናግራዋለች፡፡ ይህንን ከማየታችን በፊት በጸሎቷ ውስጥ ያለውን
ድንቅ የሆነ የቃሉን ሙላት ጥቂት እናስተውለው፡፡
መጽሐፍ እንዲህ ይላል “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ።”
(ቈላ.3፥16) ድንግል ማርያም የቃሉ ሙላት እንዳላት ከዘመረችው መዝሙር በሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ክፉዎች በበዙባት በናዝሬት
ተቀምጣ ቃሉን ለዘወትር በልበ ሰፊነት ትመረምር ፤ ታጠናም የነበረች መሆኗን ያሳያል፡፡ ለብዙዎቻችን ትልቁ ድካማችን ለእግዚአብሔር
በማይታመኑ ሰዎች መካከል ሆነን በመታመን እግዚአብሔርን ማምለክና የክርስቶስን ቃል ማጥናት አይሆንልንም፡፡ የቤርያ ክርስቲያኖች
እጅግ ክፉዎች ከሆኑት ከተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ተሽለው የተገኙት የእግዚአብሔርን ቃል በልበ ሰፊነት በማጥናታቸውና ቃሉንም ለመቀበል
የተገባ ልብ ስለነበራቸው ነው፡፡(ሐዋ.17፥10)
አማኝ ከምንም ጉዳይ በበለጠ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የበረታ መንፈሳዊ
ጉልበትና ብርታት ሊኖረው ይገባል፡፡ በተለይም “በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችን ለመነጋገርና ፤ ለጌታ በልባችን
ተቀኝተን ለመዘመር” (ኤፌ.5፥19) የእግዚአብሔር ቃል ሙላት ሊኖረን ይገባናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ መዝሙር ፣ ዝማሬና መንፈሳዊ ቅኔ
ብሎ የጠቀሳቸው ሃሳቦች በየራቸው ጥልቅ የሆነ ሃሳብ ቢኖራቸውም አንድ አማኝ ክርስቲያን ከሌሎች ጋር እርስ በእርስ እኒህን ማድረግ
እንዳለበትም ነው የሚያሳስበን፡፡
መዝሙር ፣ ዝማሬና መንፈሳዊ ቅኔ ዜማና ግጥም የመቻል ጉዳይ አይደለም፡፡
ዛሬ “ምድሪቱን ያጨናነቁት እልፍ ዘማርያን” ዜማና ግጥም እንጂ መዝሙር ፣ ዝማሬና መንፈሳዊ ቅኔ የሚችሉ አይደሉም፡፡ እኒህ ነገሮች
መሠረታቸው ፍጹም የሆነ የሆነ ቃለ እግዚአብሔር ትምህርትና ምክር ውጤት ነው፡፡ ቃሉ ዘር ነው (ማቴ.13፥23) ፤ ይህን የተዘራ
ዘር የሚያፈራ ልብ የሚሰማ ልብ ብቻ ሳይሆን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፡፡ በብዙዎች አማኞች መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው፡፡
ቃሉን መስማትና ቃሉን አስተውሎ መስማት፡፡ አስተውሎ ለመስማት የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልጋል ፤ ጌታ ካልረዳንና በጸሎት ካልተጋን
፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ካልተመላለስን በቀር እንደልድያ ልባችን
አይከፈትም (ሐዋ.16፥14-15) ፤ እንደተወደዱ ደቀ መዛሙርት አእምሮአችን አይከፈተልንም፡፡ (ሉቃ.24፥45) እኛ የዚህ ዘመን
ክርስቲያኖች የክርስቶስን ቃል የምንሰማ ብቻ ነንን ወይስ በማስተዋል የምንሰማ?!
መዝሙር ፣ ዝማሬና መንፈሳዊ ቅኔ ምንጩ የኮለለና የጠራ ድምጽ አይደለም
፤ ቃለ እግዚአብሔር እንጂ፡፡ ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር ቃለ እግዚብሔር ለማንበብና ለማጥናት
ያለው ልብ፥ ልል ልብ ነው፡፡ ይህ በሽታ አድጎ ዛሬ ብዙ ዘማርያን
በዜማ የሚያቀርቡት የተሸመደደ መዝሙራቸው ላይ እንጂ ቃሉን ማንበብና ቁጭ ብሎ ማጥናት ላይ በብዛት የሉም፡፡ እናታችን ድንግል ማርያም
ግን ከዚህ ትለያለች ፤ የዘመረችው ዝማሬ መሠረቱ ያማረ የቃል አወቃቀር ፣ የተዋበ ድምጽ አወጣጥ ፣ የተለየ የአሸባሸብ ስታይል
(style) ፣ የተሸመደደ ግጥምና ዜማ አይደለም፡፡ ዝማሬዋ ልብ የሚነካ ነገር አለው፡፡ እንኪያስ! እናታችን ናት ፤ እኛም ለእርሷ
ነን ብለን የምንሞግት ሰዎች ከዚህ ሕይወቷ ልንማረው የሚገባ ብዙ ትምህርት አለን፡፡
ድንግል ማርያም የዘመረችው መዝሙር ለመንፈሳዊነቱ ዓቢይ ማሳያ ምሳሌያችን
ነው፡፡ ድንቅ የሆነ የቃል ሙላት ፤ ድንቅ የሆነ ዝማሬ!!!
ጌታ ጸጋውን ያብዛልን፡፡አሜን፡፡
ይቀጥላል…
No comments:
Post a Comment