Tuesday 11 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ስትገለጥ(ክፍል - 2)



         ድንግል ማርያም የክርስቶስ የቃሉ ሙላት እንዳላት በታላቁ መጽሐፍ ከዘመረችው መዝሙር ዋቢ ብንጠቅስ ፥ ለምሳሌ ፦
  
       ነፍሴ ጌታዬን ታከብረዋለች ፤ (መዝ.34፥2 ፤ 44፥8 ፤ 103፥1-4) ድንግል ማርያም የወለደችውን ጌታ “ጌታዬ” ብላ ታከብረዋለች ፤ ታመልከዋለችም፡፡ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” እንዲል ፤ እርሷ ፈጣሪዋን ታከብረዋለች ፤ በፍርሃት ታመልከዋለችውም፡፡
       መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች ፤ ( መዝ.18፥46 ፤ 42፥11 ፤ 43፥5 ፤ 69፥32 ፤ 107፥42 ፤ 119፥74 ፤ ኢሳ.45፥15-17 ፤ 45፥21 ፤ 61፥10 ፤ ኤር.9፥24 ፤ ሆሴ.13፥4 ፤ ዕን.3፥18 ፤ 1ጢሞ.2፥3 ፤ 4፥10) የወለደችውን ያንኑ ጌታዋን “መድኃኒቴ” ብላም ትጠራዋለች፡፡ መድኃኒቱ ለእርሷም ፤ ለእኛም ፤ ለአለሙ ሁሉ ነውና፡፡

       የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። (ሉቃ.1፥38 ፤ መዝ.34፥22 ፤ 40፥4 ፤ 112፥6-8 ፤ 138፥6 ፤ ማቴ.23፥12)
       እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል ፤ (ሉቃ.1፥45 ፤ 11፥27)
       ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና ፤ ( መዝ.71፥19 ፤ 125፥3)
       ስሙም ቅዱስ ነው ፤ ( ዘሌዋ.11፥44-45 ፤ 19፥2 ፤ ኢያ.24፥19 ፤ 1ሳሙ.2፥2 ፤ 1ዜና.29፥16 ፤ ነህ.9፥5 ፤ መዝ.8፥1 ፤ 9 ፤ መዝ.99፥3 ፤ ኢሳ.57፥15 ፤ ኤር.32፥18)
       ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል ፤ ( ዘጸ.20፥6 ፤ መዝ.102፥17 ፤ 130፥7)
       በክንዱ ኃይል አድርጎአል ፤ (ዘፍጥ.11፥8 ፤ መዝ.98፥1 ፤ ኢሳ.40፥10)
       ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል ፤ (ዘጸ.18፥11 ፤ 2ሳሙ.22፥28 ፤ ምሳ.11፥2 ፤ 16፥18 ፤ ሕዝ.7፥24 ፤ 30፥6 ፤ 18 ፤ 32፥12 ፤ 33፥28 ፤ አሞ.6፥8 ፤ ዘካ.9፥6 ፤ 10፥11)
       ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል ፤ ( 1ሳሙ.2፥7-8 ፤ መዝ.18፥27 ፤ ምሳ.3፥34 ፤ ኢሳ.57፥15 ፤ ሕዝ.21፥26 ፤ ማቴ.23፥12 ፤ ሉቃ.1፥52 ፤ 14፥11)
       የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል ፤ (መዝ.22፥26 ፤ 23፥1 ፤ 33፥10 ፤ 63፥5 ፤ 106፥9 ፤ 107፥9 ፤ኢሳ.58፥11 ፤ ኤር.31፥25)
       ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ ፤ (ዘፍጥ.49፥10 ፤ 1ዜና.16፥15 ፤ መዝ.48፥9)
       ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል ፤ (ዘፍጥ.17፥7 ፤ 19 ፤ መዝ.97፥3 ፤ 119፥9 ፤ ኢሳ.41፥8 ፤ ገላ.3፥16 ፤ ዕብ.1፥1) (የእኒህን ቃላት የእያንዳንዳቸውን ማብራርያ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡)

       እኒህንና ሌሎችንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና የድንግል ማርያምን ጸሎት ያየን እንደሆን ያለጥርጥር ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ቃል ሙላት እንዳላት እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ቃሉን የሚያነቡትንና የሚሰሙትን ፤ የሚጠብቁትንም (ራዕ.1፥3) ፣ የሚያስቡትን ፤ የሚያሰላስሉትን ፤ የሚያጉተመትሙትን (ኢያ.1፥7-8 ፤ መዝ.1፥2) ሞገስን ይሰጣቸዋል ፤ ደግሞም አይጥላቸውም ፤ ብጹአንም ብሎ ያመሰግናቸዋል፡፡ ስንቶቻችን እንሆን የዚህ ብጽዕና መንገድ ገብቶን ቃሉን በማንበብ የምንተጋ? “መጽሐፍ ቅዱስ ገና ሳነብ እንቅልፌ ይመጣል” የሚል ክርስቲያን ስንሰማ ስንቶቻንን እንሆን የማንደነግጠውና ግር የማይለን?
      ስለዚህም ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ የማግኘቷ ምስጢር ቅዱስ ቃሉን ማንበቧ ፣ የመስማቷ ፣ መጠበቋ ፣ ማሰቧ ፣ ማሰላሰሏ ፣ ማጉተምተሟ ነው፡፡ ለብዙዎቻችን እንዲህ ያለ ነገር ብዙ ጊዜ አይከናወንልንም፡፡ ለራሳችን ቃሉን ከማንበብ ፣ ከማጥናት ፣ ከማሰብ ፣ ከማሰላሰል ፣ ከማጉተምተም ይልቅ ሰፊ ዘመናችንን “የምናባክነው” የቃሉን ተናጋሪዎችና ሰባኪዎችን በማድነቅና በመከተል ነው፡፡ እንዲህ ስል ህብረት አያስፈልግም እያልኩ አይደለም ፤ ዳሩ እንደድንግል ማርያም ቃሉን በግል የማጥናት ልምምዳችንና በእግዚአብሔር ፊት የመቆየት አቅማችን አናሳ ነው ለማለት እንጂ፡፡ የበሰለ የጸሎት ሕይወት ፣ ልብን ማሳረፍ የሚችል የምክር ቃል ፣ ሞገስ ያለው የተግሳጽ ቃል ለማውጣትና ለመናገር ቃሉን ከማንበብና ከማጥናት ምንጭ ውስጥ ነው የሚፈልቀው፡፡
    ድንግል ማርያም ግን እንኳን በምቹ ጊዜ በክፉዎቹ ናዝሬታውያን መካከል የቃሉን ዕቃ ጦር ታጥቆ መኖር እንደሚቻል በሚገባ ታስተምረናለች፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ካላጠናን ለአዳዲስና ለእንግዳ ትምህርቶችና በአሮጊት ተረታ ተረቶች ተጠላለፈን መውደቃችን አይቀርም፡፡ “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” የሚለው ድፍረት የሚኖረን በቃሉ የበሰለና የጠራ አቋም ያለን እንደሆን ብቻ ነው፡፡ (2ጴጥ.1፥16)
   በዚህ በድንግል ማርያም የክርስቶስ ቃል ሙላቷ ውስጥ የምናነሳቸው ብዙ ቁም ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን ግን እንዲህ እናነሳለን፡፡
ይቀጥላል …


2 comments:

  1. Tebarek wendmachn

    ReplyDelete
  2. ድንግል ማርያም ግን እንኳን በምቹ ጊዜ በክፉዎቹ
    ናዝሬታውያን መካከል የቃሉን ዕቃ ጦር ታጥቆ መኖር
    እንደሚቻል በሚገባ ታስተምረናለች፡፡

    ReplyDelete