ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ከስድስት ቀን በፊት በጥንት ስሟ “ፓኒያስ” ፥ በአሁን ስሟ ደግሞ “በናያስ” በምትባለው ከገሊላ ባሕር በስተሰሜን ከሔርሞን
ተራራ ተዳፋት ሥር በነበረችው በፊልጶስ ቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡”
(ማቴ.16፥13) ንጹሐ ባሕርይው ጌታ፥ ደካሞችና ገና በእውቀት ያልጎለመሱትን ደቀ መዛሙርት “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡
እነርሱም የሰሙትን ሁሉ ሳያስቀሩ ነገሩት፡፡ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ
ነው” ብለው ተናገሩ፡፡ ሰዎች ስለጌታ የሰጡት ስያሜ፥ ቀርበውት ያዩት ወይም ከእርሱ የሰሙት አይደለም፡፡ የየራሳቸውንና ከሌሎች
ጋር ሲያወሩት የደረሱበት “እምነታቸውን” እንጂ፡፡
ሰዎች ስለእኛ የሚሉት አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር አላቸው
፤ የሚሉት ነገርም ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና ያለውም ፤ የሌለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ስለጌታ የተናገሩት ከእርሱ ጋር ምንም
ዝምድና የሌለውን ነው፡፡ እኛም በተለይ ከታወቀ ነውርና ከኃጢአት ሕይወት ነጽተን በእውነተኛው በጌታ ወንጌል አገልግሎት ውስጥ ስንመላለስና
ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ ቅንአት ስናገለግል ብዙ ጊዜ የምንባለው፥ ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና የሌለው ነገር እንደሆነ ከዚሁ ለጌታ
ከተነገረውና ከደቀ መዛሙርቱ ሕይወት እንማራለን፡፡ (ማቴ.9፥34 ፤ 12፥24 ፤ ሐዋ.21፥37-38 ፤ 24፥5-6) ስለዚህ ብዙ
መባላችን ፤ ተብሎም በድርጊት ቢገለጥ ምንም ሊያስደንቀን ፤ ሊያስበረግገንም አይገባም፡፡ (1ጴጥ.4፥12)
ጌታችን ሁሉንም ነገር ከደቀ መዛሙርቱ ካደመጠ በኋላ ጥያቄውን፥ “እናንተስ
እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” በማለት የጥያቄውን አቅጣጫ ወደእነርሱ ቀየረው፡፡ በአገልግሎት አለም ከብዙ አማኞችና አገልጋዮች
ሕይወት የራቀው ጥያቄ ቢኖር ይህ ጥያቄ ነው፡፡ በዙርያችንም ያሉ ይሁኑ ከአጠገባችን ያሉ ምን እንደሚሉን በትክክል አለመረዳት ብዙ
ጊዜ የንስሐ በራችንን እንኳ ሲዘጋብን ከማስተዋል እንዘነጋለን፡፡ አንድ አገልጋይ ወይም አማኝ የእግዚአብሔር ቤት እውነተኛ አገልጋዮችና
አማኞች ለእርሱ ያላቸውን ነገር በሚገባ ማጤን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ስል አገልግሎቱን ሁሉ በጌታ ከመደገፍ ይልቅ በእነርሱ
ቅኝት ሊመራ ይገባዋል እያልኩ አይደለም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ “ኤጲስ ቆጶስ … በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው
ይገባዋል። … ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ።” (1ጢሞ.3፥2
፤ 7 ፤ 12) ሲል ኤጲስ ቆጶስም ሆነ ዲያቆን ከመሾሙ በፊት ልክ ለአገልግሎቱ ቅድስና እግዚአብሔር
እንደተጠነቀቀው ሁሉ፥ ለኤጲስ ቆጶሱም ፤ ለዲያቆኑም ምስክርነትን የሚሰጡ ሰዎች እንዳሉ ከማሳየቱም ባሻገር ፤ እኒህ ምስክርነት
የሚሰጡትም አማኞች እግዚአብሔርን የሚፈሩና ሰውን የሚያከብሩ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ማስተዋል እንችላለን፡፡ ዛሬ አገልግሎታችንና ቅድስናው
ወደቁልቁለት ለመውደቅ የተንደረደረብን የአደራው ተረካቢዎችም ሆኑ “ምስክርነት ሰጪዎቹ” በተለያየ የጉቦና የዘረኝነት ወጥመድ ውስጥ
ስላሉ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን ለመንግሥቱም ፤ ለባልንጀራችንም ከረብ በራቀ ህሊና እንድንመሰክር ይሻል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የሰውን ብቻ ተጠይቀው የቀሩ አይደለም ፤ እነርሱም ምን
ሊሉ እንዳላቸው ጌታችን ጠየቃቸው፡፡ አንድ ቀን ወዳጅነትን በተመለከተ መፈተናችን አይቀርም ፤ ወዳጅነት በመከራ ዘመን ብቻ በድርጊት
አይፈተንም ፤ ምን ያህል የልብ ቅንነትና ከሐሜት የጸዳ ፍቅር እንዳለን በሰላሙ ዘመንም እንፈተናለን፡፡ የመከራው ዘመን ይቆየንና፥
ስንቶቻችን እንሆን ወዳጃችንን ከልብ እጅግ እንደራሳችን የምንወድድ? በእውኑ ባልንጀራችንን ከእርሱ ጋር ባልሆን ጊዜ ያው አብረን
ስንሆን የምናወራውን ነው የምናወራለት? ደግሞስ ስንቶቻችን ነን ከውዳሴ ከንቱ በራቀ አንደበትና መንፈስ የባልንጀራችንን ትክክለኛ
ማንነቱን የምናደንቅለት? የምንወድለትስ? በእውኑ ለመልካም ባልንጀሮቻችን መልካም ምስክርነት አለንን? መልካሙ ምስክርነታችን ከአገር
ልጅነት ፣ ከአገልግሎት የሥልጣን ተዋረድ ፣ ከዘረኝነት ፣ በመተዋወቅ ከመሥራትና ከመናገር ፣ ከሃይማኖተኝነት መንፈስ ፣ ከንቀትና
ከጥላቻ የጸዳና በቃሉ እውነትነት ላይ የተመሰረተ ነውን? ይህንን ለመረዳት ዙርያ ገባችንን ማየት እንጂ ምንም ጥናታዊ ጽሁፍ አያስፈልገንም፡፡
በስህተት ተዘፍቆ ነገር ግን “የክህነት ሥልጣንና ሰባኪ አገልጋይ” ስለሆነ ብቻ ደግፈን፥ አማኙን የምናሳድድ ስንትና ስንት እንሆን?
በሌብነቱ ፣ በፍርድ አጉዳይነቱ ፣ በጉበኝነቱ ፣ በዝሙቱና በግብረ ሰዶማዊቱ ንስሐ እንዲገባ ሲመከር ፣ ሲዘከር ፣ ሲገሰጽ ፣ ሲቆጡት
… ምን አገባችሁ? እያሉ ሌላውን ግን ድንጋይ ለመጫን የእጃቸው ድንጋይ አልበቃ ብሎ በኪሳቸው ይዘው የሚዞሩትን ቤት ይቁጠራቸው!
አዎን! ስንቶቻችን ለቅዱስ ቃሉና ለእግዚአብሔር ብቻ የምናደላ ነን?
ከሰጠው ምስክርነት የተነሳ፥ በግሪኩ “ፔትሮስ” “ትንሹ ዐለት” ወይም
“ፔትራ” “ትልቅ ዐለት” የተባለው ስምዖን ጴጥሮስ፥ ደቀ መዛሙርቱን ወክሎ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።”
(ማቴ.16፥16) ቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን ዐለት፥ ማለትም ስለጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስነት በትክክል ተናገረ፡፡
ቤተ ክርስቲያን የቆመችበት መሠረት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው የሚል ነውና፥ ሐዋርያው ይህን እውነት ከሥጋና ከደም ያይደለ ከሰማይ
አባት ተገልጦለት መሰከረ፡፡ ከዚህ እውነት የሚበልጥ እውነት እንደሌለ ስንቶቻችን አምነን እየመሰከርን ነው?
ጌታችን የጴጥሮስን ምሰክርነት ከሰማ በኋላ አመሰገነው ፤ አደራም ሰጠው፡፡
እውነት ለሚናገሩ ሰዎች ተገቢውን ክብር አለመስጠት እውነትን የመቃወም ያህል እኩል ነው፡፡ ጌታ የደቀ መዛሙርቱን መሰደድ ፣ መጠላት
፣ መገፋት ፣ መናቅ ፣ መታሰር ፣ መንገላታት ፣ መገደል … በእርሱ ላይ እንደተደረገ ያህል ቆጥሮ ተቆጥቷል፡፡ (ዮሐ.15፥18
፤ ሐዋ.9፥5 ፤ 1ዮሐ.3፥13)
ከዚህ በኋላ ጌታችን የመጣበትን ዋናውን አላማውን ሞቱንና ትንሳኤውን በግልጥ
መናገር ጀመረ፡፡ እውነተኛ አገልጋይ የመጀመርያው መነሻው ፤ የመጨረሻውም ፍጻሜ በትክክል ይታወቃል፡፡ ጌታችን አገልጋይም ሆኖ ለእኛ
ተገልጧልና የመጨረሻ አላማው ምን እንደሆነ በትክክል ተናግሯል፡፡
ሁልጊዜ በጣም የሚያስጨንቀኝ ነገር ቢኖር፥ የዛሬ ዘመን ብዙ አገልጋዮችን
ሳስብ ነው ፤ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ነገሯ ክንፏ ታድሶ በደንብ መብረር እንዲቻላት እጅግ በጣም ሲናገሩ እሰማለሁ ፤ ግን ከየት
ወዴት እንደምታድግ ጥርት ፤ ግልጥ ያለ ነገራቸው አይታየኝም፡፡ ሁሉም ነገር ድንግዝግዝ ነው፡፡ በልማቷ ፤ በመንፈሳዊ ሕይወቷ ፤
በቀኖናዎቿ ፤ በልጆቿ አያያዝ ፤ በአዋልድ መጻሕፍቷ ዙርያ ባሉ ነገሮች ፤ በአስተምህሮዋ ፤ በአስተዳደር ሥራዎቿና መሪዎቿ ወዘተርፈ
… ያሉትን ችግሮች የሚያነሱ ብዙ ሰዎች እንዴት ይስተካከል? ሲባሉ የጠራ ነገር የላቸውም፡፡ ለዚህም ይመስላል፥ እኒህ ወንድሞች
ጨክነው ለበጎ ነገር ስላልተጉ በዚህ መሃል የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ገብተው ሕዝቡን ሥጋዊ ሃብቱን ከበዘበዙ ፤ የገዛ ሥጋውን
በዝሙት ካረከሱበት ፤ ለሥጋቸው መጠቀሚያ ካደረጉ በኋላ ወደሞት ሲነዱት የምናየው፡፡ አዎ! የተውሸለሸለ ሳይሆን እንደደቀ መዛሙርቱ
በግልጥ ደፍረን የምንናገረው መሲሐዊ ቅዱስ ራዕይ ይኑረን ፤ እርሱንም ባለማፈር ደፍረን እንናገረው!!! (ሐዋ.4፥13 ፤ 31 ፤
26፥26 ፤ ሮሜ.6፥20 ፤ 2ጢሞ.1፥12 ፤ ዕብ.13፥6)
ይህን ጥያቄ ደቀ መዛሙርቱን ከጠየቀና የሞቱንና የትንሳኤውን ነገር ከተናገረ
ከስድስት ቀን በኋላ፥ ጌታችን የሰጡትን ምስክርነት ሊያስረግጥላቸውና ሞቱን ሰምተው በልባቸው እንዳይታወኩ ፤ ባመኑትም ነገር ፈጽመው
በማመን እንዳይፈሩም ሊያደርጋቸው ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን መርጦ፥ ከፊልጶስ ቂሣርያ አቅራቢያ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ በልማድ የታቦር
ተራራ እየተባለ በሚጠራው የአርሞንዔም ተራራ ላይ በመውጣት፦ “በፊታቸውም
ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።” (ማቴ.17፥2)
ጌታችን በፊታቸው ተለወጠ ፤ መለኮታዊ ክብሩንም አይተው ፍጹም አመኑ፡፡
ሰዎች እንዳሉት ሳይሆን እርሱ እንደተናገረው ክርስቶስ መሆኑን ገለጠላቸው፡፡ ይህ ክብሩ በዳግም መምጣቱ ሲመጣ እንደሚገለጠው ያለ
ክብር ነው ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ልጅ ፤ ክርስቶስ ሆኖ የተገለጠው መገለጥ ነው፡፡ ማንኛው አገልጋይ ይሆን ኢየሱስን በክርስቶስነት
ክብሩ አይቶ እየሰበከ ፤ እየመሠከረ ያለው? አገልጋዩና አማኙ ሆይ! ለዚህ እውነት እንጂ ለሌላ እንዳትታዘዝ ፤ ሌላም ስብከት እንደሌለህ
ቃሉ ይላልና፥ በእውኑ ለዚህ እውነት ብቻ ታምነህ እያገለገልህ ነውን!? (1ቆሮ.1፥23 ፤ 2፥2 ፤ ገላ.3፥1 ፤ 4፥19)
የእውነተኛ ምስክርነት መሠረቱ እውነትን ማየት ወይም በትክክል መረዳት
ነው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ምስክርነታቸው በድፍረት የተመላውና በእውነት ላይ ምንም ላይጨምሩ የጨከኑት ይህን ብርሃናዊ የመለኮት ክብር
በማየታቸው ነው፡፡ ሐዋርያው “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን
ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” (2ጴጥ.1፥16) ደቀ መዛሙርቱ ላዩት ለዚያ እውነት ብቻ ታመኑ እንጂ ሌላ ለምንም ነገር አላደሉም፡፡
የበዓሉ መታሰቢያ
እንዲህ ባለ ምስክርነት እንድንኖር ይመክረናል!! ተዘጋጅተናልን?
አቤቱ ጌታ ክርስቶስ
ኢየሱስ ሆይ! የባርያዎችህን አይን በብርሃንህ አብራልን፡፡ አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment