እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፡፡
አሜን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሚለውን ቃል፥ አንድ ረዥም ጊዜን (ገላ.4፥4)
፣ የአንድ ወቅት አገዛዝን (ማቴ.2፥1-2 ፤ ሐዋ.12፥1) ፣ አንዳንዴ ሰዓት በሚለው አገላለጥ አምልኮን ወይም የመዳንን ጊዜ
(ማር.1፥15 ፤ 2ቆሮ.6፥2 ፤ኤፌ.2፥6 ፤ 2ጢሞ.1፥9) ፣ ሌላም ተግባር የተከናወነበትን ወይም የሚከናወንበትን ጊዜ (1ጢሞ.4፥1-2
፤ 1ጴጥ.1፥5-6) ፣ ውስን ጊዜንና (መዝ.102፥24) የመሲህ ኢየሱስ በምድር የነበረበትን ጊዜና (1ጢሞ.2፥6 ፤ ዕብ.1፥1)
ሌሎችንም ለማመልከት ቃሉን ይጠቀምበታል፡፡ ስለዚህ ዘመን የሚለውን
ቃል እንደሚገኝበት አውዱ፥ በጥንቃቄ ልናየውና ልንተረጎመው ይገባናል ማለት ነው፡፡
ጊዜያትን የፈጠረ፥ “የዘመኑ ቍጥር የማይመረመር” (ኢዮ.36፥26) ፣
“ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ … አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም
ከቶ አያልቁም።”(መዝ.90፥2 ፤ 102፥27) የተባለለት ቅዱስ እግዚአብሔር
ነው፡፡ (ዘፍጥ.1፥5 ፤ መዝ.102፥24) ስለዚህም ዘመን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች በስጦታነት ተሰፍሮ ፤ እንኖርበት ዘንድ የተሰጠን
በረከት ነው፡፡ ( ዘፍጥ.6፥3 ፤ ኢዮ.14፥5 ፤ 21፥21 ፤ 31፥15 ፤ 39፥4-5 ፤ 139፥16 ፤ ሐዋ.17፥26) የዘመናችን
መርሑም አንዱ ሲያልፍ ሌላው እንዲተካ “በብዙ ተባዙ” (ዘፍጥ.1፥28 ፤ 9፥1) ፤ በማለፍ ሕግ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ (መዝ.103፥15)
ዘመናት የእግዚአብሔር ሥራዎችና ሥጦታዎች ከሆኑ ከእርሱ ተባርከው ሊሰጡን
፤ እኛም ከእርሱ እጅ አስባርከን መቀበል ይገባናል ማለት ነው፡፡ በዘመኑና በዕድሜው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር መንገዱን ያደረገ ፤
ሕጉን የማይረሳና ትዕዛዛቱንም የሚጠብቅ ሰውና ሕዝብ፥ ዘመኑን ሙሉ በሰላም ያርፋል ፤ እንደዛፍ ረጅም ዕድሜንም በደስታ ፍጹም ይጠግባል፡፡
(መሳ.8፥28 ፤ መዝ.91፥16 ፤ ምሳ.3፥2 ፤ ኢሳ.65፥22) እግዚአብሔርን መፍራት ዘመንን ካረዘመና የሕይወትን ዕድሜ ከጨመረ
(ምሳ.9፥11 ፤ 10፥27)፥ እግዚአብሔርን አለመፍራት ደግሞ ፈጽሞ ዕድሜን ያሳጥራል ማለት ነው፡፡
ከአስርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ፥ “አባትህንና እናትህን አክብር
፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።” (ዘጸ.20፥12) በማለት ከሌሎቹ ትዕዛዛት በተለየ አቀማመጥ፥ ሕጉን
በመጠበቅ የሚገኘውንም በረከት አብሮ ያስቀምጣል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም
አባትህንና እናትህን አክብር ፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” በማለት የተስፋ ቃል ያላትን ሕግ በማስታወስ
ይመክራል፡፡ (ኤፌ.6፥1) አንድ ልጅ አባቱንና እናቱን ሲያከብር ለክርስቶስ ማድረግ የሚገባውን በማድረጉ ምክንያት ፍጹም በረከትን
ይባረካል ማለት ነው፡፡
የእግዚአብሔር ቅዱሳን ዘመናቸውን ለእግዚአብሔር በመስጠት ይታወቃሉ ፤
ይህም ማለት ዘመናቸውን ለእግዚአብሔር ብቻ ይቀድሳሉ፡፡ ቅዱስ ዳዊት ብዙ ኃጢአትና በደል የሠራ ቢሆንም እንኳ ፥ ፈጣሪውን ልብን
ደስ በሚያሰኝ ንስሐ ደስ በማሰኘቱና በማገልገሉ ምክንያት “ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ
… ” (ሐዋ.13፥36) ተብሎ ተነግሮለታል፡፡ በትዳራችን ፣ በሥልጣናችን ፣ በንግዳችን ፣ በሥራ ገበታችን ፣ በሕጻንነት ፣ በወጣትነትና
በሽምግልናችን ዘመን ሁሉ ሊከብር የሚገባው ጌታ ብቻ ሊሆን ይገባዋል፡፡
ዘመናችን በእውነት ለእርሱ ፤ ከእርሱ የተሰጠን ከሆነ በዕድሜያችን
ጌታ ትልቁን ሥፍራ ሊይዝ ይገባዋል፡፡ ታሪክ እንደሚነግረን ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ በነበረችባቸው ዘመናት ዓለሙ
ሁሉ የእርሷ ጠላት ነበር ፤ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በእውነት ላይ አንዳች ጨምራ ወደኋላ ከማለት ይልቅ፥ ለእውነት ስትል በተቀበለችው
መከራ የነገሥታቱ ክንድ ዛለ እንጂ የሰማዕታቱ አንገት ፍሬ ከማፍራት ወደኋላ አላለም፡፡ ዘመን ተቀይሮ ቤተ ክርስቲያን ከነገሥታት
ጋር ተመቻምቻ ፤ በሽርክና ሥራ መሥራት ስትጀምር ግን፥ ያ ውብ መልክና ደምግባት ከመደብዘዝ አልፎ መዘባበቻ ሆነ፡፡
እግዚአብሔር ብቻ ፤ ሙሽራው ኢየሱስ ብቻ ፤ አጽናኙ መንፈስ ፤ መንፈስ
ቅዱስ፥ አንድ አምላክ ብቻ እንዲሰለጥንባት ዋጋ ተከፍሎላት ሳለ እርሷ ግን ከነገሥታት ጋር አዲስ ፍቅርና ጋብቻ በመመስረቷ ምክንያት
በትምህርታቸው ጆሮ ጭው የሚያደርጉ መናፍቃን ድንገት ዙርያዋን ከበቡ ፤ ልጆቿን ተናጠቁ ፤ የአንድነት ቅጥሯን አፈረሱ ፤ የጳጳሳቶቿን
ልብ ከሁለት ከፍለው አመነፈቁ ፤ “ከክርስቶስ ጋር ከምንጣላ ሞትን እንመርጣለን” እንዳላሉ፥ ዛሬ ግን በግን ለአራጁ እየሰጡ እነርሱ
በጓሮ በር የሚደራደሩ ፤ የሚቆምሩ ሆኑ፡፡
እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር በነበሩበት ዘመናቸው ጠላቶቻቸው ፈጽመው
አይችሏቸውም ነበር ፤ ከእግዚአብሔር በተለዩበት ዘመናቸው ግን፥ “የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ ፤ እግዚአብሔርም
በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ
ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ።” (መሳ.6፥1-2) ይለናል ፤ ዘመናቸውን ለእግዚአብሔር ባልሰጡበት ወራት እንደአውሬና እንደአዕዋፍ
በጉድጓድ በዋሻና በተራራ እየተሸሎከለኩ ኖሩ፡፡
ቤተ ክርስቲያንም ከእግዚአብሔር ጋር በነበረችባቸው ወራት ካታኮንቡ
(ግበበ ምድሩ) የእልልታ ሥፍራ ፣ ምድረ በዳው ደግሞ የዝማሬ መቅደስ ነበር ፤ ከእግዚአብሔር ተለይታ ዘመኗን ከመሳፍንትና መኳንንት
፤ ከነገሥታት ጋር ባደረገች ጊዜ ግን በክርስቶስ ላይ ስታመነዝር ተገኘች፡፡ ስለዚህም ሞገስዋንና መፈሪያዋን ተቀምታለችና ፥ እንደቤተ
እስራኤል ለክርስቶስ ያላደሩ ነገሥታት ቀኖና ሲቀንኑላት ፤ ዶግማ ሲያቁሙላት ዝም ብላ በመቀበል ታሪክ ታዘባት ፤ ጌታም አዘነባት፡፡
ወንጌል የጨበጡት
ልጆቿ፥ በጳጳሳቶቿ እስከመገደልና መታረድ የደረሱት ጋብቻዋን ከአለማውያንና ፖለቲከኛ መሪዎች ጋር በማድረጓ ነበር፡፡ የዛሬዋስ ቤተ
ክርስቲያን የት ይሆን ያለችው? ለክርስቶስ እንድትኖርበት በተሰጣት ዕድሜና ዘመኗ ላይ እያዘዙት ያሉት እነማን ይሆኑ? በእውኑ ከዘፋኝነቱ
ያልተመለሰውና በንስሐ መንገዱን ያላጠራው ዘፋኝ ከአውደ ምህረቱ ምንድር ነው የሚሠራው? ሁለት ሚስት ያለውና በሃብቱ የሚመካው የሰበካ
መንፈሳዊው ጉባኤ መሪ ምን እያደረገ ነው? ግብረ ሰዶማዊው ሰባኪና ዘማሪ ምን ይሆን ከመካከሏ እየሠሩ ያሉት? በአለማዊው ሥልጣናቸው
የብዙ ነፍሳትን ሕይወት የቀጠፉ መሪዎች በሲኖዶሱና በየጉባኤዋ ምን እየሠሩ ይሆን? ሚዛን የሚያምታቱ የሚሰልቡ አስነዋሪ ነጋዴዎች
ከጉያዋ ምንድር ነው የሚያደርጉት? አስማተኞች ፣ ድግምተኞች ፣ ምዋርተኞች ፣ ጠንቋዮች ፣ ሞራ ገላጭ ቄስና መነኮሳቶቿ ከቅኔ ማህሌቷና
ቅድስተ ቅዱሳንዋ ምን ይሠራሉ ?
በእውኑ በቤተ ክርስቲያን ዛሬ እያዘዘ ያለው ማን ነው? ዘመኗን እንዴት
ይሆን እያገለገለችበት ያለው? በእውኑ እኛ ወጣቶችስ ዘመናችን የመባረኩ ምስጢር እናትና አባትን ማክበር መሆኑን ተረድተናልን? በድኃ
ወላጁ የማያፍር ልጅ ማን ነው? በእውኑ ለቤተሰብ የሚሰማን ስሜት ከእኩያ ፍቅር ያለፈ ነውን? ዘመን ለመለወጥ ዕድል ነው ፤ እግዚአብሔር
ዘመንን የሚጨምርልን ፊቱን እንድንፈልግ ነው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ዘመን ጨምሮልን ዝም አይልም ፤ ፍሬ ፍለጋ ይመጣል፡፡ በዘመናችን
እርሱን በማክበርና በመፍራት ፤ ለእናትና አባቶቻችን በመታዘዝ አልሾምንበት እንደሆን “ … ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም
አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች?” (ሉቃ.13፥7) የሚል ጽኑ የወቀሳ ፍርድ ያገኘናልና፥ ዘመናችን እንዲባረክ
በዘመናችን ጌታችንን እንሹመው!!!
ጌታ ኢየሱስ ጸጋውን ያብዛልን፡፡
አሜን፡፡
ቃልህይወት ያስማልን፡፡ ዘመናችን ንስሀ የምንገባበት፣ ስጋ ወደሙ የምንቀበልበት፣ ከኑፋቄ የምንወጣበት፣ የተቸገሩትን የምንረዳበት፣ … የተባረከ ዓመት ያድርግልን
ReplyDelete