Tuesday, 2 December 2014

የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮች(ክፍል - ሦስት)



5. የሚነሱት ከመካከላችን ነው፡፡
     እውነተኛውና ለእግዚአብሔር የጨከነ አገልጋይ ሲጠፋ ክፉው አገልጋይ ከውጪ ወደውስጥ ወይም በብዛት ከመንጋው መካከል ይነሳል፡፡ ከመካከል የሚነሱ የሐሰት መምህራን በዋናነት የመሳታቸውና የማሳታቸው ምክንያት ከመሠረተ እምነት ትምህርት ጉድለት ነው፡፡ ገበሬ እርሻውን አለስልሶ ከዘራ በኋላ በየጊዜው መከታተል ይገባዋል፡፡ የሚከታተለው አለስልሶ የዘራው እርሻ የማይበቃ ሆኖ ሳይሆን አረምና እንክርዳድ ዋናውን ዘር እንዳይውጠው ነው፡፡ አረምና እንክርዳድ ገበሬው የዘራው አይደልም፤ እርሱ ያልዘራው ከመካከል የበቀለው አረም ግን የዘራውና ዋና ዘር ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ስለዚህ በየጊዜው  ሊያርም ፤ ሊኰተኩተው ይገባዋል፡፡ በመንፈሳዊ አለም ደግሞ መልካሙ ገበሬ እግዚአብሔር ዘርን ከዘራ በኋላ መጥቶ ክፉን ዘር የሚዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፡፡ (ማቴ.13፥28) ስለዚህ ልንተጋ ቃሉን በማጥናት ልንበረታ ይገባናል፡፡

    ስለሐሰተኞች መምህራን ቅዱስ ጴጥሮስ “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ … ” (2ጴጥ.2፥12) በማለት ባህርያቸውን በግልጥ አስቀምጦታል፡፡ “መናፍቃን” ብለን የምንጠራቸውን ከሩቅ ስንጠብቅ በመካከላችን ፈክተው አፍርተዋል፡፡ በዋናነትም የሚታወቁት “የዋጃቸውን ጌታ በመካድ” ነው፡፡ ዳሩ ከፍሬያቸው በታወቁ ጊዜ (ማቴ.7፥20) ከጥንቱም ከእኛ ጋር ስላልነበሩ ፤ ከእኛ ጋር አይጸኑምና ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገልጥ ዘንድ በፍጻሜው ከእኛው መካከል ተለይተው ይወጣሉ፡፡ (1ዮሐ.2፥19)
  የሐሰት መምህራን ብዙ ጊዜ እውነተኛ አገልጋዮች ተላላ በሆኑበት ወራትና ዝንጉ በሆኑበት በዚያው መንጋ ውስጥ ይገለጣሉ፡፡
ከእውነተኛ መምህራን ምን ይጠበቃል?
1.    በደሙ የተዋጀችውን ቤተ ክርስቲያን ሊጠብቁ ይገባል፡፡
መጠበቅ የእረኝነት ሥራ ነው፡፡ እረኛ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠባቂ መሆንን ያሳያል፡፡ ጌታ ሾሟቸው ያልታመኑትን እረኞች የሰጣቸውን ትልቁ ኃላፊነት ከእነርሱ ነጥቋል፡፡ (ኢሳ.56፥9-12 ፤ ሕዝ.34) ስለዚህም ነፍሱን ስለታመኑት በጐቹ የሚያኖር (ዮሐ.10፥11) የሚያሰማራ እውነተኛ አንድ እረኛ መሢሁን ሊሰጥ ኪዳን ገባ፡፡ (ሕዝ.34፥23)
   ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛና ብቸኛ የቤተ ክርስቲያን እረኛ ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን በደሙ ቅጥርን ቀጥሮላት ፤ በመንፈሱ ደግሞ ያረጋጋታል፡፡ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ዝምድና እንደበግና እንደእረኛ ነው ስንል እርሱ ያሰማራል፤ እርሱ ባሰማራባት ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን ልትኖር ፤ ልትሰማራም ይገባታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት የተሾሙት ለሥልጣን ሳይሆን ለመልካም የእግዚአብሔር ሥራ ነው፡፡(1ጢሞ.3፥1) ሥራውም ከክርስቶስ እንደተማሩት እንደእግዚአብሔር መጋቢ (ቲቶ.1፥7) ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ለመምከርና ተቃዋሚዎችንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ ነው፡፡(ቲቶ.1፥9)
   ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ማለት ህንጻውን ቀለም ከማስቀባት ፣ መጎናጸፊያና የውስጥ ንዋየ ቅድሳት ከማሟላት ፣ አጸዱን ዘበኛ ቀጥሮ ከማስጠበቅና ተክል ተክሎ ከማለምለም ፣ ልማት ከማስፋፋት እጅግ እጅግ በጣም ይለያል ፤ ይሰፋልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማለትም የአማኝ ምዕመንንና የምዕመናንን አንድነት መጠበቅ ማለት ጤናማ መንፈሳዊ ህይወት ይዘው በጌታ ፊት በቅድስና እንዲንጓደዱ ቃሉን ዕለት ዕለት መመገብ ፤ እንዲያፈሩም ደግሞ በጸሎት መርዳት ፤ ከርኩሰት እንዲርቁ በትጋት መከታተል ማለት ነው፡፡
     ዛሬ ላይ ባማረ ህንጻና በተንቆጠቆጠ በሰው እጅ በተሠራ ቤተ መቅደስ አድባራትና ገዳማት ውስጥ በብዛት ያሉት፥ በሥጋና በደም የወየበ ስብእና ያላቸው “አማኞች” ብቻ ሳይሆኑ “ከሰውነት ተራ”  የወረዱና እንደሚናደፍ እባብ የሚቻኮሉ ምዕመናንና አጋፋሪዎች ጭምር ነው፡፡ ያ ብቻም ሳይሆን ለህንጻው የሚጨነቁትን ያህል በመለኰታዊ ዕቅድ ወልድ የሞተለትን ህያውና የማይፈርስ መቅደስ ለሆነው ክርስቲያን አማኝ የሚደረገው እንክብካቤ የሕንጻው ያህል አለመሆኑ  መንፈሳዊ የሆነ ከባድ ክስረት እንደገጠመን ያሳየናል፡፡
    የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ በደሙ የዋጃት እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ተወካይ ጠባቂዎቹ ጳጳሳት የተጠሩት የእርሱን ፍለጋ በመከተል ሊጠብቁ እንጂ፤ እርሱ ያቀለለውን ሸክምና ያለዘበውን ቀንበር ለመጫን ለሥልጣን “የተሾሙ” አይደሉም፡፡ ጠባቂ ሰባራውን አቅፎ ደግፎ ይይዛል ፤ የተሰበረውን የበጉን አካል እንደሚገባም ያስራል፡፡ ሰባራውን እየተወ ደህነኛውን ብቻ የሚጠብቅ የበግ እረኛ እርሱ እውነተኛ የበግ እረኛ አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ የሚበዙቱ ካህናቶቻችን ወንጌል ለማስተማር ሳይሆን “ጠበል ለመርጨት” ሲሄዱ እንኳ እግራቸው የሚያዘወትረው “ቀን የሠበረው ድኃ ቤት” ሳይሆን “ወዳለው ባዕለጠጋ” ቤት ነው፡፡
     ለአንድ እረኛ ሁለት አይነት የበግ ሥምሪት የለውም፡፡ ለአንዲት ቤተ ክርስቲያንም ሁለት አይነት መልክ ያለው የበግ (የምዕመናን) እረኝነት ሊኖር አይገባም፡፡ የምናየው ግን በዘር ፣ በሀብት ፣ በዝና ፣ በሥልጣን … “ልዩ እንክብካቤ ዘወትር” የሚደረግላቸውና በዓመት አንዴ እንኳ የማይጎበኙ አማኞችን በአንድ ቤተ ክርስቲያን ማየት ከጀመርን ከርመናል፡፡ ይህ መንገድ ግን የጥፋት መንገድ ነው፡፡ “ለሰው ፊት ግን ብታደሉ ኃጢአትን ትሠራላችሁ፥ ሕግም እንደ ተላላፊዎች ይወቅሳችኋል።” (ያዕ.2፥9)
  ጌታ የክብሩን ወንጌል ብርሃን በልባችን ያብራ፡፡ አሜን፡፡
        ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment