Tuesday 9 December 2014

የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮች(ክፍል - አራት)




2. ለመንጋው ሁሉና ለራሱ ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡(ቁ.28)

    ቅዱስ ጳውሎስ ቅዱስ ጢሞቴዎስን “ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፥ በእነዚህም ጽና፤ ይህን ብታደርግ፥ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህና።” በማለት ይመክረዋል፡፡ በእርግጥ የሚያድን እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ አማኞች ወደጌታ በመምጣት ሕይወታቸው  ዕለት ዕለት በማደግ እግዚአብሔርን ወደመምሰል እንዲደርሱ አገልጋዮች ትልቁን ድርሻ አላቸውና፥ ለራሳቸውም፤ ለትምህርታቸውም ሊጠነቀቁ ይገባቸዋል፡፡ ጤናማውን ጉዞ እስከፍጻሜው ልንጓዝ የምንችለው ለትምህርታችንና ለምናስተምረው የእግዚአብሔር መንጋ መጠንቀቅ ስንችል ነው፡፡
    ጥቂት እርሾ ብዙውን ሊጥ እንደሚያቦካ (1ቆሮ.5፥16)፤ ጥቂት የተባለም ኃጢአት ወይም ክፉ ትምህርት ብዙውን መንጋ ከመበከል አይመለስም፡፡ እንደዋዛ የሚደረጉና የሚነገሩ ነገሮች በመንጋው ላይ ሊያሳርፉ የሚችሉት ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ትላንት እንደዋዛ ሲነገሩ የነበሩ ተረታ ተረቶች፥ ዛሬ ወደቤተ ክርስቲያን ሾልከው ገብተው ለብዙ ምዕመናን የሕይወት መመሪያ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡ በዚህ ሳያበቃ አሁንም ለመንጋው ባለመራራት የሚጻፉትና የሚሰበኩት ስብከቶች በቃሉ ሚዛንነት ልንፈትሻቸው፤ ቀለው ከተገኙ ልናስወግዳቸው ይገባናል፡፡

    የክርስቲያን ማህበረሰብ “ስለኃጢአቱ ነጻ ክፍያ በእግዚአብሔር አብ አንድያ ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ ለዘላለም ተመልሷል፤ በማመንና በቃሉም፤ በሕይወቱም በመመስከር ይህንን የዘላለም ሕይወት ይወርስ ዘንድ” ተጠርቶ ሳለ ሌላ የኃጢአት ማሥተስረያ መንገድ ማሳየትና ሰው በዚያ ጌታ ባላለው መንገድ እንዲቅበዘበዝ ማድረግ፥ ለመንጋው ሕይወትና መዳን አለመጠንቀቅ ነው፡፡ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ይህንን የመዳን ወንጌል በጩኸት በመመስከር ሰዎችን ቀጥታ ከመድኃኒታቸው እንዲገናኙ ሊተጋ ይገባዋል፡፡
   አማኝን እስከራስ (አማኝ አካል እንጂ ራስ መሆን አይቻለውምና) ድረስ የማድረስ ፈሪሳዊ አገልግሎት ጌታ ሲመጣ በፍርድ ያጠራዋል፡፡ ወደእግዚአብሔር መንግሥት አለመግባትም፤ የሚገቡትንም መከልከል ለራስም ለመንጋውም አለመጠንቀቅ ነውና ጌታ በወዮታ ያስጠነቅቃል፡፡(ሕዝ.34       ማቴ.23፥13) አገልጋይም አምኝም ከሆንን ከአፋችን ለሚወጣውም፤ ለምናደርገውም ልንጠነቀቅ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ደኅንነት አንድ ልጁን በቀራንዮ ላይ ሰውቶታል፡፡ አንድም በግ (አንድም አማኝ) እንዲሞትበት አይፈልግም፡፡(ሉቃ.15፥7) በእኛ ተላላነት ግን አንዲት ነፍስ ከፊቱ ብትጠፋና ብትሞት ጌታ የሟቹን ሞት አልፈቅድም ብቻ ያለ ሳይሆን ደሙንም ከእጅህ እፈልጋለሁ ይላል፡፡(ሕዝ.3፥18 ፤ 18፥23)

3. ሐሰተኛ መምህራን ሊነሱ እንደሚችሉ አውቆ ሊተጋ ይገባዋል፡፡(ቁ.30)
     ሐሰተኛ መምህራን እውነተኞቹ ሲሄዱ የሚገለጡ ናቸው፡፡ ይህ አድቢ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ እንደውሻ የጊዜና ያለመኖርን እግር ጠብቀው የሚገቡ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በድጋሚ “ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ።” (ፊል.3፥2) በማለት የሚመክረው፡፡ እውነተኛ አገልጋዮች ግን ጊዜ ጠባቂ አይደሉም፡፡ ማናቸውንም ሰዓት ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡
  ሐሰተኞች አድቢዎች ስለሆኑ ፊት ለፊት አይጋፈጡም፡፡ ትምህርታቸው በእውነት ፊት ዋጋ እንደሌለው ስለሚያውቁ ምቹ ምቹ ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡ እውነተኛ አገልጋይ ግን ሐሰተኞችን ፊት ለፊት ሲጋፈጥ ፤ እንዲሁም ከመካከል  ሊነሱ እንደሚችሉ አውቆ ተግቶ ሊሠራ ይገባዋል፡፡
     የሐሰት መምህራን ከመካከላችን ቢነሱ ልንደነቅ አይገባንም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከመካከል ሊነሱ እንደሚችሉ “አውቃለሁ” በማለት ተናግሯልና፡፡ መነሳት ብቻ ሳይሆን የተመረጡትንም ማሳት ይቻላቸዋል፡፡ (ማቴ.24፥24) ከታሪክ እንደምናስተውለው ቤተ ክርስቲያንን አላውያን ነገሥታት ካደረሱባት ጥፋት ይልቅ ግኖስቲካዊ አመለካከት ያላቸው መናፍቃን ያደረሱባት ጥፋት እጅጉን የከፋ ነው፡፡ እነዚህ መናፍቃን በሐዋርያትና በሐዋርያውያን አበው ዘመን የነበሩ ቢሆኑም በብዙ ትምህርቶቻቸው ስለተራቆተና ስለተመታ አቅማቸው እጅግ ደክሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ከመከራው አርፋ ፤ ተዘልላ ከነገሥታት ጋር በሽርክና ስትቀመጥ ድንገት እንደደራሽ ውኃ ቤተ ክርስቲያንን አጥለቅልቋታል፡፡
   በሐገራችን ተጨባጭ ታሪክም እንግዳ የሆኑ ትምህርቶችና ልዩ ልዩ ኑፋቄዎች የተከሰቱት ከውጪ ሳይሆን ከውስጥ መናፍቃን ነው፡፡ ቀላል የሚመስሉ ልምምዶች (ከጥንቁልናና ከአህዛብ ልምምዶች የተቀዱ ሳይቀሩ)   እንዴት አምልኮአችንን እንደወረሱ ሌላ ማስረጃ ማቅረብ አያሻም፡፡ ዮዲት ጉዲትና ግራኝ አህመድ ካደረሱብን ጥፋትና ውድመትም ይልቅ የእነዚህ መናፍቃን ደብተራዎችና ጠንቋይ አምላኪ ነገሥታት ያደረሱብን ጥፋት ተወዳዳሪ የላቸውም፡፡
   ትልቁ ስህተት ታሪክ አለመሥራት ብቻ ሳይሆን ከታሪክም አለመማር ነውና ቤተ ክርስቲያን ከመካከልዋ የሐሰት መምህራን ሊፈለፈሉ እንደሚችሉ አውቃ መትጋት ሲገባት በመዘናጋቷ ከመካከልዋ ለቁጥር የሚታክቱ መናፍቃን ተነስተዋል፡፡ መድኃኒት ባለበት ተሐዋስያን(ትንኞች) እንደማይኖሩ እውነተኛ ትምህርትና መምህራን ባሉበት የሐሰት መምህራን አይኖሩም ነበር፡፡
   ስለዚህ እውነተኛ መምህር፦ -  ይጋፈጣል፤
                                   - እውነትን ያስተምራል፤                   
                                - ደቀ መዛሙርትን ያፈራል፤
                               - ከመካከል የሐሰት መምህራን ሊነሱ እንደሚችሉ አውቆ ተግቶ ይሠራል፡፡
     ጌታ ከሰጠንም ማስጠንቀቂያ አንዱ እንዳያሳድዷችሁ ተጠንቀቁ ሳይሆን እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ በማለት ነው፡፡ (ማቴ.24፥4)
አቤቱ ሕዝብህን አድን፤ ማስተዋሉንም አብዛ፡፡ አሜን፡፡

ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment