“እኛ ኢትዮጲያውያን” የሚለው ሃሳብ “ደምና አጥንታችንን ገብረንላታል”
ለሚሉ አርበኞች ልብ የሚመላ ነገር አለው፤ በጥንት በሕገ ልቡና፣ ቀጥሎም በሕገ ኦሪት ከዚያም በክርስትና መኖሯን ለሚያምኑ ደፍረው
የሚሉት ነገር አላቸው ፤ በአክሱምና በዛጉዌ የታነጹትን ሐውልትና ህንጻ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚያደንቁ አርክቴክቸሮችና ሌሎች፥
እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ብዙ የሚተነትኑት ነገር አላቸው፤ ሁሉም በየሙያውና በያለበት ደረጃ ስለኢትዮጲያችን ቢጠየቅ የሚለው ብዙ
ብዙ አለው፡፡
ሃሳቤ ግን ወዲህ ነው፤ አጼ ቴዎድሮስ በጥር 22 በ1858 ዓ.ም ለእንግሊዛዊቷ
ንግሥት ለቪክቶሪያ በኢትዮጲያ ምድር ከታሠሩት የእንግሊዝ እስረኞች ጋር በተያያዘ፤ እንዲሁም ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሲያስቀምጡ፦ “የኢትዮጲያን ሰዎች ድንቁርነታችነን ዕውርነታችነን ሣይሰሙት አይቀሩም ያማረ
መስሎኝ ደፍሬ የላክሁብዎን ከፍቶብኝ (አጥፍቼ እንደሆነ) ቢገኝ ይምከሩኝ እንጂ አይክፉብኝ፡፡ እግዚአብሔር የመረጠዎ ንግሥት ዓይንዎ
የበራ ነውና፡፡”(ጳውሎስ ኞኞ ፤ ዐጤ ቴዎድሮስ
፤ ግንቦት 1985 ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ.214)
አሁንም በድጋሚ በሚያዝያ 10 ቀን 1858 ዓ.ም ለዚህችው ንግሥት ድጋሚ
በጻፉት ድብዳቤ እኛን ኢትዮጲያውያንን እንዲህ ገልጠዋል፦ “ የኢትዮጲያ ሰዎች እውር ነንና ዓይናችነን ያብሩልነ፡፡ እግዚአብሔር
በሰማይ ያብራልዎ፡፡” በማለትም በግልጥ አስቀምጠዋል፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ ፤ ዐጤ ቴዎድሮስ ፤ ግንቦት 1985 ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 233)
ለራሳም በሚያዝያ ወር 1859 ዓ.ም ላይም በጻፉት ደብዳቤም “ … ከንግሥቲቱ
ከወዳጄ ፣ ካንተ ከወንድሜ የምፈልገው ፍቅራችሁን ነው እንጂ ካብት(ሀብት) አልፈልግም፡፡ ካብት አለመፈለጌ ክብር(ባለጠጋ ሀብታም)
ሆኜ አይደለም፡፡ በጥበብ ዐይኔን ትከፍቱልኝ ብዬ ነው እንጂ፡፡”(ተክለ ጻድቅ መኲሪያ ፤ ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጲያ አንድነት ፤ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ፤ 1981 ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ.
280-281)
አጼ ቴዎድሮስ እንዲህ ለማለታቸው ከሚነሱት ምክንያቶች መካከል፦
·
ኢትዮጲያን ኃያል መንግሥት ለማድረግ በነበራቸው ዘመናዊ ዓላማ ቆርጠው ለመሥራት መነሳታቸው (ሐሪ አትክንስ ፤ የኢትዮጲያ ታሪክ ገጽ.25)
·
ለሥልጣኔ ባላቸው የመጓጓት መንፈስ ውስጥ ገብተው የክብራቸውና የመዋረዳቸው ነገር ፈጽሞ እያወካቸው፤
ወይም ሕዝባቸው በድንቁርና ውስጥ መገኘቱ እየነደዳቸው፤ (ተክለ ጻድቅ መኲሪያ ፤ ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጲያ አንድነት ፤ ኩራዝ አሳታሚ
ድርጅት ፤ 1981 ፤ አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጲያ ፤ገጽ. 281) ወይም ኢትዮጲያውያን በዘመኑ ከዓለም ሥልጣኔና ጥበብ ተለይተው ሳያዩም
ሳይሰሙም ይኖሩ ስለነበረ፥ በዓለም ያለውን ጥበብ በራስም አማካይነት በእንግሊዝ መንግሥት ረዳትነት ወደኢትዮጲያ ለማስጋባት አስበው
ይሆናል፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ ፤ ዐጤ ቴዎድሮስ ፤ ግንቦት
1985 ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ. 234) እኒህና ሌሎች ምክንያቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
የአጼ ቴዎድሮስን ሕይወት በምሳሌነት ያነሳሁት ከነበረውም፤ አሁን ካለውም
ትውልድ የተለየ ስብዕና ስላየሁባቸው ነው፡፡ “እኛ ኢትዮጲውያን” አጼ ቴዎድሮስን የምናውቀው በጀግንነት፤ በአትንኩኝ ባይነት፤ በትክክለኛ
አገር ወዳድነት … ብቻ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ባልተለየ መልኩ እጅጉን በብዙ ነገር ራሳቸውን አዋርደው ለገዛ ሕዛባቸው
ማደግና መለምለም ከውጪው ዓለም ጋር ይወያዩበት ፤ይጻጻፉበት የነበረው መንገድ አይቼ አሁን ያለውን ትውልድ በአብዛኛው “የፍህም
ልጅ ስለምን አመደ?” እንድል ያስገድደኛል፡፡
የሩቅና ባዕድ እምነት ያላቸው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ “እንግዶችን”
እጅ ዘርግተን ፤ ርስት ከፍለን ያስተናገድን “ልበ ሠፊ” ነን ፤ ነገር ግን እኛ በምድራችን ካሉ ሌሎች ለምሳሌ፦ በታሪክ ከካቶሊክ
እምነት ተከታዮች ጋር በአጼ ሱስንዮስ ዘመን አንዱ አንዱን መታገስና ማስታመም አቅቶት ንጉሱም ፤ ጳጳሱም ጎራ ለይተው ፤ አንጃ
መሥርተው በከማን አንሼ ጦር አደራጅተው ሲፋጁ ውለው ፤ ሲዋጉ ከርመው እኛው ኢትዮጲያውያን እኛው ኢትዮጲያውያንን አርደን ፎከርን
፤ ገድለን ሸለልን ፤ እሬሳ ከመቃብር አውጥተን አቃጥለን እንደጀብዱ ተኩራራን፡፡ ሌላው ለክርስቶስ በመመስከር ሳይሆን ተሸንፎ በመገደል
ለመውረስ ሲሯሯጥ አይተናል፡፡ (አባ ጎርጎርዮስ(ጳጳስ) ፤ የኢትዮጲያ
ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ህዳር 1986 ዓ.ም. ፤ አዲስ አበባ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.58-59)
ከዚህ ሳንማር ደግሞ፥ ኃይማኖት የለሽ ኮሚኒስቶች መጥተው “የክርስቲያን
ደሴት” የተባለችውን ምድር “እግዚአብሔር የለም” ብለው ሲሰብኳት አሜን ብለን ተቀበልን፤ እግዚአብሔር የለምን አሜን ያለው ትውልድ፥
እግዚአብሔር አለ የሚለውን ወገኑን አረደ ፤ ቀላ ፤ በጅምላ ረሸነ፤ በሌላው መልኩ ደግሞ ጨቅላ ህጻናቱን በየትምህርት ቤቱ እግዚአብሔር
የለምን ያስጠና ፤ ያስተምር ነበር፡፡
አጼው ግን “ከሰባክያን”ና በጊዜው ከነበሩት ሊቃናት እጅግ ተሽለው “እኛ
ከጥንት እንደአህያ ጡት ሁለት ነበርን” የሚለውን የተረት ድሪት በግልጽ ተቃርነው እንግሊዛዊቷ ንግሥት ቪክቶሪያን በወንድማማችና
እህትማማች ፍቅር(ሮሜ.12፥9) በበዛበት ስሜት በ1850 ዓ.ም “ … አሁንም እርስዎ የክርስቶስ ልጅ ነዎ ፤ እኔም የክርስቶስ
ልጅ ነኝ፡፡ ስለክርስቶስ ፍቅር ወዳጅነት ፈልጌያለሁ” በማለት ጽፈዋል፡፡ ድንቅ አጼ!!! (ተክለጻድቅ መኩሪያ ፤ አጼ ቴዎድሮስና
የኢትዮጰያ አንድነት፤ ገጽ.280) እኛ የምንበዛ ሃይማኖተኞች ኢትዮጲያውያን ግን ዛሬ “አማሌቃውያንን” የጥንት ወዳጅ ብለን በመጥራት
አብረን እየኖርን ምነው እንደንጉሣችን “ወንጌል ጨብጠን ወንጌል ከጨበጠው ጋር” በስምም መኖር አቃተን? ስለምንስ ይህን በመያዝ
የትልቅ ልዩነት ምንጭ እናደርጋለን? እኛ ኢትዮጲያውያን መች ነው ከአዎንታዊነት እንጂ ከአሉታዊነት ማየት መጀመር የምናቆመው?
…
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም
ኑሩ።”(ሮሜ.12፥18) በማለት የተናገረው ከሰው ጋር የመኖር ድርሻው
የእኛ እንጂ የሦስተኛ ወገን አለመሆኑን በማስገንዘብ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ለመውደድ እንጂ ጠላቱን እንኳ ለመጥላትና ለመናቅ
አቅም የለውምና፡፡ እንዲሁም በክርስትና ሕይወት ልናፈራ ከሚገባን ፍሬ አንዱ ማስተራረቅ ነው፡፡ ማስተራረቅ የብጽዕና አንዱ መንገድ
ከሆነ (ማቴ.5፥9) የተጣሉትን ሁሉ ልናስታርቅ ይገባናል ማለት ነው፡፡ ሰዎች ደግሞ የእኛን የዕርቅ ቃል ለመቀበል የሚወዱት፥ እኛ
ስንወዳቸውና ሰላማዊ ስምም ከእነርሱ ጋር ሲኖረን ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ ከሰዎች ሁሉ ጋር ከእነርሱ ምንም ሳይጎድል ወይም
ምንም ሳያጎድሉ በሰላም ሊኖሩ ይገባቸዋል፡፡
… እኛ ኢትዮጲያውያን ፋሺስት ኢጣልያን ሐገራችንን በእብሪተኝነት
ተነሳስቶ ሊወር ፤ ቅኝ ሊያደርግ፤ በባርያነት ሕዝቦቿን ሊገዛ ሲመጣ የጋራ ጠላታችን ነው ብለን በመነሳሳት፥ ከዳር እስከዳር ተጠራርተን፥
በአንድ መክተን የመለስን ነን፤ ለራሳችን ግን በጐሳ ፤ በወንዝ በድንበር ተከፋፍለን የምንበላላና የምንጠፋፋ ነን፡፡ ብዙ ጐረቤታሞች
ዛሬ ሆድና ጀርባ ነን ፤ ከልባችን ይልቅ የምንዋዋሳቸው ቁሳዊ ዕቃዎቻችን (ሙቀጫና ዘነዘናው ፤ ወንፊትና ዱቄቱ ፤ መፍለጫውና(ፋስ)
እንጨቱ ፤ ላፕቶፕና ፍሌሻችን …) ይበልጥ ይስማማሉ፡፡
አጼው “አንድ ብቻውን ሆኖ” የቤተ ክህነትንም ተጽዕኖ በመቋቋምም በጣም
ይታወቃል፡፡ ዛሬ ቤተ ክህነቱ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንቅስቃሴ በሃይማኖትም
በአገር ልማትም ተሳትፎ ከማድረግ ይልቅ በሃይማኖት ደረጃ ብዙ የእምነቱን
ተከታይ አባላት አስረክበው ፤ ከመበላላትና በዘር በወንዝ ተከፋፍሎ ሀገረ ስብከት ከማደራጀት ያለፈ ሥራ ለማየት አልታደልንም፤ ከዚህ
ባለፈ፦
“
በተባራሪ ፥ በስደት አንድ ወይም ሁለት ኢትዮጲያውያን መጠነኛ ዕውቀትና ቋንቋ ከፈረንጅ አገር በችግር ተምረው ይዘው ፥ በብርቅ
ወደአገር ገብተው እንደሆነ ወይም ካንድ ሚሲዮን ተጠግተው ትንሽ ትምህርት ቀስመው እንደሆነ ከፈረንጅ ጋር አብሮ እየበላ ፥ እየጠጣ
የኖረ ወይም በሚሲዮን ቤት ያደገ በተዋሕዶ ሃይማኖት መጽናቱ ፥ በዓል ማክበሩ ፥ ጾም መጾሙ ፥ አጠራጣሪ ስለሆነ፥ በምንም አይነት
በመንግሥቱ ሥልጣን ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ሊሰጠው ፥ ምክሩና አስተያየቱ በቁም ነገር ሊደመጥ ወይም ተደምጦ በሥራ ላይ ሊውል አይችልም፡፡
ሲበዛ ቢውል ፥ ለንጉሡ ወይም ለባለሥልጣኑ የግደታ ሆኖ የአስተርጓሚነት ወይም የተላላኪነት ደረጃ ይሰጠዋል እንጂ ፥ የራስነትን
የደጃዝማችነትን ማዕረግ አግኝቶ በትምህትር የቀሰመውን የሥራ ፍሬ በባለሥልጣንነት ደረጃ ለማሳየት አይችልም፡፡” (ተክለ ጻድቅ መኲሪያ ፤ ዐጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጲያ አንድነት ፤ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ፤ 1981 ፤ አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጲያ
፤ ገጽ.277)
የተክለ ጻድቅ መኩሪያ አባባል ዛሬም ድረስ በቤተ ክህነትም በቤተ መንግሥትም
ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ፀሐፊ በዚህ ዙርያ የገጠመው እውነተኛ ገጠመኝ አለው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ቤተ ክርስቲያን
በብዙ መቶ ሺህ ግምት ያለው የፍትሐ ብሔር ክስ ይቀርብበትና የሆነውን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አመራሮች ባሉበት ያለውን ሁሉ አስረድቶ
ሊሆን ያለውን ያሳያል፡፡ ነገር ግን አመራሮቹ ምክሩ “የልጅና ያልጠበቁት ሰው ምክር” ሆኖባቸው ባለመቀበል ሕጋዊ ነገር እያላቸው
ከነኪሳራው በቤተ ክርስቲያኑ ተፈርዷል፡፡ በቤተ መንግስትም ቢሆን ከተማረውና ካስተዋለው ይልቅ (የተማረው በደጅ እየተገፋ) ከዕውቀትና
ከማስተዋል የጎደሉ የፖለቲካ ስል አፈኞች ሲመሩ እያየን ነው፡፡
ከዚህ የሚከፋው ነገር ብዙ ጊዜ የነገረ መለኰት ተማሪዎች ተመርቀው ወደሐገረ
ስብከት ሲላኩ ላለመቀበል ፈርተው ተቀብለው፤ ነገር ግን ከማባረርና አፍ አውጥቶ አንፈልግም ከማለት ይልቅ በተለያየ ምክንያት በማማረር
ቦታውን ለቀው እንዲሄዱ የሚደረገውም ሥራ ከእጅግ እጅግ በጣም ጥቂት
ሀገረ ስብከት በቀር ሁሉም ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም ለዕድገትና ለብዙ ነገር መሻሻል ወሳኝ ናቸው የሚባሉትን የነገረ
መለኮት ትምህርት ቤቶችን ለማስፋፋት ከማሰብ ይልቅ “የመናፍቃን መፍለቂያ ሆነዋልና ትምህርት ቤቶቹ ይዘጉ” የሚሉ በጳጳስ ደረጃም
መኖራቸውን ስንሰማና ስናይ አጼውን ለጳጳስነት ያስመኛል፤ ያስጎመጃልም፡፡
እንኪያስ፦ የአጼውን ሥርዓት ከሚናፍቁ ወገን አይደለሁም፡፡ እንዳለመታደል
የአጼዎቹን ክፋት ብቻ አጉልተን መሠረታችንን ልዩነት ላይ ያደረግን ብዙ ነን፤ ይሁንና ክፉውንም ምሳሌ የሚሆን መልካም ነገራቸውንም
አንስተን፥ ክፉውን በቅን መንፈስ ተማምነንና ተናዘን በይቅርታ ብንዘጋው የጣልነውን መልካም ነገር ደግሞ ብንወቃቀስ ያቀራርበናል
ብዬ አምናለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ እኛ ኢትዮጲያውያን እንዲህ ያለ መሪና ልብ ያሻናል ፤ አብረን ሳንኖር አብረን መሞት አይረባንም፤
ተሸነጋግለን ኖረን የእውነት መሞቱን ማቆሙ ይበጀናል፤ እኛ ኢትዮጲያውያን ከአጼያችን መማር ይገባናል፡፡ ጀግንነትን በከንቱ ትምክህት
ሳይሆን ሊማር በሚወድ ትሁት ልብ ደግሞ ማስገዛትን እንልመድ፤ በብሔርነት ፣ በወንዝነት ፣ በቀለምና በዘር ያይደለ ወንድማማችነትና
እህትነት የእውነት ዘልቆ ይሰማን፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ብዙ እንከኖች ቢኖሩበትም ከምንማርበት አንዱ ይህ ነውና ይህን እንማማርበት እላለሁ፡፡
ጌታ ኢየሱስ ሆይ! ለሕዝብህ ማስተዋልን አብዛ፡፡ አሜን፡፡
Amen
ReplyDeleteAmen
ReplyDelete"ኢትዮጲያ” እያልክ የምትጽፍ አስበህበት ነው ወይስ ኢትዮጵያ ለማለት?
ReplyDelete