Tuesday 23 December 2014

የትኩረት ጩኸት ትኩረትን ሲያደበዝዝ


                                  Please read in PDF              

     በአገራችን ትኩረትን የሚስበው ድርጊት እንጂ ዝግጅት አይደለም፤ አንድ ከባድና ዘግናኝ ድርጊት ሲፈጸም ብዙ ጊዜ ስሜቶቻችን ተጋግሎ መንጫጫት፤ ድርጊቱ እንዳይፈጸም ቀድመን ከመሥራት ይልቅ ከድርጊቱ በኋላ በጣም መጯጯህ ፣ ሰላማዊ ሰልፎች ፣ ብዙ ስብሰባዎች ፣ የአቋም መግለጫዎችና የስሜት ዕርምጃዎችም ይወሰዳሉ፡፡  ማሳያዎችን በምሳሌ ብናነሳ፦ በባለፈው ወር የአዋሽ ፓርክን በሚያቋርጠው ትልቁ የምሥራቅ ኢትዮጲያ መንገድ በጉዞ ላይ ሳለ በአንድ ቅጥቅጥ አይሱዙ ላይ በደረሰው አደጋ ከሐያ ሰባት ሰዎች በላይ የሞት አደጋ መድረሱን ሰምተን ሳናባራ፤ ወዲያውኑ በተወሰደው እርምጃ መንገዶች ላይ በተደረገው (በዋናው አስፓልት ላይ መኪናዎች በጉዟቸው እንዲያቀዘቅዙ ለማድረግ በተደረገው ሌላ የአስፓልት ጉማጅ ሥራ) በተወሰደው የስሜት ዕርምጃ ሌሎች የመኪና አደጋዎች መከሰታቸውን ከቦታው ሄዶ ማስተዋል ይቻላል፡፡
    አሁንም ሌላ ማሳያ ብናነሳ ፦ በባለፈው ወር ከተከሰተው ጆሮን ጭው ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ የእህት ሐና ላላንጎ ጉዳይ  ነው፡፡ ድርጊቱ ከዳር እስከዳር ብዙ በጣም ብዙ አነጋግሯል፡፡ ከወረዳ እስከ ሚኒስቴር ቢሮ ፤ ከሆስፒታል እስከ የፖሊስ መምሪያና ጣቢያዎች ፤ ከመንገድ ዳር “ታዛቢ” እስከመኪና አሽከርካሪዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያሉበትን ልልነትና ግድ የለሽነት በሚገባ አጢነናል፡፡ ጥቂት ስህተት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል አይተናል፡፡ የፖሊስ ዳተኝት ፣ የሆስፒታሎቻችን ከልክ ያለፈ ቸለተኝነት ድርጊቱን ከፈጸሙት የማይተናነስ መሆኑን ሌላ ምስክር ሳያሻ የአደባባይ ገመና ሆኗል፡፡

     የሐና ጉዳይ እንደተሰማ ብዙ ብዕሮች ተመዘዙ፤ ብዙ ስብሰባዎች የአቋም መግለጫ አሰሙ፤ ብዙ የሴት ወይዛዝርቶችና እንደህግ ባለሙያ ይገባናል ያሉቱ እንባ የሚያቀረዝዙ ንግግሮችን አሰሙን፡፡ ከካሚላት በፊትና በኋላ የተደረጉት ጾታዊ ጥቃቶች (ከእጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር) በወጉ እንኳ ህጋዊ መፍትሔ ያገኙ አይደሉም፡፡ አንድ አይን አጠፋ ብሎ አሥራ ሦስትና አሥራ አምስት የሚፈርደው የዳኝነት ሥርዓታችን ሁለንተናን ላበላሸ ወንጀለኛ ግን የአንድ አይን ያህል እንኳ ለምን እንደማይሰማው አይገባኝም፡፡ የነካሚላትና የሌሎችም ጉዳይ “ከባድ አቧራ” አስነስቶ ነበር፡፡ መጨረሻው ግን ይጐመዝዛል፡፡
    እያደር የሚሻል ሳይሆን የሚብስ፤ ለጆሮም የሚሰቀጥጥ ነገር እየሰማን ነው፡፡ በሰማን ማግስት እንጮኻለን ፥ ከዚያ ምንም እንዳልተፈጠረ ወደየቤታችን ተመልሰን ለሽ እንላለን እንጂ የጮህንለትን ፣ ብዙ የተወያየንለትን ነገር አስታውሰን ከፍጻሜው ለመሄድና እስከውጤቱ ለመራመድ ያለን ስሜትና ዝግጁነት የሞተ ነው፡፡ በተለይም የነገሩን ሥረ መሠረትና የመነሾውን ምንጭ ለመረዳት ፍጹም ዝግጁነት የለንም ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
    በቅርቡ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በዓለም ላይ የዝሙትና የሴት ዕርቃን ፊልሞችን (sex films and pornographic images) አብዝተው የሚመለከቱ ብዙ ዜጎች ካሉባት አገሮች ኢትዮጲያ ወደግንባር ቀደሞቹ እየገሰገሰች መሆኗን አመልክቷል፡፡ በእርግጥም በየመንግስት የስብሰባ ማዕከላት ጎራ ብለን የምንታዘበው አንድ እውነት ከተሳታፊው ጥቂት ያይደለው ቁጥር ከጎኑ ላለው ባልንጀራ የዝሙት ፊልም ወይም የዕርቃን ሴት ወይም ወንድ ገላ በማሳየት “መዝናናት” ነው፡፡ ከመጀመርያ ደረጃና ከከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩንቨርሲቲዎቻችን ጓዲያ ጐድጓዳ የሚተረማመሰው የዝሙት አውሊያና ዛር ፤ በእጅግ ብዙዎቹ ሆቴልና ሞቴል እንዲሁም ግሮሠሪዎቻችን የሚፈጸመውን ነውርና ርኩሰት ላየና ላስተዋለ … እግዚአብሔር ምን ያህል እንደታገሰን እንጂ የክርስቲያን አገር የሚሰኝ ነገር እንደሌለን አስበን ብዙ ባለቀስን ነበር፡፡
   የእግዚአብሔር ቃል “መንፈስን አታጥፉ” ይላል፡፡ (1ተሰ.5፥19) ቅዱስ ጳውሎስ የተሰሎንቄ ምዕመናን መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጠው ሙቀትና ብርሃን በመራቅና በመለየት ፥ የተወደዱበትንና ለልጅነት የተጠሩበትን ለቤዛም ቀን የታተሙበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ በማሳዘን (ኤፌ.4፥30) እንዳያጠፉ ይመክራቸዋል፡፡ በጥንት ማኅተም የባለ ንብረትነት ማረጋገጫ ነው፡፡ እኛ የእግዚአብሔር ንብረት ለመሆናችን ፥ ደሙም የታተመብንና መንፈስ ቅዱስም ሕያዋን መሆናችንን የሚመሰክርልን ነው፡፡ ስለዚህም መንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል አለውና ያዝናል ፤ በኃጢአትም ከጸናን ከእኛ ዘንድም ሊጠፋም ይችላል፡፡
    የመንፈስ ቅዱስን እሳት ከሚያጠፉ ኃጢአቶች ዋነኛው ዝሙት ነው ፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የሚያዳክም ሥጋዊ የሆነ አምልኰ እንዳይደረግም ሐዋርያው ያስጠነቅቃል፡፡ ዝሙትን እንድንሸሸው በጥብቅ የተነገረን (1ቆሮ.6፥18) ልናመልጠው የምንችለውና የምናሸንፈው ቆመን በመታገል ሳይሆን በመሸሽ ስለሆነ ነው፡፡(ዘፍ.39፥12) ዝሙትን መሸሽ ፈሪነት አይደለም ፤ ትልቅ ማስተዋልና መንፈሳዊ ጥበብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ጥለን በዝሙት ፊልሞችና በዕርቃን ስእሎች ፊት መቆማችንና ለማየትም መቀመጣችን ሰውነታችንን ከማንደድ አልፎ ውጤቱን እንዲህ ሐና ላላንጎና ሌሎች ባልተጠቀሱ እህቶችና ወንድሞች ላይ የሚፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊትን እያሳየን ነው፡፡
    ትኩረት መስጠት ካለብን አገባብ ባለው መልኩ ከመሠረቱ ችግሩ ሊፈታ በሚችል መልኩ እንጂ የለብ ለብ ጫጫታ ለወንጀሎች የልብ ልብ እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሔ ፍጹም አይኖረውም፡፡ የችግሮቻችን ምንጩና መነሻው ያለው የህጉ መጥበቅና መላላት ብቻ ሳይሆን የችግራችን ዋናው መፍትሔ ያለው ቢመረንም የመንፈሳዊነታችን መጠልሸት ላይ ነው፡፡ ሞባይሎችንና ላፕቶፖቻችን የተሸከሙት የዝሙትና የርኩሰት ነገር ሆኖ ከልጆቻችን ድንግልናና ክብርን መጠበቅ ምስኪንነት ነው፤ በአስነዋሪ የዝሙት ጥያቄ የሥር ሠራተኞቻችንና ህጻናትን እያስጨነቅን፥ በየስብሰባው “የዝሙትን አስከፊነት ብንደሰኩር” ውጤቱ አሳዛኝ ከመሆን አያልፍም፡፡
     “ትኩረት ይሰጠው” የሚለው ጩኸታቸው  እውነተኛውን ትኩረት እንዳያደበዝዝ ቀድመን በዝሙትና የፖርኖግራፊ ፊልም በማየት ወጣቶቿና ጎልማሳዎቿ ግንባር ቀደም እየሆኑባትን ያለችውን ኢትዮጲያችንን እንዴት ከዚህ ካለ የርኩሰትና የነውር ግስጋሴዋ ማስቆምና ማውጣት እንዳለብን ከማሰብ መጀመር እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ጩኸታችን ድርጊትን ተከትሎ መሆን የለበትም ፤ ችግሩ እንዳይከሰት ከችግሩ ቀድመን መሥራትን ልማድ አድርገን ልንጀምር ፤ የማህበረሰብንና የቤተሰብ ስብራት ከማከም ቀድሞ እንዳይሰበር በትጋት ከመሥራት መጀመር ይገባናል እንጂ፡፡ 
    እውነት እንናገር ከተባለ እየተሸነጋገልን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ ከመካከላችን አጥፍተነዋል፡፡ ነውራችን ከጌታ መንበር ፊት መድረሱን ማስተባበያ ማቅረቡ ለንስሐ ልብ አያዘጋጀንም፡፡ ወጣት ሐና ላላንጎ ላይ የተፈጸመው ድርጊት የኢትዮጲያ አብያተ ክርስቲያናት ምን እየሠሩ ነው? ያስብላል፡፡ መንግሥትና ወንጀለኞች ላይ ብቻ ማላከኩና እኛ ጥፋተኞች አይደለም ማለት አግባብ አይመስለኝም፡፡ “መንፈስን አታጥፉ” ተብለን በእርግጥም በግልጥ ነውራችን መንፈስን አጥፍተናልና ከልብ ንስሐ ልንገባ ይገባናል፡፡ አልያ ትኩረት እያልን ጮኸን ትኩረት እያደበዘዝን ሊመጣ ያለውን ጥፋት ለመናገር ነቢይ መሆን አያሻም፡፡ 

አቤቱ ሕዝብህን አድን ፤ርስትህን ባርክ ፤ካህናትህንም ለእውነት እንዲጨክኑ አንቃ፡፡ አሜን፡፡ 

2 comments:

  1. Without a doubt, the best how to make homemade ice cream to make ice cream cake,
    is the one which you may often use. The one that is worst is the one which remains in the garage and gathers dust.

    ReplyDelete
  2. Yehenen blog yagegnewet ke Abaselama blog new. Ene yemenorow America new.Alfo alfo Abaselaman Anebalew ena hule yegermegal benesu blogelaye Ethiopian,Erasen Aywalew kerstnas mendenw elalew. Eski Andeneger lengerh wendeme!BEABASELAMA Blog yetesafe".Americ ezi yederesechiw Bible lay seletemeseretech new" blo Asenebeben!!wow yAmerica churchoch( Wondoch na Wondoch)(set na set) Yemtagaba hager, Hatiyat Zemenawinet yehonebet hager, yegnawoch wengel gebtonal yalwut yenesu simesekrulun, Manew tefategn Ethiopia hizbeko denke neber,seraten yemiyawek!!! wengel gebtonal mamen bech yebekal besera Atedenem belew Hezbun endikebezebze yaderegu kalun tetew zemenawineten yemiterku.! Manew teteyaki??eski meleselng!! Ewenet wendeme leke blehal.chegeru yalew kemenchu new Lezihulu meskelkel hiwet Ethiopian Abiyatekrestanoch nachew.Ewenet yegeban Wengel SileHatiyat Ayaweram Ende??Kerstose endemiweden ena Adagn endehone becha new? Egziabeher lizihizbe meheretun yelakelet.Antenem bagelgelot yasenahe. Selefidelu yekerta!!

    ReplyDelete