Monday 15 December 2014

የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮች(የመጨረሻ ክፍል)



4. አገልግሎቱን ለእግዚአብሔር ለቃሉ አደራ መስጠትን ያውቃል (ቁ.32)

                  “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ
                  ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ።” (2ጢሞ.2፥1)

   አገልጋዮች የእግዚአብሔርን መንጋ የምንጠብቅ ሲመስለን እንስታለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የኤፌሶንን ሽማግሌዎች (ጳጳሳት) “እናንተን ራሳችሁን … ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋችሁ” ሲላቸው እናያለን፡፡ የእግዚአብሔር መንጋ የሚጠፋው ወይም የሚጎዳው ከእግዚአብሔር በኃጢአቱ ሲለይ ወይም እግዚአብሔር ንስሐ ባለመግባቱ በኃጢአቱ ምክንያት ሲለየው  ነው፡፡ ያ እንዳይሆን መሪዎቹ ሕዝቡን ትክክለኛው የጸጋውን ቃል ወንጌል በማስተማር ሊመሩት ይገባል፡፡ በትክክል ሳይነግሩትና ሳያስተምሩት ሲቀር ግን ይጎዱታል ማለትም የመንግሥተ ሰማያት በር ይዘጉበታል፡፡
      ቅዱስ ጳውሎስ እርሱ ቀድሞ ወንጌልን ለመስበክ አደራ ከክርስቶስ ኢየሱስ እንደተቀበለ እንዲሁ፤ (ሐዋ.9፥1-16 ፤ 26፥16 ፤ 1ቆሮ.9፥17) አሁን ደግሞ እርሱ ለታመኑት ሲሰጥና የታመኑትም ለሌሎች ለታመኑ አደራ እንዲሠጡ ሲተጋ እናየዋለን፡፡ ወንጌል መስበክ አደራ ከሆነ አደራው ኃላፊነት ያለበት አደራ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወንጌልን ኃላፊነት ተሰምቷቸው ከፍቅር በተነሳ ውዴታ እንጂ በምርጫ እንዲያገለግሉ አልተጠሩም፡፡

  ወንጌልን በምርጫ ማገልገላችን ለራሳቸው የሚስማሙ አስተማሪዎችን የሚያሳድዱና ከእግዚአብሔር የሆነውን ለመማርና ለመለወጥ የማይዘጋጁ ፣ የሚፈልጉትን ብቻ እንዲነገራቸው የሚናፍቁበእውነት መሠረት ላይ ከመታነፅ ይልቅ በራሳቸው ፈቃድ ለገዛ ምኞታቸው የሚመቻቸውን ትምህርት የሚያከማቹ አማኞችን እንድናፈራ አድርጎናል:: (2 ጢሞ. 4፥3) የራሳቸውን አስተማሪዎች የሚያከማቹ በበዙበት በዚህ በእኛ ጊዜ ከእግዚአብሔር የሆነውን ሀሳብ ለማንፀባረቅ እንዲሁም በትክክል የእግዚአብሔር ቃል የሚለውን ለመረዳት ቃሉን ለባለአደራዎች በእምነት መስጠት የተገባና አማራጭ የሚገኝለት አይደለም::
   መንጋውን ለማነጽ የእግዚአብሔር የጸጋ ቃል ያስፈልጋል፡፡ የለውጥ ፤ የማሳደግ ዋናው ሃሳብ የእግዚአብሔር ሃሳብ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁን ቅዱስ ጢሞቴዎስን “ … ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ” በማለት የሚመክረው ስለዚህ ነው፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር የጥበቃንና የመንከባከብን ሕይወት ከተለማመድንና በዚህ ሕይወት ከተጓዝን አደራውን ማስተላለፍ ያለብን ፍጹም በሆነ በእግዚአብሔር ፍርሃት ሙላት ላላቸውና ለታመኑት አገልጋዮች ነው አደራውን መስጠት የሚገባን፡፡
   አገልግሎታችንና ሩጫችንን ፤ አማኞቻችንንም ጭምር ሁሉ ለእግዚአብሔር አደራ አለመስጠት ማለት በቀዳዳ ኮረጆ ዕንቁ የማስቀመጥ ያህል ነው፡፡ ለእግዚአብሔር አደራ የተሰጡ የትኞቹም ነገሮቻችን፥ አወላለዳቸው መንታ መንታና ባለብዙ ትርፎች ናቸው እንጂ ከቶውንም ኪሳራ የለባቸውም፡፡ ለዚህ ነው የታመኑቱ የጌታ አገልጋዮች ለአህዛብ ወንጌልን ከሰበኩ በኋላ “ላመኑበት አደራ በመስጠት” የሚታወቁት፡፡(ሐዋ.14፥23)
       ሁለት ነገሮች መዘንጋት የለባቸውም ፤ እኛ አገልጋዮች ራሳችን ለእግዚአብሔር አደራ የተሰጠን ነን፤ እንዲሁም ቃሉንም ለታመኑት አደራ የምንሰጥም ነን፡፡ እኛ በእግዚአብሔር ፊት ለአደራው ከታመንን (እግዚአብሔር ታማኝ አድርጎ ከመረጠን) ፥  በእግዚአብሔር ፊት የታመኑትን በትጋት ልናዘጋጅ ደግሞ ይገባናል፡፡ ጳጳሳት የተባሉቱ ራሳቸው ለእግዚአብሔር አደራ የተሠጡ ከሆነ እንኪያስ በብዙ ሊያገለግሉና ሊደክሙ፤ የታመኑ ባላደሮችን ሊያከማቹ ይገባቸዋል ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ይህን እውነት በዙርያችን ብንፈልግ በጭንቅ እንኳ ማግኘት ይከብዳል!!! እርሱ የታመነ የወንጌል ባለሟል እንደሆነ አስቦ ለጌታው የታመኑ የወንጌል ባላደሮችን የሚያከማች የተመሰገነ ነው!!!
       በጐችን ለእግዚአብሔር አደራ ከመስጠት ይልቅ በራስ ጥበብ ለማቆየት የምናደርገው ጥረት ብዙ ጊዜ ማፍረስን እንደሥራ ለምደነው እንድንኖር አድጐናል፡፡ በአፈኛ ሰባኪ ፣ በድምጸ መረዋ ዘማሪ ፣ የአደረጃጀት ንድፍና ተዋረድ ፣ ተረትና ምሳሌ እየነገሩ ሕዝቡን ለፌዝ ፤ አውደ ምህረቱን የቧልት መድረክ በሚደርጉቱ የሆነውን እያየን ነው፡፡ የጸጋውን ወንጌል ሰብከንና አስተምረን በጐችን ለእግዚአብሔር አደራ መስጠት የዘላለምና የማይነጥፍ ፍሬን በአይናችን ለማየታችን ሌላ ምስክር ሳያሻ እኛው ሕያው ምስክሮች እንሆናለን፡፡
    የብርሃን መልአክ የሚመስሉ አገልጋዮችን የክፋት መንገዳቸውን በመረዳት እንዲህ ባለ ማስተዋልና ጥበብ ልንለያቸው ይገባናል፡፡ እረኛ ከሆንን የበጐቹን ጠላት ባህርይና እኛ ልናደርግ የሚገባንን በሚገባ ማወቅ አለብን፡፡ እረኝነት ሙያ ሳይሆን የሕይወት ኃላፊነትን ተረክቦ ለታመነው ጌታ በሕይወት ማስረከብ ነው፡፡ ሕያውና አንድ የበግ መንጋ(አማኞችን) ተቀብሎ በየምክንያቱ በታትኖ ፤ አካሉንና መንፈሱን አጉድሎ ጌታን እንደመጠበቅ ያለ የእረኝነት ክስረት የለምና በጐችን በሚገባ በአደራ የሚጠብቅ ልብ እንዲሰጠን የመከሩን ጌታ በትጋት መለመን ያሻናል፡፡
 ጌታ ሆይ! አገልግለን ላንተ አደራ መስጠት እንድንችል እርዳን፡፡ አሜን፡፡

ተፈጸመ፡፡

No comments:

Post a Comment