2. የቂሳርያው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ(ሐዋ.10፥1-48)
ቆርኔሌዎስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር “እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ
ሰው” ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የመፍራቱና የማክበሩ መገለጫ እግዚአብሔርን ያከብራል(ሐዋ.10፥22)፣ ለህዝቡ እርዳታና ቸርነትን
ያደርጋል፤ የጸሎት ህይወትም ነበረው፡፡(ሐዋ.10፥2) ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የአይሁድን ሥርዐት በመከተል አልተገረዘም፣ ምስክሮች
ባሉበት የውኃ ጥምቀት አልተጠመቀም፤ በመቅደስም መሥዋዕት አላቀረበም፡፡ ይህ ደግሞ አህዛብ ወደይሁዲ እምነት እንዳይመጡ ከልካይ
ከነበሩት ሥርዐት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ነበሩ፡፡
ከአህዛብ ወደአይሁድ እምነት ሙሉ ለሙሉ የገባና ሥርዐታቸውን ሳያጓድል
የሚፈጽም ባይሆንም፤ ቆርኔሌዎስ በአንድ አምላክ አምኖ የአይሁድን ሃይማኖትና ምግባር የሚከተል ሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ፦ እንደአይሁድ
ሥርዐት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጸልይ ነበር፡፡(ሐዋ.3፥1) በዛሬ ዘመን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያሉ አማኞችን ተቀብለው፤
የጸጋውንና የመዳኑን ወንጌል ከመስበክ ይልቅ የራሳቸውን ሥርዓትና መመሪያ በማሸከም አማኞችን ማጉበጣቸው ያሳዝናል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ
እንደመናፍቅና ቀኖና ጣሽ ቆጥረው ማውገዝ እንጂ ማቅረብ አይሆንላቸውም፡፡
ቆርኔሌዎስ፦
v እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክም
ቢሆን፤
v ምጽዋትን እየሠጠ ቸርነትን ቢያደርግም፤
v በየእለቱ በጸሎት ቢተጋም፤
v መልዐክ ተገልጦለት ራዕይ ቢያይም፤
v ጸሎቱና ምጽዋቱ ያረገለት ጻድቅ፤
v በአይሁድም ህዝብ ሁሉ የተመሰከረለት
ቢሆንም(ሐዋ.10፥22)፤
ቆርኔሌዎስ “እርሱና ቤተሠቡ የሚድኑበትን
ነገር ያልሠማ ነበርና፤ እንዲሠማ ተባለለት”፡፡(ሐዋ.10፥13) ትጉህ መንፈሳዊ፣ የተመሰከረለት አገልጋይ፣ ታላላቅ ህልምና ራዕይ
የተገለጠልን ወይም የምንተረጉም፣ በአማኝ የተከበብን፣ መልዐክ የሚገለጥልን፣ ብዙ ምጽዋት የምንሰጥ፣ ብዙ ጸሎት የምንጸልይ፣ ብዙ
ጾም የምንጾም ወይም የአብርሐም ዘር ልጆች፣ እግዚአብሔርን የምንፈራ ብንሆን የመዳን ቃል ወይም የመዳኑን ወንጌል ያልሰማን እንኖራለን፡፡
ስለዚህም ይህ ሁሉ ሆኖልን ወንጌሉ ግድ ያስፈልገናል፡፡(ሐዋ.13፥26)
ቅዱስ ጴጥሮስ ያየውን ራዕይ ለመቀበል በመንፈሱ ሙግት ገጥሟል፡፡ “ጌታ
ሆይ ይህማ አይሆንም”(ሐዋ.10፥14) እያለ የሰማርያ ሰዎችን፣ ኢትዮጲያዊውን ጃንደረባ(ሐዋ.8፥14፤26)፣ ይህንኑ የመቶ አለቃ
ያሸነፈውን አህዛብንም ተቀባዩን ወንጌል ለመቀበል ተቸግሯል፡፡ በልቡ ሥር የሰደደው ኦሪታዊ ሰውነቱ “አንዳች ርኩስ የሚያጸይፍ ከቶ
በልቼ አላውቅምና” በማለት ወዲያው ከመታዘዝ ዘገየ፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ ድካም ብዙ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን ዛሬም እየራራ
በውበት ድካሙን ያግዛል፡፡ ስለዚህም ጴጥሮስ ለመጡቱ አህዛባውያኑን የቆርኔሌዎስን እንግዶች ማረፊያ አዘጋጅቶ፤ ወደውስጥም አስገብቶ
ተቀበላቸው፡፡(ሐዋ.10፥23) ድንበር ሠርተው የተለያዩት አይሁድና አህዛብ አሁን በግልጥ በአንዱ ማረፊያ በክርስቶስ ኢየሱስ ተጋመዱ፡፡
ፈራ፤ ተባ ባዩ ጴጥሮስ ከአይሁድ ስደት እንደሚያመጣበት እያወቀ የታወቀውን የአይሁድ ወግና ባህል ስለወንጌል ሲል ጣሰው፡፡
የመቶ አለቃው
ቆርኔሌዎስ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደእርሱ በመጣ ጊዜ ሙሉ ቤተሠቡን ሰብስቦ ነበር የጠበቀው፡፡(ሐዋ.10፥33) አህዛባዊው አማኝ መልዕክቱ የጴጥሮስ ሳይሆን የእግዚአብሔር መሆኑንና ጴጥሮስም
ከእግዚአብሔር የታዘዘውን እንጂ ከራሱ እንደማይናገር እርግጠኛ ነበር፡፡ ስለዚህም ራሱን በጴጥሮስ ፊት ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት
እንዳለ ቆጠረው፡፡ ብዙ ጊዜ የዛሬው “የወንጌል አውደ ምህረቶች ” የጣሉት እውነት፤ አገልጋዩ የጴጥሮስን ልብ፥ ሰሚው ደግሞ
የቆርኔሌዎስን ማስተዋል አለመያዙ ነው፡፡ ጴጥሮሳዊው አገልጋይ ከእግዚአብሔር ብቻ የታዘዘውን መናገር ሲገባው እንጀራውንና የደብሩን
አለቃ፤ ከሳሾችንና አበሉን እያሰበ “ወንጌሉን ያመቻምቸዋል”፤ ቆርኔሌዎሳዊው ሰሚም ተሰባሪውን ሰው እያደመጠ፦ ቃሉን ያደንቃል፣
ጐራ ለይቶ ይደግፋል፣ የሚፈልገውን እንዲናገርለት ይማጠናል እንጂ እውነትን በልበ ሰፊነት ከቃሉ አንጻር እየመዘነ እንደቆርኔሌዎስ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አያስቀምጥም፡፡
የመቶ አለቃው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ቃሉን በተከፈተ ልብ ሰምተዋልና መንፈስ
ቅዱስ ወርዶላቸዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አንድ ጊዜ ብቻ ለሐዋርያት የወረደ
አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ሊያንጽ፣ ሊያበረታ፣ ሊያጸና፣ ሊያጽናና፣ ኃይልን ሊሰጥ ብዙ ጊዜ ወርዷል፤ በጸለዩ ቁጥርም ሊለውጥ፣
ሊያጐለምስ በተደጋጋሚ ወርዷል፡፡ ለሐዋርያት ሥራን ሊያሠራ የወረደው
መንፈስ ቅዱስ እነሆ አሁን ለቆርኔሌዎስና ቤተሠቡ ወረደ፤ ሥጦታውም እንደወንዝ ፈሰሰ፤ ልሳኖችንም ተናገሩ፡፡ (ሐዋ.10፥44-47)
ከአይሁድና
ከአህዛብ የተመለሱ ክርስቲያኖች እኩል የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታ ተቀብለዋል፡፡ የአይሁድ ክርስቲያኖች በጰንጠቆስጤ(በበዓለ ሐምሳው)
እለት(ሐዋ.2፥4) በብዙ ልሳኖች እንደተናገሩ፤ የአህዛብ ክርስቲያኖችም የመቶ አለቃው ቆርኔሌዎስና ቤተሠቡ በልሳኖች ተናግረው አሳይተዋል፡፡
ከአይሁድም ከአህዛብም የመጡ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር መንግስት ሥጦታና ጸጋ እኩል ፈሶላቸዋል፡፡
አደላዳዩ ጌታ ሆይ! ክብርና አምልኰ
ሁሉ ላንተ ብቻ ይጠቅለልልህ፡፡ አሜን፡፡
ይቀጥላል…
kale hiwot yasemalin
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማለን!!!
ReplyDeleteተባረክ የህይወትን ቃል ያሰማህ ወዳጄ ጸጋህይብዛ
ReplyDelete