Friday, 4 July 2014

“በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ”(ሐዋ.7÷39) (ክፍል - 1)

Please read in PDF
     
     የጌታ ኢየሱስ መንግስት እየሰፋች፤ ብዙዎችንም እየወረሰች የመጣችውን የመጀመርያቱን የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ለማስቀጠል “በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ሐዋርያት መርጠው ለማዕድ አገልግሎት ሾሟቸው፡፡”(ሐዋ.6፥6) ከእነዚህ ከሰባቱ ታላቁ ዲያቆን እስጢፋኖስ “ ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር።”(ሐዋ.6፥8)፡፡ ይህ ብርቱ የእግዚአብሔር ሰው ሰማዕት ሆኖ፤ ሞቱ ብዙዎችን ለጥቅም ከመበተኑ በፊት  የቀደሙትን የእስራኤልን ዘሥጋ ህይወትና አሁን የኪዳኑን ፍጻሜ እያዩ ያላመኑትን ፈሪሳውያንና የመቅደሱን ታላላቅ ካህናት እያነጻጸረ ሳይሸነግልና ሳይፈራ በብርቱ ቃል ወቀሳቸዋል፡፡

የግብጽ እስራኤል

     እስራኤል ልጆቹ ወደግብጽ ሲወርዱና በኋላ ላይ እርሱም አብሮ በረሃብ ምክንያት ሲሰደድ የመረረ ልቅሶ፣የልጁ የዮሴፍን ውለታ የሚረሳ አዲስ ንጉስና ህዝብ … እንደሚነሳ ያስተዋለ አይመስልም፡፡ እነርሱም ጥቂት በጥቂት ልባቸው በዚያ እየቀለጠ፣ የተገባላቸውን ኪዳንና ተስፋ ረስተው፣ ፈጽሞ ልባቸው በጣዖት አምልኮ ሊያዙ እንደሚችሉ ለቅጽበት እንኳ አላስተዋሉትም፡፡ ሰባ የእስራኤል ነፍስ ወደግብጽ ሲወርዱ (ሐዋ.7፥14)ሁለት ሚሊየን ገደማ ይሆኑም እንደሆነ ማን ለአፍታ እንኳ አሰላሰለ? አዎ! እስራኤል ወደግብጽ ሲወርዱ ሆዳቸውን እንጂ ጌታ እግዚአብሔር ለእነርሱ ያሰባትን ሃሳብ ፈጽመው ያስተዋሉም አልነበሩም፡፡
      ግብጽ ለእስራኤል ዘሥጋ የባርነት ቀንበር በመጫን ለእስራኤል ዘነፍስ ደግሞ መዳን ምክንያትና ቤዛ ለሆነው ስደተኛ ህጻን አባቱ እስኪጠራው (ሆሴ.12፥2፤ማቴ.2፥15) ማረፊያ በመሆኗ በታላቁ መጽሐፍ ተቀምጣለች፡፡ የእስራኤል ልጆች ግብጽን ባሰቧት ጊዜ በብዙ ቅንአት ይቃጠላሉ፡፡ ወንዶች ልጆቻቸውን ገና በማህጸን የገበሩባት፣ ጉልበቶቻቸው አለልክ የተበዘበዘባት ፣ ስድብን የጠገቡባት፣ ውለታቸውና ብድራታቸው በባዶ የተጣፋባት፣ የድካማቸውን ወዝ ያጡባት ፣ ምግብ ለጌቶቻቸው እያበሰሉ የተራቡባት ፣አስገባሪዎቻቸው ወዛቸውን የመጠጡባት ፣በልቅሶ ሸለቆ እንባቸውን የታጠቡባት ፣በዋርካዎቿና በዛፎቿ ጥላ ሥር የተከዙባት ፣በኮረብታዎቿ ሁሉ ላይ ምሬታቸውን ያሰሙባት ፣ራሔል እንባዋን ወደራማ የረጨችባት፣ እንግዶች አማልክት ነፍስና መንፈሷን ያስጨነቁባት ፣ እየዳኸች በባርነት ምጥ የተንፏቀቀችባት … የምድር ተስፋዋ ሁሉ ተሟጦ ክንድ ከኤሎሒም የተላከላትን ያቺን የግብጽ ምድር ኑሮ፣ ፊትና መልክ እንኳንስ እርሷ እስራኤል እኛም መቼም አንዘነጋውም፡፡

    ጌታ እግዚአብሔር እስራኤልን ነጻ ሊያወጣ የተነሳው በአስጨናቂዎቻቸውና በአስገባሪዎቻቸው ፊት በኩራቸውን መትቶ፤ እነርሱን በህይወት ታድጎ ነው፡፡ ወደተስፋይቱ ምድር የመራቸው ክንዱ ጸንታ ፤ እጁ ተዘርግታ፤ ባህረ ኤርትራን በኃይሉ አሻግሮ ነው፡፡ ግብጽ ለእስራኤል ልጆች የሞት መቃብር አስፍታ ስትቆፍር የሚምስ  በማሰበት እንዲወድቅ በኤርትራ ባህር ፈርዖንና ጐበዛዝቱ ከፈረሶቻቸው ጋር ወደቁ፡፡ አዎን! “ኃጢአት ከኃጢአተኛ ትወጣለች” እንዲል በፈርዖን እንዲሁ ሆነ፡፡ ሰይፍም የሚያነሱ በሰይፍ ይጠፋሉ፡፡(ማቴ.26÷52) ዛሬም በኃጢአት የሚቀማጠሉ መቃብራቸውንና ገሃነማቸውን በገዛ እጃቸው ነው የሚያዘጋጁት፡፡
    የግብጽ እስራኤል በሞትና በምሬት ደጃፍ ተቀምጠው ብዙ አመታትን የቆጠሩ ናቸው፡፡ ርስትና መንግስት እንደሌላቸውም የተጠቁና እጅግም የተጨቆኑ ነበሩ፡፡ ቀን መጥቶ ቀና እስኪያደርጋቸው በባህር ሊሰጥም ላለው ፈርኦንና መንግስቱ ባሮችና ገባሪዎች ነበሩ፡፡ ባርነቱ ከባድ ቢመስልም የማይሰበር የፍጡር ክንድ ግን የለምና ፤የግብጽ እስራኤል በታሪክ ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ የኤርትራን ባህር ሆድ ረግጠው “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው” ብለው ከአስፈሪው ባህርና ባርነት ማዶ በከበሮ ዘመሩለት፡፡የግብጽ እስራኤል ጭንቁን ባርነት በድል ዜማ ደመደሙት፡፡(ዘጸ.15፥1-19)

የበረሃው እስራኤል

     ሁለት ሚሊየን የሚጠጋ ህዝብ በቃዴስ በርኔ በረሃ ቀን ደመና፤ ሌሊት አምደ ብርሐን ተተክሎለት ሳይደክም በእግዚአብሔር መግቦት ይራመዳል፡፡እስራኤል በድንቅና በግሩም ትድግና ከግብጽ በአካለ ሥጋ ቢወጡም ግብጽ ግን ከልባቸውና ከሃሳባቸው አልወጣችም ነበር፡፡በበረሃው አለም እንደደመና የተጋረደችውን እጁን አላስተዋሉም፡፡ በሚያዝለው በረሃ ውስጥ ከዋርካ ይልቅ የሚያሳርፈው ጥላውንም ዘነጉ፡፡ የዋዕዩ አዙሪት በሚጥለው ምድረ በዳ ውስጥ አጽንቶ ያራመዳቸውን ታዳጊውን ጌታ በማጉረምረም አስመረሩት፡፡በጠል ገበታ የመና ማዕድ ዘርግቶ የመገባቸውንና ከዓለቱ ውኃን ያጠጣቸውን የህይወቱን ምንጭ የሚያረካውን ውኃ ተዘባበቱበት፡፡
     ከግብጽ ምድር ጀምሮ የለበሱት ልብስ በተባይ ሳይቀምል፣ የተጫሙት ጠፈር ሳያልቅ ፣በበረሃው ዓለም የሰውነቱ እድፍና ጉድፍእንደተላላፊ በሽታ ሳይፈጃቸው እንደግንብ የከለላቸውን መታመኛ ረሱት፡፡ ትላንት የተደረገልንን ማስተዋልን ካልቻልን ጠላት እንዴት እንደቀበረን ፣ግብጽ እንዴት እንደተጫወተችብን እንኳ እንዘነጋለን፡፡ግብጽ በፍጹም አትዘነጋም፡፡የማትዘነጋው በበጎነቱ አይደለም፡፡ ድሆችን ሙሉ የወዛቸውን ዋጋ የበላች ፣በደማቸው ብዙ ህንጻዎችን የገነባች የግፍ ከተማ በመሆኗ ነው፡፡
     እስራኤል ከሞትና ከመቃብራቸው በእግዚአብሔር ክንድ ወጥተው በበረሃ ውስጥ በተንጣለለው በእግዚአብሔር መግቦትና ጥበቃ ውስጥ ሆነው በልባቸው ግን ወደኋላ ተመለሱ፡፡ቅዱስ እስጢፋኖስ ይህንን ነው የገለጠው፡፡አመጸኝነታቸው ከልክ አልፎ ፦የኤርትራ ባህር በድንቅ ተከፍሎ፣ፈርዖንና ፈረሱ ሠራዊቱና ፈረሰኞቹ በባህሩ ዳርቻ ወድቀው እንዳላዩ ዛሬ ልባቸው ወደግብጽ መመለሱን ሲናገር እናንተም እንዲሁ ሆናችኋል ነው ያላቸው፡፡
    የመሲሁን ተስፋ ሲጠባበቁ የነበሩቱ ፈሪሳውያንና አይሁድ የመሲሁን መምጣትና መዳን አለመቀበላቸው ልክ የእስራኤል ዘሥጋን መንፈስ እንደሚመስል ይናገራቸዋል፡፡ይህን የሚናገረው ማንም ሊቃወም በማይችለው ጥበብና መንፈስ ነው፡፡“ … እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም፡፡”(ሐዋ.6፥10)፡፡እስጢፋኖስ ነቢያትን ያሳደዱትንና ጌታን ያሳዘኑትን አያቶቻቸውንና ጌታ ኢየሱስን የሰቀሉትን ልጆቻቸውን እያነጻጸረ ያቀርባል፡፡
የጌታ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡አሜን፡፡
ይቀጥላል …


No comments:

Post a Comment