የእግዚአብሔር ሀሳብ -
የእግዚአብሔር እስራኤል
በአንዱ እስራኤል መካከል ክርስቶስን በማመንና ባለማመን ምክንያት ልዩነት ሆኗል፡፡ በሥጋ የአንድ ዘር ወገን ነኝ ማለት የእግዚአብሔር ወገን ስለመሆን ዋስትና አይደለም፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ምንም እንኳ በመገረዝና እስራኤላዊ በመሆን ብቻ የእግዚአብሔር ወገን እንደሆኑ በቀደመው ኪዳን ቢታወቅም፤ አሁን ግን ይህ የለም፡፡ በግልጥ ቃሉ “ከእስራኤል የሚወለዱ ሁሉ እስራኤል አይደሉም” ብሏል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር እስራኤል ከአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም ህዝብ በክርስቶስ በማመን አዲስ ፍጥረት በመሆን የእግዚአብሔር እስራኤል ይሆናሉና፡፡
እስራኤል ዘሥጋ የሚመኩባቸው አብርሃምና ሣራ አላስተዋሉም እንጂ፤
አሞራዊና ኬጢያዊ ነበሩ፡፡(ህዝ.16፥1-4) እግዚአብሔር ለእስራኤል የገባውን የተስፋ ቃል ግን አጸናው፤ ከቶውንም
አላጠፈውም፡፡ ምክንያቱም ከጥንትም ተስፋው ከህዝቡ ታማኝ ያልሆኑትን አያካትትምና፡፡ ለአብርሃም “… ታላቅ ሕዝብም
አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ
የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ።”(ዘፍ.12፥2-3) እንዳለው ተስፋው ቀድሞም የታቀደው ለተስፋው ታማኝ ለሆኑ እውነተኛ
እስራኤላውያን ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ተስፋ የጠበቁ ጥቂቶች ተገኝተዋል፡፡
ዋናው የእግዚአብሔር ሀሳብና ዓላማ ግን አይሁድንም አህዛብንም
በክርስቶስ የሚያምኑትን ሁሉ ወደመንግስቱ ማፍለስ ወይም መጠቅለል ነው፡፡ ለዚህም ነው ከእስራኤል ዘሥጋ ይልቅ በክርስቶስ
የእስራኤል ዘነፍስ ወይም የእግዚአብሔር እስራኤል ወይም የክርስቶስ እስራኤል ያስፈለገው፡፡ ፊተኛው ኪዳን በክርስቶስ ታድሷል፡፡
በፊተኛው ኪዳን ያልተካተቱ ህዝቦች አሁን ይካተቱ ዘንድ የተገባ ሆኖ ተገኝቷልና ፤አዲሲቱ የክርስቶስ እስራኤል ቤተ ክርስቲያን
ልትመጣ ግድ ሆነ፡፡ አዎ! የአብርሃምን ዱካ የሚከተሉ ሁሉ መዳን የሆነላቸው የክርስቶስ እስራኤል ናቸው፡፡(ሉቃ.19፥8)፡፡ አዎ! ከእስራኤል ዘሥጋ ያልሆኑ በሌላ በረት ያሉ ለእርሱ ሊሆኑ
ይገባል፡፡(ዮሐ.10፥16)፡፡ አዎ! “ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው” እያሉ ነጭ ለብሰው የዘንባባ ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው
ይዘው በበጉ ፊት ቆመው በታላቅ ድምጽ ጮኸው የሚዘምሩቱ፤ ለቁጥር
የሚታክቱቱ፤ ከጥንት በኪዳኑ ተካፋይ ያልነበሩ፤ አሁን ግን የበጉ እስራኤል የሆኑቱ ናቸው!(ራዕ.7፥9)
በአዲስ ኪዳን የክርስቶስ እስራኤል የሆኑትም፤ እንዲሁ በብሉይ ኪዳን
የነበሩ እስራኤላውያን ከኖሩት አይነት የኃጢአት ኑሮ ራሳቸውን ሊጠብቁ ይገባቸዋል፡፡ በተለይ በልብ ወደዚህ አለም በመመለስ
የትኛዋም ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስና ከቃሉም ዘወር ያለች እንደሆነና ሌላ ድምጽን መስማት ከተለማመደች፤ የመንፈስ ቅዱስን
ድምጽ በመጥላት፤ ባለመታዘዝ ክርስቶስን ልትቃወም ትችላለች፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ በሚያሳዝን መልኩ ፍርድን በራሷ ታመጣለች፤ መንግስቱም
ከእርሷ ይወሰዳል፡፡
እስጢፋኖስ ጨክኖ የመሰከረው እውነት ይህን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን
የእግዚአብሔር ናት፡፡ በምንም አይነት መልኩ ከመለኮታዊ መገለጥ ራሷን በማራቅና በመለየት በሰዎችና በዓለማውያን መሪዎች ሀሳብ
በመስማማት ፊቷን ከሙሽራዋ ዘወር ካደረገች እስከፍጻሜዋ ትዋረዳለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን “መንፈስ ካልመላባት” “የቃሉም ሙላት
በውስጧ ከሌለ” (ኤፌ.5፥18፤ቆላ.3፥16) የእግዚአብሔር ኃይልና ኃለዎት በዙርያዋ እንዳለ አይሰማትም፡፡ ስለዚህም ቤተ
ክርስቲያን ወደልምላሜዋ ለመመለስ ፤እርሱን ጌታዋን ልትሰማ ፣ በሰውና በባዕለሥልጣናት ከመደገፍ ጣዖት አምልኮና ቃሉን
ባለመታዘዝ መንፈስ ቅዱስን ከመቃወም በመከልከል ወደሙሽርነት ክብሯ በውበትና በሽልማት በንስሐ በመመለስ እንደክርስቶስ እስራኤል
ልትሆን ይገባታል፡፡
“በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ” የተባለው ተግሳጽ እኛንም የማያገኘን
እልኸኛ ያልሆንን እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ እልኸኛነት በእግር ቢያስጉዝም በልብ አያደርስም፡፡ እልኸኛነት ከግብጽ ቢያስወጣም
ከኢየሩሳሌም አያደርስም፡፡ እግዚአብሔር ወደእረፍቱ ያላስገባቸው ልባቸውን እልኸኛ አድርገው፤ ድምጹን እየሰሙ በእልኸኛነት ጌታን
በማስመረራቸው ምክንያት ነው፡፡(ዕብ.3፥15፤4፥6)
እንኪያስ! የክርስቶስ እስራኤል ሆይ! የሚያበረታሽን ጌታሽን
አስቢው፡፡ እርሱ በድካምሽ የሚራራልሽ፣ በሚያስፈልግሽም ጊዜ የሚረዳሽን ፀጋ የሚሰጥሽ ታማኝ ሊቀ ካህንሽ ነውና በእምነት
ወደማይጎድል የጸጋው ዙፋን ፊት ቅረቢ፡፡
ጌታ ልባችንን ከክፉ መንገድ ይመልስልን፡፡አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment