እግዚአብሔር ሥልጣንን ለሰው ሁሉ
የሚሰጥ አምላክ ነው፡፡ ምክንያቱም “ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ
ናቸው።”(ሮሜ.13፥1) የሥልጣን መገኛው እግዚአብሔር ከሆነ ሥልጣንን የጨበጡ ወገኖች ቀዳሚ ተግባራቸው ደግሞ ህዝብ መምራታቸው
ሳይሆን እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ “እግዚአብሔርን መፍራታቸው ክፋትን ፤ ትዕቢትንና እብሪትን፤ ክፉንም መንገድ፤ ጠማማውንም
አፍ እንዲጠሉ ይረዳቸዋል።(ምሳ.8፥13)
በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሱት የሥልጣን እርከኖች መካከል መቶ አለቅነት አንዱ
ነው፡፡ የመቶ አለቃ በሥሩ መቶ ወታደሮችን የሚያዝዝ የሮማዊ ጦር መኰንን የማዕረግ ሥልጣን ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱት
ሮማውያን የመቶ አለቆች ደግሞ፤ አህዛባውያን ሆነው ካመኑት የተሻለ ህይወትና እምነት ይዘው ተገኝተዋል፡፡ ጌታ ቢረዳን እነዚህን
የመቶ አለቆች አንድ በአንድ እናያለን፡፡
1.
የቅፍርናሆሙ የመቶ አለቃ (ሉቃ.7፥1-11)
ጌታ ኢየሱስ በኪደተ እግሩ ተመላልሶ፤ ደጋግመሞ ያስተማረባትና ብዙ ተአምራት
ያደረገባት ከተማ ናት፤ ቅፍርናሆም፡፡ (ማር.2፥1-12፤ዮሐ.4፥46) ተዘዋውሮ ካስተማረ በኋላ ለጌታ ኢየሱስ መኖርያውም፤ ማረፊያውም
ነበረች፤ ቅፍርናሆም፡፡(ማቴ.4፥13-16) ቅዱስ ጴጥሮስ ያደገባት፤ ቅዱስ ማቴዎስም ከቀራጭነት የተጠራባት ከተማ ናት፡፡(ማር.1፥29፤ማቴ.9፥9)
ወደጌታ ዘወር ለማለት ይህ ሁሉ ዕድል የነበራት ቅፍርናሆም እንዳለመታደል በአለማመኗ ምክንያት የፍርድና የጥፋት ትንቢት ተነገረባት፡፡(ማቴ.11፥23)
ጌታ ወደዚህች ከተማ ሲገባ “አንድ የመቶ አለቃም ነበረ፤ የሚወደውም ባሪያው
ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር።”(ሉቃ.7፥2) ይህ የመቶ አለቃ የአህዛብ ባለሥልጣን ሆኖ የቤቱን ሠራተኛ ፤አገልጋይ ባርያውን አብዝቶ
የሚወድ ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ነን፣ “የህጉና የእግዚአብሔር ጠበቆች ነን” … የሚሉቱ “በገዛ ወገናቸው ላይ ለራሳቸው በጣታቸው
ሊነኩ የማይወዱትን ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ በሚጭኑበት”(ማቴ.23፥4) በዚያ ዘመን፤ ወገኑ ያልሆነውን ሠራተኛውን
በሰባራ ቀን የሚወድ የመቶ አለቃ ተገኘ፡፡
ዛሬም አገልጋይ ነን እያሉ የቤት ሠራተኞቻቸውን በግፍ የሚበድሉ፤ የሚያስጨንቁ፤
ደመ-ወዛቸውን አሰርተው የሚከለክሉና የሚነጥቁ … “በድኃው ያደረጉት ግፍ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።”(ያዕ›5፥4)
የሚለውን ቃል መዘንጋት የለብንም፡፡ ሐገራችን በዚህ ዙርያ በሚበዛ
ግፍ ተይዛ፤ ሠራተኞችን በጤንነታቸው ተገልግለን በህመማቸው ጊዜ ከቤተ ክርስቲያንና ከመንገድ ዳር መጣል የተለመደ ክስተት ሆኗል፡፡
የመቶ አለቃው ለአገልጋዩ የተጨነቀው በእውነት ከመውደዱ የተነሳ ነው፡፡ ስለኢየሱስ ሰምቶ ነበርና፤ ስለዚህም በጆሮው የሠማውን አሁን
በእምነት ሊገልጥና ሊያይ ወደደ፡፡
የምኩራብ አለቆች ያልሆኑ፤ በህዝቡ ዘንድ ተደማጭነት የነበራቸውንና የተከበሩትን
ሽማግሌዎች ወደኢየሱስ ልኮ፤ መጥቶ ባርያውን እንዲያድን ለመነው፡፡ የተላኩትም ሽማግሌዎች “ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል
ብለው አጽንተው ለመኑት።”(ሉቃ.7፥5) በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች አንዱና ትልቁ ህመማቸው በህይወት እያሉ መልካም የሚናገርላቸው
ማጣትም ይመስለኛል፡፡ እኛ ሀገር ሲሞቱ ማወደስ ወግና ልማድ ሆኗል፡፡ ለሞተው በቁሙ መልካም መናገር መሸነፍ እየመሰለን፤ በቁም
ያሉትን በሐሜት፤ ሥጋና ደማቸውን በልተን ጠጥተን ጨርሰናቸዋል፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ የሚሆን ወሬና ጥላቻ እንጂ ጸሎትና ምልጃ የለንም፡፡
ጌታ ኢየሱስ ይፈውሰን፡፡አሜን፡፡
ጌታ ኢየሱስ
ይህን ድንቅ ምስክርነት እንደሰማ ወደዚህ የመቶ አለቃ ቤት እግሩን አቀና፡፡ የመቶ አለቃው ጌታ ኢየሱስ ወደእርሱ እንዳቀና፤ ወደቤቱም
እንደቀረበ ባወቀ ጊዜ፦ “ጌታ ሆይ በቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝምና አትድከም፤ ስለዚህም ወደ አንተ ልመጣ እንዲገባኝ ሰውነቴን
አልቈጠርሁትም፤ ነገር ግን ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል። እኔ ደግሞ ከሌሎች በታች የምገዛ ሰው ነኝ፥ ከእኔም በታች ወታደሮች
አሉኝ፥ አንዱን፦ ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም፦ ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬን፦ ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል።”(ሉቃ.7፥6-9)
አለ፡፡
የመቶ አለቃው እንደመጥምቀ መለኰት (ማቴ.3፥11) ፍጹም የሆነ ትህትናን
የተላበሰ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ “እውቀትና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች” ዘንድ የማትገኝ ሀብት ትህትና ናት፡፡ በራስ ተማምኖና በትዕቢት ተነፍቶ
መናገር የተደባለቀብን የትህትና ድንበር ፍጹም ጠፍቶብን ነው፡፡ የመቶ
አለቃው ከትልቅ ትህትናው የተነሳም ጌታ ኢየሱስ ዘንድ በመቅረቡ ኃጢአተኝነቱን በማመን ተቀበለ፡፡ በእርግጥም፤ ያለጌታ ምህረትና
ይቅርታ ከቤታችን ጣርያ በታች ያለውን ነውርና በደል ማንም፤ የትኛውም ፍጡር ሊምርና ይቅር ሊል አይቻለውም፡፡ እጅግ የሚገርመው
ነጥብ! ትልቁ የሮም ባዕለ ሥልጣን እንደቀበሮ ጉድጓድ፤ እንደወፍ ማደርያ የሌለውን
ድኃውን “የአይሁድ መምህር”(ሉቃ.9፥58) ከቤቴ ጣርያ በታች ልትገባ አይገባህም ማለቱ!!! የሚደንቅ ትሁት ልብ!!!
ጌታ ኢየሱስ በዚህ ንግግሩ ተደነቀ፡፡ በወንጌላት ላይ ጌታ እንደተደነቀ
የተነገረው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ አንዱ በመቶ አለቃው እምነት ሲሆን ሁለተኛው ናዝሬታውያን እምነት በማጣት ባለማመናቸው ነበር፡፡(ማር.6፥6)
የመቶ አለቃው ኢየሱስ እርሱ በተጨነቀበት ነገር ላይ ሥልጣን እንዳለው ያውቅ ነበር፡፡ እርሱ ወታደሮቹን በማዘዝ “የወደደውን ማድረግ
እንደሚቻለው” ሁሉ በሥልጣን ቃል ጌታ ሁሉን እንደሚያደርግ ያምን ነበር፡፡ እምነቱ እንደሚፈውስ ብቻ ሳይሆን “ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም”
(መዝ.106(7)፥20) እንዲል ቃሉ እጅግ በሩቅም ቢሆን እንደሚፈውስ ያምን ነበር፡፡ ስለዚህም “ቃል ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።”
አለ፡፡ በእውነትም ይህ ቃል ከማያምን አህዛብ መስማት ይደንቃል!
ይህ የመቶ
አለቃ ከአብርሃም ቤት ለጠፉት ወደፊት በኢየሱስ አምነው ደህንነትን ለሚቀበሉ በሩቅ ላሉት በጎች(አረማውያን)ፈር ቀዳጅ ነው፡፡ ጌታ
ያደገባት የናዝሬት ሰዎችና ኢየሩሳሌም ሠላሳ አመት አብሯቸው የነበረውንና በየአመቱ እየመጣ በኢየሩሳሌም መቅደስ እንደኦሪት ህግ
መሥዋዕት እያቀረበ ሲያስተምር፣ ከሊቃውንቱ ጋር ሲጠይቁት እየመለሰ የነበረውን ጌታ አላመኑትም፡፡ ይደንቃል! ሙሴንና አብርሃምን አምነው፤ ኢየሱስን ግን ናቁት፡፡ ስለሙሴና ስለአብርሃም መስክረው፤
ነቢያትና ህግ የመሰከሩለትን ግን ካዱት፡፡ ዛሬም ይህ እየሆነ አይደለምን?
ጌታ ኢየሱስ ስለዚህ መቶ አለቃ በፍጻሜ እንዲህ አለ፦ “እላችኋለሁ፥
በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም አላቸው።” ጌታ ኢየሱስ “እምነትህ(ሽ) ታላቅ ነው” ብሎ በወንጌል የመሰከረላቸው
ሁለት ሰዎችን ብቻ ነው፡፡ አረማዊውን ይህን መቶ አለቃና አረማዊቷን ከነዓናዊት ሴት፡፡(ማቴ.15፥28) ሁለቱም ወገኖች ካመኑት
አይሁድ ይልቅ ትልቅ እምነት ተገኘባቸው፡፡ ወንጌል በትዕቢት የቀረቡትን
አይሁድ አርቃ፤ በታላቅ እምነታቸውን የቀረቡ አረማውያንን በትህትና ተቀበለቻቸው፡፡ ህግ፣መቅደስ፣ሥርዐት፣መሥዋዕት … አለን ያሉቱ
በያዙት ስላልታመኑ መርገፉን ብቻ ይዘው ቀሩ፡፡ ህግ፣መቅደስ፣ሥርዐት፣መሥዋዕት … የሌላቸው አህዛብ በእምነት ልብ ቀርበው፤ ከበጉ
ደም የተነሳ ነጭ ልብስ ለብሰው፤ በጽድቁ ጸድቀው ክብሩን ወረሱ፡፡ መቶ አለቃው “ጥቂት የእግዚአብሔር ቃል” ትልቅ እምነት አለው፡፡
እኛስ? ብዙ የእግዚአብሔር ቃል ግን ባዶ እምነት? ወይስ … ?
እንደየመቶ አለቃው ያለ እንዲህ እምነት፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛም ይሁንልን፡፡አሜን፡፡
ይቀጥላል …
kale hiwot yasemalin Amen!
ReplyDeleteቃለ ሕይወት ያሰማልን!!!
ReplyDelete