Monday, 14 July 2014

“በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ”(ሐዋ.7÷39) (ክፍል - 2)


v ሙሴ ከእግዚአብሔር “እርሱን ስሙት” የተባለለት ሰው ነበር፡፡ ምክንያቱም “ይሰጠን ዘንድ ህይወት ያላቸውን ቃላት የተቀበለ” ነውና፡፡(ሐዋ.7፥37-38) ነገር ግን “አባቶች” የነበሩቱ ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ይልቁንም ገፉት እንጂ፡፡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ፤ታናናሽና ታላላቅ አይሁድም ነቢያት የመሰከሩለትና አብ በድንቅ በተገለጠው የደብረ ታቦር መገለጡ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት…”(ማቴ.17፥5) ብሎ የተናገረና በሥጋ የወለደችው እናቱ ድንግል ማርያምም “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” በማለት የተናገረችለት ናት፡፡ነገር ግን ሙሴን ባለመታዘዝ እንደገፉት ሁሉ፤ ልጆች የተባሉቱም ክርስቶስ ኢየሱስን ብዙ ጊዜ ጠሉት፤ገፉት፤ሊገድሉትም ይፈልጉት ነበር፡፡(ዮሐ.5፥16)
    የእስራኤል ልጆች በዚያን ጊዜ በምድር ካሉት ሁሉ እጅግ ትሁት የነበረውን(ዘኁ.12፥3) ሙሴን  ባለመስማታቸው ካገኛቸውና ሙሴንም ካስቆጣው አንዱ ኃጢአት ክፉ ምኞት ነው፡፡(ዘኁ.11፥4፤10)፡፡ ክፉ ምኞታቸው ለገዛ መቃብራቸውና ለሞት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡(ዘኁ.11፥34)፡፡ ጲላጦስ፦ አይሁድና “…የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደሰጡት ያውቅ ነበር”(ማር.15፥6) ማወቅ ብቻ አይደለም ፤ “ኢየሱስን ግን ለፈቃዳቸው አሳልፎ የሰጠው”(ሉቃ.23፥25) መሪው ጲላጦስ ከአይሁድ ጋር የተባበረበት አንዱ መንገድ ክፉ መሻታቸውንና ሃሳባቸውን እያወቀ፤ ህግ ተላልፎ ለክፉ ምኞታቸው አሳልፎ መስጠቱ ነው፡፡ ይህ ድርጊት አይሁድን “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” እስኪሉ ዕውር አድርጓቸዋል፡፡(ማቴ.27፥25)

 ክፉ ምኞት ክርስቶስን አስክዶ ለገዛ ምኞታችን አሳልፎ የሚሰጥ የኃጢአት ሁሉ መሠረት ነው፡፡የህሊናችን በር ቃሉን በማጥናትና በጸሎት ካልተዘጋ፤ እግዚአብሔርን እያወቀ እንደእግዚአብሔርነቱ መጠን ካላከበረና ካላመሰገነ “… እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ይሰጠዋል፡፡”(ሮሜ.1፥21፤26) ሰው ከክፉ ምኞት የራቀ “በጎ ህሊና ከሌለውና ከጣለው መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ በእምነት ነገርም ይጠፋል፡፡”(1ጢሞ.1፥19) የዚህ ትውልድ ትልቁ አደጋም “ ባለ ጠጎች ሊሆኑ እየፈለጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም መውደቅ ነው።”(1ጢሞ.6፥9) “ትልልቆቹ” “business” እየተባሉ የሚሰሩት “ሥራዎች” የህጻናትን ጉልበት በመበዝበዝ፣የሴቶች እህቶቻችንን ገላ በመሸጥ፣በምዋርትና በድግምት ጥንቆላ፣በማጭበርበርና ሚዛንን በመስለብ … የሚገኙ ናቸው፡፡ እኒህ ሰዎች አህዛብ ብቻ ሳይሆኑ ክርስቲያን ተብለው የሚጠሩም ናቸው፡፡ ግና እነዚህ “ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን የወጉ ናቸው እንጂ ክርስቲያኖች ናቸው ማለት እጅግ በጣም ያስቸግራል፡፡(1ጢሞ.6፥10)

v የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር በተራራው የኪዳኑን ሰነድ ሊቀበል በዘገየ ጊዜ የሚበዙቱ የጥጃ ጣዖት አቁመው ፤መስዋዕትም አቅርበው፤በእጃቸው ሥራ ተደስተው ሲጨፍሩ ታይተዋል፡፡(ሐዋ.7፥41፤ዘጸ.32፥1-6)የእስራኤል ልጆች በመጀመርያ አይናቸውን ከእግዚአብሔር ማንሳታቸው ከባድ ስህተትና መናፍቅነት ነው፡፡የብዙ ክህደትና መናፍቅነት ምንጭ እግዚአብሔርን በህልውናውና በሁሉን ቻይነቱ ካለመረዳትና ካለማስተዋል የሚመነጩ ናቸው፡፡
   የገላትያ ቤተ ክርስቲያን የተነቀፈችበት ትልቁ ስህተቷ አይኖችዋን ከተሰቀለው ጌታ በማንሳት ወዳለመታዘዝ ሐሰተኝነት ስለገባች ነው፡፡መረዳት እየቻሉ በቸለተኝነት አዚም ተይዘው በፊታቸው እንደተሠቀለ ሆኖ ያለውን ጌታ ባለማስተዋል ዘነጋችው፡፡(ገላ.3፥1)
     “ለጌታ ተገዙ” (ሮሜ.12፥12) ተብለን ለትልቁ ጌታ ባንገዛ ቀጥሎ የሚገዛን “አስጨናቂ ጌታ” ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች “ይህ ከግብጽ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደሆነ አናውቅምና…” በማለት አይናቸውን ከእግዚአብሔር ላይ አንስተው ፍጡሩ ሙሴ ላይ አደረጉ፡፡ በድንቅና በግሩም ተአምራት ከግብጽ ተዋጊ ሆኖ ያወጣቸውንና “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው” ብለው ጮኸው የዘመሩለትን ጌታ “እርሱን ሙሴ ነው” አሉ፡፡(ዘጸ.15፥3፤ዘጸ.32፥1) የእግዚአብሔር የሆነውን ለፍጡር ሰጥቶ ማምለክ ጣዖት አምልኮ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ጳውሎስና በርናባስ እጅግ አድርገው ተቃውመውታል፡፡(ሐዋ.14፥14-18) አሮን የእስራኤል ልጆችን በጽኑ መምከርና መገሰጽ ነበረበት እንጂ መሪ ሆኖ ሳለ በእነርሱ ሊመራ አይገባውም ነበር፡፡ ስለዚህም “በፊታችን የሚሄዱ አማልክትን ሥራልን” ሲሉትም ተቀበላቸው፡፡
  ተዋረዱን አስተውሉ! ከእግዚአብሔር ወደሙሴ፣ከሙሴ ወደጥጃ፣ ጥጃውንም  “እስራኤል ሆይ፦ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክት ናቸው”(ዘጸ.32፥8) በማለት አይናቸውን ከእግዚአብሔር ላይ አንስተው የአማልክቱን የጣዖት በዓል “የእግዚአብሔር በአል ነው”ብለው አወጁ፡፡ከዚያም መስዋዕትን አቅርበው ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ሊዘፍኑም ተነሱ፡፡በእውነትም በግብጽ እንዳሉቱ ጣዖትን በማምለክ በእግዚብሔር አደባባይ በተራራው ፊት ለፊት ሆነው በልባቸው ወደግብጽ ተመለሱ፡፡
    ሰው አይኑን ከእግዚአብሔር ላይ ካነሳ ለገዛ ስሜቱ እንኳ የባርያ ያህል ይገዛል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የፈጣሪን ክብር ለፍጡር መስጠትና መገዛት ከባድ ጣዖት አምልኮ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቁ በእስጢፋኖስ ዘመን በባቢሎን የምርኮ ዘመን የነበረውን የጣዖት አምልኮ ልምምድ ወደሃገራቸው በማምጣት በዚያን ዘመን  በእስራኤል መካከል ጣኦት አምልኮ እጅጉን ተስፋፍቶ ነበር፡፡የመመለክ ያህል መከበር ደግሞ በጌታ ዘመን በግልጥ ይንጸባረቅ ነበር፡፡(ማቴ.23፥6) ከዚህ አልፎ ይህንን የመበለቶችንና የድሆችን ቤት ለመበዝበዝ ይጠቀሙበትም ነበር፡፡
    ዛሬ ላይ ከሚታዩት ታላላቅ ክህደቶች አንዱ ብዙ “አማኝ” የሚባሉ ሰዎች ከአግዚአብሔር ይልቅ የሚገዙለትና የሚያከብሩት የራሳቸው ነገር አላቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጌታ ፣ከኢየሱስ ውጪ መድኃኒት ፣ከደሙ ውጪ ሌላ የኃጢአት ማሥተሰረያ መንገድና አማራጭ መፈለግ ከባድ መናፍቅነት፤ጣዖት አምልኮም ነው፡፡ ዛሬም ይህን የሚያደርጉ ከግብጽ ርኩሰት ያልጸዱ ግና በቤቱ ያሉ ግብዝ “ክርስቲያኖች” ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ልጅ ከኢየሱስ ክርስቶስ ደም ውጪ የኃጢአት ማስተሥረያ መድሃኒትና ከእግዚአብሔር ውጪ በፍጡር መታመን መረገም፤ የፍጡርን ማዳን መፈለጉም የተከለከለ ነው፡፡(1ዮሐ.1፥7፤መዝ.146፥3) በፍጡር መመካት ከምንም አይቆጠርም፤ ማዳኑም ከንቱ ነው፡፡(ኢሳ.2፥22፤መዝ.60፥11)
  የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መናፍቃን ከሚታወቁባቸው ባህርያት መካከል አንዱ “ከእግዚአብሔር ቃልና እውነት ይልቅ ለመሪዎቻቸው መመሪያና አስተምህሮ የሚገዙና የሚታዘዙ መሆናቸው” እንደሆነ ያስተምሩናል፡፡ “የሊቀ ጳጳሳቸውን ቃል ከክርስቶስ መለኮታዊ ቃል ጋር እንደእኩል የሥልጣን ቃል የማይሳሳት ፍጹም አድርገው ቆጥረው፣ የመሪዎቻቸውን ትዕዛዝና መመሪያ ከእግዚአብሔር ቃል አብልጠው የሚያዩ፣ የሚቀበሉና ለሌሎች የሚሰብኩ …” ዛሬ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ በዝተዋል፡፡ ግን እግዚአብሔርና ቃሉ ብቻ የዘላለም እውነት ነው፡፡

v አባቶቻቸው መንፈስ ቅዱስን የሚቃወሙ ነበሩ፡፡(ሐዋ.7፥51) የእስራኤል ልጆችን ታሪክ ስናጠና ለብዙ ጊዜ ባለመታዘዝና ከእግዚአብሔር ለእነርሱ የተገለጠውን ቃሉን ተቃዋሚ ህዝቦች እንደነበሩ ነው፡፡ ሙሴ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ እንዳይረሱት የነገራቸውን የጌታን ህጎችና ትዕዛዛት (ዘዳግ.8፥1) ፈቀቅና ችላ ብለው በዙርያቸው ያሉትን አህዛብን እየተመለከቱ እግዚአብሔርን በከንቱ ጣዖት ያስመርሩት ነበር፡፡ ከሁሉ ይልቅ የመሲሁን መምጣት ተግተው ይነግሯቸው የነበሩትንና ንስሐ እንዲገቡ ይመክሯቸው ፤ይነግሯቸው የነበሩትን ታላላቆቹን ነቢያትን አሳደዱ፤ገደሉም፡፡(2ዜና.36፥17፤ማቴ.23፥31፤ሐዋ.7፥52)
   የጌታን ህጉን መቃወምና የመሲሁ የክርስቶስ ነገር ሲነገር የሚቆጣና የሚበሳጭ የትኛውም ዓይነት ሁኔታ እርሱ መንፈስ ቅዱስን ተቃዋሚ መንፈስ ነው፡፡ በክርስቶስ የተነገረው ቃል ሁሉ ከመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱ ቃሉን ለድሆች የሰበከው በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቶ ነው፡፡(ሉቃ.4፥18) ይህንን የእርሱን የመዳን ወንጌል የሚቃወም ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ተቃዋሚ ነው፡፡ዛሬ ላይ ስለክርስቶስ ሲነገር የሚጨማደድ ፊት ያላትን “ቤተ ክርስቲያን” ማየት ልብ የሚሰብር ህመም ነው!

ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን።(ኤፌ.6፥23)

ይቀጥላል …


2 comments:

  1. ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ደም አለም አይደንም!!!!!!!!!!!!!!!!!!ከደጀ እውነት ዘ ኦርቶዶክስ

    ReplyDelete
  2. ኢየሱስ ሲምጣ ጣዎታት መድረሻ አጡ!!!!!!!!!!!!!!!!!!!ከደጀእውነት ዘ ኦርተዶክስ

    ReplyDelete