ፈሪሳውያን ወንድማዊ መሪነትን ወደ አስፈሪ አለቃነት ለውጠውታል፡፡እኛንም እንደወንድም አለመተያየትና
አለመዋደዳችን የጎዳን ብቻ አይደለም፤ ብዙዎችን ያሰናከልንበትም ከባድ ኃጢአት ነው፡፡ጥቂት የማይባሉ
በአሜሪካ፣በአውሮፓ፣በካናዳና በሌሎችም የስደት ምድር ላይ ያሉት “አማኝ ተብለው” በጽዋና በጉባኤያት የሚሰባሰቡት በብሔር ተኮር
ስብስብ፤ ያውም ከኦሮሞ ወለጋና አርሲ፣ከአማራ ጎንደርና ጎጃም፤ከደቡብ ወላይታና ሲዳማ … በሚል ተከፋፍለው “በቤተ ክርስቲያን”
ሲሰበሰቡ ማየት የሚያመውን ያህል ምንም ህመም፤ከባድ ስቃይም የለም፡፡ እዚህ አይናችን ሥርም ያለው የሀገር ቤቱ የሚብስ እንጂ
የሚሻል ነገር የለውም፡፡በብዛት የአንድ ሀገረ ስብከትን ሥራ አስኪያጅ ወይም ጳጳስ ዘርና ወንዝ ቆጥረው የሚሰባሰቡትን የቄስና
የዲያቆን መንጋ ማየት እንግዳ አይደለም፡፡ሥር የሰደደው የዘረኝነታችን ዘር የእግዚአብሔር ነፍስ አብዝታ የምትጠየፈውን
በወንድማማች መካከል ጠብ መዝራትን እንኳ ረስተነዋል፡፡(ምሳ.6፥19)
አገልጋይ ግን እንዲህ ያለውን ነገር ሊያጠራ፤ እንደወንድም በቅርብ ሊመራ እንጂ አለቃ ሆኖ ሊያዝ አልተጠራም፡፡
ስለዚህ ፈሪሳውያን አለልክ ክብርን ሽተዋልና ፍፁም ወቀሳቸው፡፡ አለመታደል ሆኖ እንጂ አለቅነት ከወንድምነት አይበልጥም፡፡
ወደሌላ ከምትተላለፍ ህልቅናና ሹመት ይልቅ ለዘለዓለም አብሮን የሚኖረው ወንድምነት ትልቅ ክብር አለው፡፡
ወንድም ገመና ሸፋኝ ነው፤ ወንድም የገዛ ወንድሙን ገመና ለማይራራ ባዕድ አሳልፎ አይሰጥም፡፡ወንድማማችነት በደም ተሳስሯልና
እስከመከዳዳት በሚያደርስ ክፋት አይያዝም፡፡ አዕምሮው ካልጎደለው በቀር ወንድም ወንድሙን “ወንድሜ አይደለህም” ብሎ ለመካድ
አቅም አይኖረውም፡፡ወንድምነትን የሚክድ እርሱ ነው እንጂ ከዳተኛ ፤ወንድምነቱ ፈጽሞ የሚሻር አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ
ወንድማችነትን ክደን ስንነካከስ፣ስንበላላ፣ስንጠፋፋ … ዓለም እንኳ ታዝባናለች፤ የስድብ ምክንያትም ሆነናል፡፡
መንፈሳዊነቱ ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ተጨባጭ የመሪዎችና የህዝቡን ቅርርቦሽ ስናይም እጅግ የመረረ ነው፤ዛሬም መሪ የሚባሉቱ
በወንድምነት መንፈስ ህዝብን ማገልገል የሚቀፋቸውን ያህል ሌላ ነገር የሚቀፋቸው ያለ አይመስለኝም፡፡
ለምን እንደሆን ለራሴ ግራ ይገባኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ከሚያገለግሉኝ ወንድሞቼ መካከል ብዙዎቹ ትህትና የሚጎድላቸው ብቻ አይደሉም፤
እንደወንድም የማያቀርቡም ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሲነገራቸው እንኳ ለመስማት ዝግጁ አለመሆናቸው ነው፡፡ … ግን ከሁሉ በላይ
በአማኑኤል የተዛመድን ወንድማማቾች ከደም ይልቅ በህያውና ለዘላለም በሚኖር፤ ከማይጠፋው ዘር በመወለድ አንድ የሆንን
ነን፡፡እንኪያስ ከሥጋ ወንድምነት በሚልቅ የወንድማማች ፍቅር ልንዋደድ፣ልንከባበር፣ገመና ልንሸፋፈን፣ ሳንሸነጋገል በምክር ቃል
በግልጥ ልንነጋገር፣ልንተያይ … በእውነት ይገባናል፡፡
የወንድምነት እውነት ያልገባው አገልጋይ ሥልጣን ቢሰጠው መግዛትና መንዳት እንጂ ዝቅ ብሎ ማገልገል አይሆንለትም፡፡ ማዘዝ
ወደከፍታ አያወጣም፤ መታዘዝ እንጂ ወደክብር ሰገነት ይመራል፡፡ ፈሪሳውያን ከእነርሱ የተሻለ ሰው እንኳ እንዳለ አላሰቡምና፥
ከህዝቡ በክብር የማይጠራቸውን ፤ሠላምታ እየሰጠ፤ ፀጥ ለጥ ብሎ የማይገዛላቸውን ያወግዙት፤ ያገልሉትም ነበር፡፡ (ዮሐ
10፤34)
በአንድ ወቅት አንድ ወዳጄ ጉባኤ እንዲያስተምር ተጋብዞ የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊውን
“ወንድማችን” ብሎ በመጥራቱ ምክንያት “እንደጋለሞታ ሴት ስሜን ዘንጥለህ ጠርተሃልና ከእንግዲህ መጥተህ
እንዳታስተምር” ተብሎ መባረሩን ነገረኝ፡፡ በሌላ ጊዜ በቅዳሴ ላይ የደብሩን “አለቃ” ስም “አባታችን”
በማለቱ በትክክል አልጠራህም ተብሎ ደመወዙን የተቀጣ ወዳጄንም አስታወሳለሁ፡፡ እንዲህ ያሉ እጅግ አስነዋሪ
ነገሮችን መስማትን ጆሮዐችን ለምዶታል፡፡
እኛ
እኮ “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች የሆንን” (ኤፌ.2፥19)
“የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፥ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ
በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ”(1ጴጥ.5፥2-4) ተብለናልና፤
በአለቃና ሎሌ ይትበሐል ያሻንን ልናደርግ አልተጠራንም፡፡ በተለይ አንዳንድ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ ካህናት፣ሰባክያን፣
ዘማርያን … ጎንበስ ተብሎ እግራቸው ካልተሳመ ፤ ካልተሰገደላቸው ፤ ጉልበታቸው በርከክ ተብሎ ካልታቀፈ
... ባልንጀራ ወንድማቸውን ለማናገር እንኳ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡
የነገስታቱ
ወግ በነበረበት ዘመን ጪሰኛው ገበሬ ለመኳንንቱ ለመሳፍንቱ፤ ለአቅራቢያው ሹማምንት ለጥ ብሎ ይሰግድ፣
ጫማቸውንም ይስም፤ ለንጉሱ ደግሞ ነጠላውን አንጥፎ እስከማምለክ የደረሰ እንደነበር ታሪክ
ያስነበበን የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ዛሬም ግን ይኸንኑ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ስናይ ህሊናችን
ያደማል፡፡ በጋርድ /በጠባቂ/ የሚንቀሳቀስ ሰባኪና ዘማሪ፣ ካልተሰገደለት የማያቀርብ ቆሞስና ጳጳስ፣ ለበዐልና ለንግስ
እንጂ የማይታዩ የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎችን፣ የወጡበትንና ለትልቅ ቁም ነገር ያበቃቸውን
ማህበረሰብ ተጠይፈው፤ ከማድመጥ ችላ ብለው አምባገነን የሆኑ የዚህ ዘመን “የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ” የሰባኪ መኳንንት፣
የዘማሪ መሳፍንት፣ የመጋቢ ደጃዝማች፣ የወንጌላዊ ግራዝማቾችን፣ የጳጳሳትን ነገስታት … “ወንድማማች ነን! “ያ ታች” ያለው
አስራት ከፋይ ምዕመን ወንድማችሁ ነውና ስሙት!!!” ብንል ይሰሙን ይሆን? እላለሁ፡፡
ወደክፍለ
ሀገር ለአገልግሎት ስትወጡ ለእንግድነት የምትመርጡት ሶፋና ምንጣፍ የተደረደረበት የነውረኛውንና የስም ክርስቲያን የባዕለጠጋውን
ቤት ወይስ ህይወቱን ለክርስቶስ የሰጠውን “የድኃውን” ወንድማችሁ ቤት ነው? አላስተዋልንም እንጂ ሁላችንም የታላቁ ወንድማችን
የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ነን!!! ጵጵስና ፣ቁምስና ፣ቅስና ፣ሰባኪነት፣መጋቢነት፣ነቢይነት፣ዘማሪነት … ሰውነት ላይ እንዳሉ
የተለያዩ የአካል ብልቶች በእድገት ሂደት ውስጥ እርስ በእርስ የሚረዳዱ፤ የማይበላለጡ ናቸው፡፡አዎ! ያለአንዱ አገልግሎት
የሌላው አገልግሎት ባዶ ነው፡፡
ከሁሉ
የሚልቀው ግን ወንድምነት ይኸውም አማኝ ከእምነት የተነሳ የልጅነት መብት በማግኘት በልዩ ክብር የተሾመ፤ በዚህም ብቻ ወራሽም
የሆነ ነው፡፡(ገላ.3፥29፤ሮሜ.8፥14) በደሙ ለእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ለጌታ ኢየሱስ ደግሞ በፍጹም ሰውነቱ በኩል ወንድሞች
ሆነናል፡፡ አገልጋይ የሆንነው ይህን ትልቅ መዳን በማክበር በፍቅር እንደልጆች ልንታዘዝ እንጂ እንደክፉው ጌታ ማዘዝ መናዘዝ
ቢያምረን፣ማቃለልና በረብ በጥቅም ማገልገል ብንጀምር፣በትዕቢት ተነፍተን ካልሰገዱልን ካላጎነበሱልን የምንል ከሆነ “የእረኞች አለቃ
በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል አይሰጠንም”፤ ድንቅና ብዙ ተአምራት በስሙ ብናደርግም ፈጽሞም
አያውቀንም፡፡ (1ጴጥ.5፥4 ፤ማቴ.7፥23፤25፥50)
በጌታ የምንገዛቸውን ምዕመናን ልናስጨንቅ ፤በአመጻ ልናዝ የምናስብ ከሆነ ከጥንት የሮማና የግሪክ አማልክትን ሲከተሉና
የራሳቸውንም ምስል አቁመው ያሰግዱ ፤ ይህንን ባለማድረግ የተቃወሙትን በጊዜው የነበሩ ክርስቲያኖችን ሲያስጨንቁ ከነበሩት
አላውያን ነገስታት በምንም አንሻልም!!! የቦታና የዘመን ልዩነት እንጂ የካልሰገዳችሁልኝ የሀሳብ ልዩነት የለንምና፡፡
“ሁላችን
ወንድማማች ነን፡፡” ስንል አገልጋይ አያስፈልገንም፤ክብር አይገባውም ወደሚል “የዋህ ትርጉም” እንደማይተጎም አምናለሁ፡፡ አዎ!
ወንድማማች ነን! ከወንድምነት የበለጠ ሌላ ክብር የለምና “ክብር የምንቀበል አገልጋዮች” ስንወደስ አሜን፣ ሲሰገድልን
እሰይ፣ጫማችን ሲሳም ይሁን፣አባ መምህር ስንባል ልባችንና ፊታችን እየሳቀ በመቀበል ሰማያዊ ዋጋችንን አናሳንሰው! ይልቁን
አገልግሎቱን በተመለከተ የሚመጣውን ክብር ወደታላቁ ወንድም ወደጌታ እንጂ ወደእኛ እንዳይመጣ በጭንቅ ልናስተው፤ ልንከለክልም
ይገባናል፡፡(ሐዋ.14፥18)
እንኪያስ፦ “በወንድማማች መዋደድ
እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፡፡”(ሮሜ.12፥10)
“ለእውነት እየታዘዛችሁ ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችሁን አንጽታችሁ
እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”(1ጴጥ.1፥22)
አዎ! ደስ ይበለን ፤
ሁላችን ወንድማማች ነን ፤እንዲህ ልንዋደድ ይገባናል!!!
ምስጋና፣ውዳሴ፣እልልታ
ዘመዳችን ለሚሆን ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን፡፡አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment