Tuesday 2 July 2024

ጌታ ኦርቶዶክስን በወንጌል ሊጎበኝ እያሰበ ቢኾንስ?

Please read in PDF

“የስብከተ ወንጌል”ና “የመንፈስ ቅዱስ ቀን”

በኹለቱ ተቋማት ዕይታ!

በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማርቆስ አማካኝነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰኔ 24ን “የስብከተ ወንጌል” ቀን ብላ ሰይማለች፤ ዓላማውንም ጳጳሱ እንዲህ ብለው ያስረዳሉ፣ “የስብከተ ወንጌል ቀን ሲባል ስብከተ ወንጌል የሌለበት ቀን የለም። የወንጌልን ቀን ማክበር የተፈለገበት ዕውቅናን ለመስጠት ነው፤ ይበልጥ በትውልዱ አእምሮ … ዛሬ የወንጌል ቀን ብሎ እንዲያዘክረው እንዲያከብረው … ሕፃናት ጭምር እንዲያውቁት ነው ትልቁ ዓላማው።” መሪ ቃሉም፣ “በወንጌል ተልእኮ ትውልዱን መታደግ” የሚል እንደ ኾነ ተጠቅሶአል።




በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ ሊቀ ጳጳስ በኾኑት አቡነ ማርቆስ የተለቀቀው አጭር ጽሑፍ በሚገባ የተብራራ ነውና ሳልጨምርና ሳልቀንስ፤ እንዲህ አስቀምጠዋለኹ።

“ወንጌል ዜና ሠናይ ዜና ሕይወት ለፍጥረት ሁሉ የምሥራች ቃል ስለሆነ ለክርስቲያናዊ ሕይወታችን ሁለንተናዊ ምንጭና መሠረት መሆኑን ሲያበሥረን ቅዱስ ያሬድ “በወንጌል ኮነ ሕይወትነ” “ሕይወታችን በወንጌል ሆነ”

በወንጌል ብርሃን ተገለጠ፤ በወንጌል ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ተቀዳጀ፤ በወንጌል የመንግሥተ ሰማያት ዜግነትን፤ የልጅነት ሥልጣንን አገኘ ይለናል። ወንጌል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውና ስለ ርሱ ቅዱሳን ሐዋርያት ያስተማሩት የሕይወት ቃል ነው። ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር ኾነን ስለ ወንጌል ኹሉን እናደርጋለን (1ቆሮ. 9፥23) እንላለን። ከቅዱስ ዮሐንስም ጋር በወንጌል የተገለጠውን ሕይወት እየመከርን ዘመኑን በመዋጀት ለዘመናችን ተደራሽ እናደርጋለን (1ዮሐ.1፥1-3)።

ዓላማው

ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የስብከተ ወንጌል ቀንን ለማክበር የተነሳበት ዋና ዓላማው የቅድስት ቤተ ከርስቲያናችን ኅልውና የኾነው የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን ዘመኑን በዋጀ መልክ ማሳለጥ፤ ለተልእኮው ተነሳሽነትን በመፍጠር ትውልዱን መዋጀትና በእግዚአብሔር ቃል መቅረጽ ነው። ስለኾነም አምላኩን የሚፈራ፤ ሃይማኖቱን የሚጠብቅ፤ ባህሉን የሚያከብር፤ ሀገሩን የሚወድ ዜጋን ለመፍጠር ዘመናትን የተሻገረ ብቸኛው መንገድ የእግዚአብሔር ቃል መኾኑ አያጠያይቅም። ቅዱስ ጴጥሮስ “... ለመዳን በርሱ እንድታድጉ አኹን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ” (1ጴጥ. 2፥2-3) በማለት ለትውልዱ መልካም ዕድገት ምን እንደ ኾነ ይነግረናል።

አስፈላጊነቱ

ስብከተ ወንጌል የእግዚአብሔር መንግሥት የምሥራች መልካም ዜና ከመኾኑ አንጻር በዘርፈ ብዙ ተግዳሮት ወስጥ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ማጽናትና ማጽናናት፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው የእምነትና የመንፈስ ትሥሥር እንዲጠነክር በማድረግ የሰባክያንን ሐዋርያዊና ሥነ ልቦናዊ አንድነት በመገንባት ትውልዱን በሰላም ወንጌል መሥራት የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ በመኾኑ ነው።

ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጣትን ሐዋርያዊ ተልእኮ ተቀዳሚ ተግባር በመኾኑ ወቅታዊ ተግዳሮቶችንና ፈተናዎችን በመቋቋም ዘመኑን የዋጀ እና ሰው ተኰር የኾነ የእግዚአብሔርን ቃል ተደራሽ ማድረግ ከምንም ጊዜውም በላይ ጊዜው የሚጠይቀው ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በጻፈው መልእክቱ “ወኢንኅድግ ማኅበረነ መሰብሰባችንን አንተው” (ዕብ. 10፥25) በማለት ያስጠነቅቀናል።

የተልእኮው ግብ

“ዘመኑን የዋጀ የወንጌል ተደራሽነትን እውን ለማድረግና የሰውን ልጅ ኹሉ ለእግዚአብሔር መንግሥት ለማብቃት ጥቅል መርሆቹ ኹለት ናቸው (1) እውቀት (2) ሕይወት ነው። የእነዚህን ተቀዳሚነትና አስፈላጊነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፤ እውነተኛ አምላክ ብቻ የኾንህ አንተን የላከኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት (ዮሐ. 17፥3)። …”

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በዚህ ልክ ወንጌልን ለመዘከርና ብሎም ለትውልዱ ችግር ዋና መፍትሔ መኾኑን በመረዳት መነሳሳትዋ እጅግ አስደናቂ ነው፤ ሊወደድ ሊመሰገን የሚገባ ተግባር ነው። ጌታ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን በወንጌል የመወረስን ዘመን እንዲያመጣ እጅግ በብዙ የምንማልድ፤ የምንናፍቀውም ነውና።

ከዚህ በተቃራኒ ግን የተሰጣቸውን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ጥለውና ገሸሽ አድርገው፤ አንዴ በኢሊሊ ሲላቸው ደግሞ በስካይ ላይት ሆቴል፣ በመሰብሰብ “የመንፈስ ቅዱስ ቀን” ብሔራዊ በአል ይኹን ለሚሉና ለሚታትሩትም እጅግ እደነቃለሁ። ከኦርቶዶክስ ጋር የበአል ሽሚያ ፉክክር የስንፍና በትር ይመስለኛል፤ ኦርቶዶክስ ወደ ወንጌል ልሂድ እያለች፣ “ወንጌላውያንን” ወደ በአል የሚመራቸው ምን የሚሉት “አዚም” ነው? ጌታ ምድራችንን ለእውነተኛ ወንጌልና መከሩን በጥንቃቄና ለጌታ ክብር፤ ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ በበጉ ደም የሚያፈልሱ የመከሩ ሠራተኞችን ያብዛ፤ አሜን። 

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)`


 

2 comments:

  1. እግዚአብሔር በድርብ ፀጋ ይባርክህ

    ReplyDelete
  2. አምላኬ እንደ ባለጠግነቱ መጠን ይባርክህ።

    ReplyDelete