Wednesday 31 July 2024

ለእውነተኛ ተሐድሶ ኦርቶዶክስን አይጠቅማትም!

 Please read in PDF

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተደረጉ “ፖለቲካዊ የቤተ ክርስቲያን ውሳኔዎች” አንዱ፣ ሰዎች በቋንቋቸው ወንጌል ሊማሩ ይገባል የሚል ነበር፤ በዚህ ዐሳብ ከቀድሞ ዘመን ጀምሮ “በወንጌል ልብ” በተደጋጋሚ ይጠይቁ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ በመኾኔ፣ በጥያቄው ፍጹም እስማማለኹ። ነገር ግን መልሱ የተሰጠውና በተግባር ላይ የዋለው ፍጹም መንፈሳዊ ባልኾነ መንገድ ባለ መኾኑ ሳዝን ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት እጽናናለኹ!


ሰዎች በቋንቋቸው ወንጌልን መስማት አለባቸው ስንል ግን፣ ከወንጌል የሚያደናቅፏቸው ነገሮች ኹሉ ሊወገዱ ይገባል ማለታችንን መዘንጋት የለብንም። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለወንጌል እንቅፋት ከኾኑት ነገሮች መካከል አንዱ ወንጌልን የሚጋርዱ አያሌ ጽሑፎችና ድርሳናት ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል አንዱ ደግሞ ተአምረ ማርያም ነው!

ተአምረ ማርያም በውስጡ ከመጽሐፍ ቅዱሷ ማርያም በተቃራኒ ኹኔታ፣ ማርያም ለተባለች አንዲት ሴት “ልዕለ ሃያል ኃይልን” በማላበስ፣ የኹሉ አድራጊና “ፈጣሪ” አድርጎ የሚያቀርባት እጅግ አሳዛኝ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ያሉትን አስነዋሪ ኹለት ተግባራት ልጥቀስ፣

·        “የእመቤታችንን ቃልኪዳንና ተአምር የሚንቁ የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መኾን ከማመን የወጡ ናቸው። ከክርስቶስ ወገኖች ከምእመናንም ጋር አይቆጠሩም።” (ተአምረ ማርያም መቅድም ገጽ 13 ቁጥር 4 እና 5) ብሎ በመናገር፣ በቅዱሳት መጻሕፍት የበዛውንና እጅግ የተትረፈረፈውን ትምህርተ ሥጋዌን ወይም በክርስቶስ ሰውነት ፍጹም ማመንን ከማርያም ተአምር ጋር በማተካከል ያልኮሰኩሰዋል፤

·        እንደ ደቂቀ እስጢፋኖስ ያሉትን ወንጌልን የሰበኩ ሰዎች መገደላቸው ትክክል እንደ ኾነ በማስቀመጥና የማርያም ተአምር ነው በማለት፣ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሟችሁን መርቁ …” በሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ ይሳለቃል!

እናም ይህ መጽሐፍ ዛሬ በኦሮሚኛ ቋንቋ መታተሙንና መመረቁን ሰማን፤ እጅግ ያሳዝናል።

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትን(መጽሐፍ ቅዱስን) በብዙ ቋንቋዎች መተርጎም፤ ማሳተምና ማባዛት ሲገባት፣ እንዲህ ያሉ ወንጌል የሚጋርዱ መጻሕፍትን በመተርጎም የትውልዱን ልብ እንደገና በማጨለም መትጋትዋ በድጋሚ እላለኹ፤ ያሳዝናል። ተአምረ ማርያም ለወንጌልና ለቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ በተቃራኒ የቆመና የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የማያከብር መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መልካሙንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ተሐድሶ እንዲያደርግ እጅግ ጥልቅ መሻቴና ጥማቴ ነው!

 “በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)`

No comments:

Post a Comment