Friday 5 July 2024

ወርቅ ሲደብስ!

 

ጳጳሱ ቅዱሳት መጻሕፍትን አላነበቡምን?

ጳጳሱ ለማርያም ያላቸው አስተምኅሮ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒ የቆመ ነው፤ እንዲህ ያለ ነገር በርግጥ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ “የታወቁ መምህራን” የሚናገሩት ነው፤ ከዚህ ቀደም ዲያቆን ኃይሌ፣ “እመቤታችን ማማለድ አይደለም አፍርሳን መሥራት ትችላለች” ብሎ መናገሩንና ለዚህም ምላሽ መስጠታችን ይታወሳል፡፡ ለምን ኾን ብለው ማርያምን በማግነንና በማስመለክ፣ እግዚአብሔርንና ስሙን መሳደብ እንደሚፈልጉ አላውቅም፤ እግዚአብሔርንና እግዚአብሔር በልጁና በመንፈሱ የሠራውን ሥራ ባለማወቃቸውም እጅግ እደነቃለሁ!

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኤጲስ ቆጶስ መኾን ስላለበት አገልጋይ ሲናገር፣ “እንደ እግዚአብሔር መጋቢ … ለማስተማር የሚበቃ፥” (ቲቶ 1፥7፤ 1ጢሞ. 3፥2) ይላል፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጳጳሳት ለዚህ ታላቅ የጌታ ቃል አለመታደላቸውን ሳስብ ከልብ አዝናለሁ፡፡ ከዚህ የተነሣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የተናገሩትን ሥራ ላይ ልናውል ይገባናል፤ እንዲህ ብለዋል፦

“ጌታችን እንደ ተናገረ መምሕራን የሚያስተምሩን ትምሕርት ከወንጌል ቃል ጋራ መስማማቱን እየመረመርን እንቀበላቸዋለን፡፡ ስለ ሥራቸው ግን በግድ ፍለጋቸውን ለመከተል አልታዘዝንምና የእነርሱን ፍለጋ ትተን የጌታችንን ፍለጋ እከተላለን፡፡ (ማቴ. ፳፫፥፫)”[1]

በርግጥም ጳጳሱ የተናገሩት ቃል የወንጌል ቃል ተቃራኒ ነውና አንቀበላቸውም፤ ድንግል ማርያም ባትኖር እግዚአብሔርም ክርስቶስም የሉም ብለን ጽርፈትን አንናገርም! እግዚአብሔር እንደ ወደደ የሚሠራ፣ ልዑልና ኃያል ጌታ ነውና እንዲህ እናምነዋለን!

ሊቀ ሥልጣናት ሀ/ማርያም ወርቅነህ፣ ስለ ክርስቲያናዊ ስብከት በተናገሩት መጽሐፋቸው፣

“ለስብከት ሳይዘጋጁ መቅረብ በአንድ በኩል ምእመኑን መናቅ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ እርሱ ኃላፊነቱን ዘንግቶታል፤ ሥራውን አቅልሎታል ማለት ነው፡፡”[2]

ይላሉ፡፡ በርግጥ ጳጳሱ ጳጳስ ስለ ኾኑ ብቻ ተናገሩ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጥንቅቅ ብለው ተዘጋጅተው ጠቅሰው አላስተማሩም፤ ይህ ደግሞ ምእመኑን ከመናቅ በዘለለ ከባድ ነውርም ነው!

ሊቀ ሥልጣናት በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፣

“የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን የምናድሰውና የምናንጸው በእጃችን ሳይኾን በልሳናችን ነው፤ ማለት በስብከታችን ነው፤ እንግዲያውስ ስብከት የማነጽ ጠባይ ያለው ስለሆነ አለመስበክ ደግሞ በተቃራኒው ማፍረስ መሆኑ ነው፡፡ … ከዚህም ጋር በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራ የእግዚአብሔርም ጸጋ የተሰጠው ሰው እንዲሆን ያስፈልጋል፤ እንዲሁም በንቃት፤ በትጋት የሚያስተምር በነገሩም አምኖበት በግለት የሚያስተምር ካህን መሆን አለበት፡፡”[3]

እንኪያስ እንዲህ ከባድ የስህተት ትምህርት ያለበትን ትምህርት ያስተማሩበትን ጳጳስ፣ ንስሐ እንዲገቡ አልያም ደግሞ ለዚህ የስህተት ትምህርት ማስተካከያ እንዲሰጡና እንዲቆጠቡ በቅዱሱ በእግዚአብሔር ቃል እንማጸናለን! ወርቁ ግን ለምን ደበሰ?!

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)`



[1] ኅሩይ ወልደ ሥላሴ(ብላቴን ጌታ)፤ ጎህ ጽባሕ፤ 1919 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ጎሐ ጽባህ፤ ገጽ 146

[2] ሊቀ ሥልጣናት ሀ/ማርያም ወርቅነህ፤ የስብከት ዘዴ፤ 1980 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ 9

[3] ዝኒ ከማኹ ገጽ 16

2 comments:


  1. የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር በቁጥር ጠቅሶ ለበአል ያልሰገዱትን ቅሬታዎች እንዳሉት ይናገራል በዚህም ዘመን እንደ አንተ ሌሎችንም እግዚአብሔር ቅሬታዎች ስላደረጋችሁ እግዚአብሔር ን በጣም አድርጌ አመሠግናለሁ

    ReplyDelete
  2. በጣም ነው የምወድህ ወንድሜ ዘመንህ የበረከት ይሁን፣ ፀጋ ይጨመርልህ፣ እስከ ህይወትህ ፍፃሜ ምህረቱ ትደግፍህ። አትያዝ በኢየሱስ ደም ተሸፈን።

    ReplyDelete