Friday 19 July 2024

ስለ ኦርቶዶክስ በልቤ ያለ ብዙ ኀዘን የማያቋርጥም ጭንቀት!

 Please read in PDF

ከልጅነቴ ያደግኹት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነው፤ የተጠመቅኹት፤ የቆረብኹት፤ በቅንአትና በትጋት ያገለገልኹት … በዚያ ነው። በዚያ የነበረኝ አገልግሎት በዕውቀትም በቅናትም እንደ ነበር ብዙዎች ምስክሮቼ ናቸው። የክብሩንና የትንሣኤውን ወንጌል በትክክል ስረዳና ስመሰክር ግን ብዙዎች ተቃወሙኝ፤ እናም አብረኸን ልትኾን አይገባም ሲሉኝና ሲገፉኝ ወጣኹ።

ብወጣም ግን ዛሬም ድረስ መሻቴ፤ ናፍቆቴ፤ ጥማቴ፤ በልቤ ያለው ብዙ ኀዘንና የማያቋርጥ ጭንቀቴ … ይህ ነው፤ እርሱም፦    

  1. የተሰቀለውን ክርስቶስን ከፍ አድርጋ በቀጥታ እንድትሰብከው! ክርስቶስን ብቻ የሚሰብኩ የማይሰደዱባት ቤት እንድትኾንና የክርስቶስን መሥዋዕታዊ ሞቱን፣ መቀበሩንና ትንሣኤውን የሚጋርዱ ትምህርቶች ፈጽሞ እንዲወገዱና የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ልቆና ገንኖ እንዲታይ፣
  2. መጽሐፍ ቅዱስን “የእግዚአብሔር እስትንፋስ”ና የእግዚአብሔር ሥልጣን ያለበት ቅዱስ ቃል እንደ ኾነ እንድትቀበል፤ ኹሉም መጻሕፍቶቿ (ድርሳኑ፣ ተአምሩ፣ ነገሩ፣ ገድሉ፣ ዚቁ፣ መልክዑ፣ ኪዳኑ፣ ቅዳሴው፣ አንድምታው፣ ሰዓታቱ …) በቅዱሳት መጻሕፍት ተዳኝተው እንደ ቅዱስ ቃሉ የኾኑት ብቻ እዲቀሩ ሌሎቹ ወደ ሙዝየም እንዲገቡ፣
  3. ይህን ኹሉ ቀሳውስትና ዲያቆናት ያላት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢየሱስ ልብ እንድታይና ለሕዝቧ ራርታ፤ በዙሪያዋ ላሉ (ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ የመንና ሌሎችም አገራት) ለሐዋርያዊ ተልእኮ አገልጋዮችዋን የምታሰማራ፤ የምትልክ እንድትኾን፣
  4. የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ በንቃትና በብቃት በመስማት፣ በመቀበል፣ በማደግደግ የታዘዘች ትኾን ዘንድ፣
  5. ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ልጆችዋ ተዋጅተው ለታረደውና ለቆመው በግ ብቻ ይገባሃል እያሉ ሲሰግዱና ሲዘምሩ ብመለከትና የዚያን ቀን ብሞት ደስታዬ ወደር የለውም!

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታረደውንና የቆመውን በግ፤ በጽዮን ተራራ በድል ከተማ በግርማ ያለውን በግ ያየችውና አይታውም ፈዝዛ የቀረች ቀን ቀናትን ኹሉ ለርሱ ትዋጃለች፣ ስግደትን ኹሉ ፍግም ብላ ለርሱ ብቻ ትሰግዳለች፤ ማራን አታዋ እርሱ ብቻ ይኾናል፤ እምነትዋም ሥራዋም የታረደው በግ ወንጌል አዋጅ ይኾናል።

ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ምጤ ይህ ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለገዛ ወገኖቹ ክርስቶስን ለሰቀሉት አይሁድ እንዲህ ከተመኘ፤ ክርስቶስን ለኢትዮጵያ፤ ወንጌልን ለምድራችን ያቆየችው ቤተ ክርስቲያን ተስፋ የላትም ብዬ የስንፍና ቃል አልናገርም፤ ጌታ እግዚአብሔር የአባ ሰላማንና የደቂቀ እስጢፋኖስን ወንጌልና እውነት በኦርቶዶክስ ቤት እንደገና እስኪያመጣ ልቅሶዬን አልተውም፤ መማጠኔን አላቋርጥም፤ ናፍቆቴ አይበርድም፤ ጌታ አንድ ቀን በኔ ዘመን ባይኾን በልጆቼ ዘመን ጉብኝት ያደርጋል!

3 comments:

  1. የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር በቁጥር ጠቅሶ ለበአል ያልሰገዱትን ቅሬታዎች እንዳሉት ይናገራል በዚህም ዘመን እንደ አንተ : ህሊና ዳዊት እናም ሌሎችን እግዚአብሔር ቅሬታዎች ስላደረጋችሁ እግዚአብሔር ን በጣም አድርጌ አመሠግናለሁ ዘመናችሁ በእግዚአብሔር ቤት በፍጹም ቅንነት እና በትጋት ይለቅ

    ReplyDelete
  2. ልዑል እግዚአብሔር ይባረክ ተባረክ ፀጋ ይብዛልህ በብዙ ተባረክ

    ReplyDelete
  3. የእግዚአብሔር ጸጋ የበዛልህ

    ReplyDelete