Sunday 28 July 2024

የፓሪስ ኦሎምፒክ ሴሰ*ኝነት፣ ሰዶ*ማ*ዊነት፣ በጌታ እራት ሲሳ*ለቁ!

 

“ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥”
(ሮሜ 1፥22)

በዘመናት መካከል ዓለምና ሥርዓትዋ፤ ሰይጣንና ሠራዊቱ ለእግዚአብሔርና ለሥራው ኹሉ ጠላትነታቸውን ደብቀው አያውቁም። ቅዱሱ መጽሐፍ፣ የዚህ ዓለም ሰዎች፣ “... የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት እየ ለወጡ ...”(ሮሜ 1፥25) በጥበባቸው ደንቆሮዎች እንደ ኾኑ በግልጥ ይናገራል።



በርግጥ፣ “እኛ የእግዚአብሔር መሆናችንን እናውቃለን። ዓለም ግን በሞላው የሰይጣን ተገዢ ሆኖአል።”(1ዮሐ.5፥19) እንዲል፣ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና ከዚህ ዓለምና ከመላው ሥርዓቱ ጋር አንድ አይደለንም። በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ “...ከጨለማ ሥልጣን ድነን፥ ቤዛነትንና የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት ፈልሰናል”(ቆላ. 1፥13-14)።

በዚህ እውነት የማይመላለስ ለኢየሱስ እንግዳና ባዳ የኾነ፤ በመስቀሉ የሚሳለቅ፤ በሞቱ የሚዘብት፤ በሥራዎቹ የሚያፌዝ ... “... ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም ከሚመጣው”(ዮሐ. 10፥10) እና ሌባ ከተባለው ሰይጣን ጋር በግልጥ የሚሠሩ ጥቂቶች አይደሉም። ጌታ ይገስጻቸው!

በፓሪስ አደባባዮች ላይ የታየውና ጥበብና የመዝናኛ ትርኢት በሚመስል መልኩ የቀረበው ይህ ነው፤ በጌታ እራት ላይ እየተሣለቁ፤ ሴሰ*ኝነትን እየወደሱ፤ ሰዶ*ማ*ዊነትን እየነዙ።  ተወዳጁ መሲሕ በጸሎቱ አስቀድሞ ነግሮናል፤“ ... እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።”(ዮሐ. 17፥14) እንዲል፣ በምንም መንገድ የኢየሱስ ላልኾኑ፣ የኢየሱስ ነገር ፈጽሞ አይጥማቸውም።

በተያያዘ መንገድ የቱንም መዝናኛ ሲያዘጋጁ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን ጠላትነት ለመግለጥ፣ ሥራዎቹን በማዋረድና በማጥላላት ይገለጣሉ። ሥራቸውን እንደሚያፈርስ ስለሚያውቅ፣ አብዝተው ይቃወሙታል። እንደ ሞተላቸው፤ ደሙን ስለ እነርሱ ኀጢአት  ዋጋ ከፈሎ ማፍሰሱን መቀበል አይሹም። የዚህን ምክንያት መጽሐፍ ሲናገር፣ “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፤”(ሮሜ 1፥28)።

የፓሪስን ኦሎምፒክ መክፈቻ የጌታን እራት በማቃለል፣ ሴሰ*ኝነትን እያመለኩ፣ ሰ*ዶማ*ዊነትን ያለ ሃፍረት በድፍረት ያቀረቡትን ርኩ*ሰት፣ ብዙዎች ተቃውመዋል። ጥቂቶቹ ተቃውሞዎች እኒህ ናቸው፦

“በክርስትና ላይ የተደረገ ከባድ ተሳልቆና የጥልቅ ዓለማዊ የድኅረ ዘመናዊ አስተሳሰብ ነው ...”

“... ለክርስቲያኖች እጅግ አክብሮት የጎደለው ተግባር ነው ...”

“... እንዲህ ባለ መንገድ በሌላ ሃይማኖት ላይ ይሳለቁ ነበር? አሳፋሪ ውሳኔ።”

“... በእውነት ይህ ስድብ ነው”

በማለት ብዙዎች ድርጊቱን አውግዘዋል።

በርግጥ ክርስትና በየትኛውም ዘመን ከተግዳሮት፤ ከስድብ፤ ከነቀፋ ... ነጻ ኾኖ አያውቅም። ከክርስቶስ ጋር ጸንተው ለቆሙ መስቀሉና ነቀፋው፤ ከርኩ*ሳን መካከል ወጥቶ መጣል ዛሬም ሕያውና ያለ ነው። ቀኖቹ እየከፉ እንጂ እየተሻሉ እንደማይሄዱ እናውቃለን። መጽሐፍ እንደሚል፣ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።”(ኤፌ. 5፥15-17) ተብለናልና እጅግ እንጠንቀቅ፤ የመዝናናቱ ዓለም በሙሉ አቅሙ እየሠራ ያለውን ዓመጽ በመመልከት እንጠበቅ። ኀጢአተኝነትን በመካድና በመጠየፍ ጸንተን እንቁም!

“ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ጌታችን ሆይ፥ ና።” (1ቆሮ. 16፥22)።

 


1 comment: