Saturday 6 March 2021

የጾመ ሕርቃልና የጾመ ዓቢይ ተቃርኖ

 Please read in PDF

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የዓቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ስያሜ “ዘወረደ” ወይም “ጾመ ሕርቃል” ይባላል። የመጀመሪያውን ሳምንት “ዘወረደ” የሚለውን ስያሜ ያገኘው በባለዜማው ያሬድ ሲኾን፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሰማያት መውረድና የሰዎችን ልጆች ለማዳን ያደረገውን የውርደት መንገድ በማሰብ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ንባባት እየተነበበ አምልኮ የሚቀርብበትም ሳምንት ነው። ይኸው ሳምንት ከዚህ ከጌታችን ባሕርይ ተቃራኒ በኾነ መንገድ “ጾመ ሕርቃል” ተብሎም ይጠራል።

የጾመ ሕርቃል አጭር ጥንተ ታሪክ[1]

በ614 ዓ.ም ሕርቃል የሚባል የቤዛንታይን ንጉሥ ይኖር በነበረበት ዘመን፣ ኪርዮስ የተባለ የፋርስ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ወረረ፤ ንግሥት ዕሌኒ አሠርታ ወደ ነበረውና የጌታን መስቀል አስቀምጣ ወደ ነበረበት መስቀሉ መቅደስ ቢገባ፣ መስቀሉ ታላቅ ብርሃን አውጥቶ ሊያስቀርበው ስላልቻለ፣ በካህናቱ አማካይነት መስቀሉን አሸክሞ፣ ብዙ ሺዎችን ገድሎ፣ ሌሎችንም አቁስሎ ከተማዋን አቃጥሎ ወዳገሩ ተመለሰ። ከዚህ በኋላ በዚህ ተግባር ያዘኑ ክርስቲያኖች አቤቱታቸውን ለንጉሥ ሕርቃል አቀረቡ፣ እርሱም ክርስቲያን ነበርና የፋርስን ንጉሥ ሊወጋላቸውና የወሰደውን መስቀልና ሌሎችን ንዋየ ቅድሳት ሊያስመልስ አስቦ፣ አንድ ነገር ግን አስጨነቀው፣ ይኸውም፣ “ሐዋርያት ሰውን የገደለ ዕድሜውን በሙሉ ይጹም ብለዋል፤ እኔ ደግሞ ጦርነት የምገጥም ከኾነ ሰውን እገድላለሁና ምን ላድርግ?” አላቸው፣ እነርሱም፦ “የአንተን ዕድሜ ተከፋፍለን እንጾማለን” አሉት፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንድ ሳምንት ሕርቃል በጦርነት ስለ ገደላቸው ሰዎች ሲባል፣ ይቅርታና ስርየት ያገኝ ዘንድ አንድ ሳምንት መጾም ተጀመረ።

አማናዊ ትምህርተ ክርስትና

በክርስትና ትምህርት ሰውን በማናቸውም መንገድ መግደል ወይም እንዲሞት ማድረግ ኀጢአት ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማኞቹ ወይም እርሱን የተከተሉት ደቀ መዛሙርቱ ጠላቶቻቸውን መውደድ፣ የሚረግሙአቸውን መመረቅ፣ ለሚያሳድዷቸው መጸለይ፣ ለሚጠሉአቸው ደግሞ መልካም ማድረግ እንዳለባቸው በግልጥ አስተማረ (ማቴ. 5፥44-45)፤ ሰውን መስደብ ወይም መቈጣት (ማቴ. 5፥22)፣ መናቅ ወይም በንቀት ማበላለጥ (ያዕ. 2፥1-3)  ፍጹም ኀጢአት ነው።

ስለዚህ ማናቸውንም ሰው መግደልም ኾነ መጥላትና መናቅ አንችልም ማለት ነው። ንጉሥ ሕርቃል ሰዎችን በጦርነት መግደሉ ሳያንስ፣ መግደሉ ይቅር የሚባለው በዕድሜ ዘመኔ ጾም ነው ብሎ አመነ፣ ሐዋርያት ያላስተማሩትን አስተማሩ ብሎ መጥቀሱ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌለውና “ዕድሜህን ተከፋፍለን እንጾምልሃለን” ያሉትም የዚያ ዘመን “ክርስቲያኖችን”፣ ፍጹም ስሑታን መኾናቸውን እናስተውላለን።

የትኛውም ኀጢአት ያለ ክርስቶስ ኢየሱስ ደም አይሰረይም፤ እግዚአብሔር ለኀጢአት ሥርየት ያፈሰሰው የልጁን ደም ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ስለ ኀጢአት ከልጁ በቀር የማንም ሥራ ወይም ጾም ወይም መልካም ሥራ አይመለከትም፤ ሰው ያለ ክርስቶስ የትኛውም መልካም ሥራዬ የሚለው ዕድፋምና ርኩስ ነው። ያለ ክርስቶስ ኹላችን መናኛ፣ ውራጅና በበደላችን ሙታን፣ የማንጠቅም የቊጣ ልጆች ነን። ስለዚህም ሕርቃል በጦርነት ተሳትፎ ሰውን መግደሉም ኾነ፣ እርሱ ስለ መግደሉ ተከፋፍለው ጾመውለታል የተባሉት ፍጹም ተሳስተዋል።

ከዚህ የሚከፋው፣ ይህን የክርስትና ትምህርት ተቃራኒ ተግባር ዛሬም ድረስ እየተፈጸመ መኾኑን ስናስተውል ነው። በሰው ደምና ታላቅ በደል ራሳችንን ተጠያቂ ማድረጋችን እንዴት አሳዛኞች ነን? እንኳን የሰው ተጨምሮ፣ የእኛ ስፍር የሌለው በደልና ኀጢአት ያለ ክርስቶስ ታላቅ ምሕረት በምን ይሠረይ ዘንድ ይችላል? የሰውን ደም ማፍሰስ በምንም መንገድ መልካም አይደለም፤ ምክንያቱ ክርስቲያናዊ ቢመስልም እንኳ። የሰውን ደም በማፍሰስ የረከሰውን ተግባር በልጁ ኢየሱስ ደም፤ ደም አፍሳሹ ባልታጠበበትና ባልነጻበት ኹኔታ ከጌታችን ኢየሱስ ፍጹም የጽድቅ ጾም ጋር ወስዶ መደባለቅ፣ ሰይጣንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ የሚደረግ ፍጹም የግብዝነት መንገድ ነው። እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ካለ ጸያፍ ተግባርዋ ተመልሳ፣ ወደ ቅዱስ ቃሉ ፊቷን ዘወር ታደርግ ዘንድ እንማልዳለን።  ጌታ ሆይ፤ ዘመናችንን አድስልን፤ አሜን።



[1] ፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭

3 comments:

  1. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete
  2. ዘመናችንን አድስልን የሚለው ቅኔ ነው?ኦርቶዶክስን አድስልን የሚለው ቀረ?
    ኦርቶዶክስ የቁጥርን ምስጢር አለማወቋ በጣም ይገርማል፤40ን በ55 መቀየሯ ምንያህል ለቁጥር ምስጢር ደንታ እንደሌላት ነው የሚያሳየው፤ኦርቶዶክስ ከ55 ቁጥር ጋር ለምን በፍቅር(lust ) እንደወደቀች ግልፅ አይደለም፤ጌታ ኢየሱስ ተወለደ ብላ የምትተርተውም ከ5500(55×100) አመታት በኋላ ነው በማለት ነው፤ትክክለኛው ግን ከ4000(40×100) ነበር!!

    ReplyDelete
  3. ዘወረደ ብለህ የጠቀስከው የኦርቶዶክስን አስተምህሮ ነው፡፡ ሕርቃልም የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ነው፡፡ ነገር ግን አንተ ለምትከተለው ምንም የምታስተምርበት ነገር ሳይኖርህ ትምህርቱን ወስደህ ነቀፌታ ማስቀመጥ አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ የምታስተምረው ይኑነህ ራስህን ቻል፡፡ ከነቀፌታ ውጣ፡፡ ተዋህዶ ለትምህርት የሚያክላት እንደሌለ ልቦናህ እያወቀ ምሥጢርን አደላድላ ማስተማሩአን ፍትው እድገህ እያሳየህ ለመቃወም መሞከር ከጀርባ ምን አለ ያስብላል፡፡ እርግጥ ነው የእኛ ቤተክርስቲያን ገንዘብ አትዘራም፡፡ ደባ የለባተም ሳታውቁት ለአላውያን ሐገር ማፍረስ ተልእኮ መሳሪያ መሆናችሁ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡

    ReplyDelete