Friday, 19 January 2024

“እያጠመቃችኋቸው፥ … እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” (ማቴ. 28፥20)

 Please read in PDF

ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጡ ሐዋርያዊ ተልእኮዎች ውስጥ፣ ቀዳሚውና የዘወትር ተግባር “አማኞችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ” ነው። እንደ ጌታችን ትምህርት፣ አማኞች ደቀ መዛሙርት የሚኾኑት፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሲጠመቁ፣ ጌታ ያዘዘውን ኹሉ እንዲጠብቁ ሲማሩ፣ እንዲሁም በመታመን እርሱን ለመከተል ደቀ መዛሙርት በሕይወት ሲኾኑ ነው።


ኢየሱስን መከተል አካላዊ ብቻ አይደለም፤ ብዙዎች በአካላቸው ቢከተሉትም ነገር ግን ሕይወት አልኾነላቸውም። በሕይወት ለመከተል ደግሞ ማሟላት ካለብን ነገሮች አንዱ የውኃ ጥምቀት ነው፤ ለምን ግን እንጠመቃለን?

1.   ክርስቶስ በውኃ መጠመቅን ስላዘዘን፦ በርዕሳችን የጠቀስነው የማቴዎስ ወንጌል ትእዛዝ በውኃ መጠመቅን ብቻ ባያመለክትም፣ በውኃ መጠመቅ እንዳለብን ጌታችን ኢየሱስ በውኃ በመጠመቅ እውነታውን አሳይቶ፣ አዝዞናል።

ሰዎች እንዲያው ሊጠመቁ አይችሉም፤ ነገር ግን እኛ በጌታችን ትእዛዝ “ሂዱ” ተብለን ታዝዘናል፤ ወደ መላለሙ ሂዱ ተብለናል፤ በሉዓላዊነቱ በሚገዛበት ስፍራ ኹሉ፤ እስከ ምድር ዳርቻ፤ ሰዎች ባሉበት ቦታ ኹሉ፤ ጎሳዎች፣ ብሔሮች፣ በልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች፤ ከውቅያኖስ ማዶ፤ ከባሕርና ከአድማስ  ባሻገር … ሂዱ፤ ወንጌልን አውጁ፤ ለፍፉ፣ ተናገሩ፣ መስክሩ … ከዚያም አጥምቁ፤ ከዚያም የጌታን ትእዛዛት በመጠበቅ እንዲጸኑ ሰዎችን አስተምሩ፤ ቅረጹ፤ አሳድጉ፤ አጽኑ፤ ደቀ መዛሙርት አድርጉ ተብለናል።

2.   በአደባባይ ምስክርነታችንን ለአማኞችና ለዓለም ለመግለጥ፦ ሰዎች ክርስቶስን በማመን ከመንፈስ ቅዱስ በመወለድ፤ በመንፈስ ቅዱስ ይጠመቃሉ። ስለ ተጠመቁም መንፈሳቸው ከመንፈስ ቅዱስ መወለዳቸውን ይመሰክርላቸዋል። ልክ እንዲሁ ሰዎች ስለ ማመናቸው ምስክርነት በቤተ ክርስቲያን ፊት ይጠመቃሉ።

ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ስለ ተጠመቁ፣ ወደ ፍጹሙና ወደ ሥላሴ ሕብረት ይገባሉ፤ ሰዎች በውኃ ሲጠመቁ ደግሞ ወደ ቅድስቲቱ ኅብረት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይጨመራሉ። በበዓለ ሃምሳ ሰዎች ልክ በኢየሱስ እንዳመኑ ወይም በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተጠመቁ፣ የውኃ ጥምቀት ፈጸሙ (ሐ.ሥ. 2፥38)፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የፊልጶስን ስብከት ሰምቶ ልክ እንዳመነ በውኃ ተጠመቀ፤ (8፥37)።  

በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ያመኑ ብቻ ተጠመቁ፤ ክርስቶስን ቤዛና መድኀኒት ያደረጉ ብቻ ተጠመቁ፤ ደቀ መዛሙርት ለመኾን የጨከኑ ብቻ ተጠመቁ፤ በአይሁድና በአሕዛብ ፊት ምስክር ሊኾኑለት የጨከኑና ወደ ተናቀችውና በብዙዎች ዘንድ ስፍራ ወዳልተሰጣት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ ሊጨመሩ የወደዱ ተጠመቁ! ስንጠመቅ የሚያዩን ለክርስቶስ መጨከናችንን፣ ለዓለም መሞታችንን ለእርሱ ብቻ ሕያዋን መኾናችንን ያስተውላሉ!

ስንጠመቅ ኅብረታችን ከማን እንደ ኾነ ገልጠናል፤ በቤተ ክርስቲያናችን በውኃ ስንጠመቅ፣ በክርስቶስ ስለ ማመናችን አሰምተን እንመሰክራለን! ይህን እምነታችንን መኖር የምንጀምረው፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ መኾኑን ለማብሠር ደግሞ ክርስቶስ ራስ ወደ ኾነባትና ብልቶቹን ሕያዋን ወዳደረገባት ወደ ቅድስት ኅብረት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንገባለን!

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።” (ኤፌ. 6፥24)

No comments:

Post a Comment