Saturday 6 January 2024

ከባሪያዪቱ የተወለደ ንጉሥ!

 Please read in PDF

የክርስትና ትምህርት ከደመቀበትና ከተንቈጠቈጠበት ቀዳሚው እውነት አንዱ፣ የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ የሚያምኑትን ኹሉ በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች ያደርግ ዘንድ የሰው ልጅ መኾኑ ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኾኖ፣ ዓለማትን የፈጠረና ደግፎም የያዘ ወይም ዓለሙ ተያይዞ የቆመው (ዮሐ. 1፥3፤ ቈላ. 1፥17፤ ዕብ. 1፥3) በእርሱ በታላቁ አምላክ ቢኾንም፣ በተለየ አካሉ  ከባሪያዪቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም (ማቴ. 1፥21፤ ዮሐ. 1፥14) ሥጋን ነሥቶ ተወለደ።

ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ዘወትር አምላክና የመለኮት ኃይል ያለው ጌታ ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን የመለኮት ባህርይ በኃይል እንደ ያዘ ሳይቈጥር ክብሩን ኹሉ በፈቃዱ ትቶ፣ እንደ ባሪያ ታየ ብሎም እንደ ሰው ተወለደ” ይለናል፤ (ፊል. 2፥6-7)። ታላቁ አምላክ የሰውን ሥጋ በመልበስ ተዋረደ፤ ፍጹሙ አምላክ የሰውን ባሕርይ በመያዝ አገልጋይና ባሪያ ኾነ (ማር. 10፥45)። በሰማያዊ ስፍራ ፈጣንና ተልእኮ በትክክል ፈጻሚ የኾኑ መላእክት እያመለኩትና እየታዘዙት በመንግሥተ ሰማያት በተድላና በሐሴት መኖር የሚቻለው ጌታ፣ በከብቶች ግርግም በቂ ልብስና መጠለያ በሌለበት ስፍራ ከባሪያዪቱ ተወለደ (ሉቃ. 2፥6-7)!

እርሱ እንዲህ ወደ ውርደትና ውድቀት ዓለም ሲመጣ፣ ክብሩንና መብቱን ኹሉ ትቶ፣ ራሱንም ባዶ አድርጎ ነው። በትህትናው ወደር የሌለው አምላክ ነውና (ማቴ. 10፥29) ፍጹም ትሁት ኾኖ በምድር ተገለጠ። እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ ይህ ትሁት ጌታ፣ ከባሪያዪቱ በተወለደው ማንነቱ ከአባቱ ፈቃድ በቀር የራሱን አንዳች ፈቃድ ላይፈጽም፣ በሰብዓዊ ሰውነት ሰውነት ውስጥ ራሱን ወሰነ። እንደ ባሪያነቱና አገልጋይነቱም ለሌሎች ሊኖርና ሊሞት ተወለደ።

ኢየሱስ ከሰማያት ሲወርድ ብቻ ሳይኾን፣ ከቅድስት ድንግልም ሲወለድ በፍቱም ትህትና ነበር፤ ትህትና ደግሞ ኹል ጊዜም በደል ለደረሰበት ሰው ስቃይን ያስከትላል። ክርስቶስ የመስቀል ጉዞውን የጀመረው ሰው ከመኾኑ ጀምሮ ጭምር ነው፤ የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ፣ እርሱ የባሪያን መልክ ይዞ፤ አባቱንና እኛን አገለገለን።

ቅድስት ድንግል ማርያም ይህ ታላቅ ምስጢር በእርስዋ እንደ ተፈጸመ ስታውቅ እንዲህ አለች፣ “የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና።” (ሉቃ. 1፥48)። እግዚአብሔር፣ የተዋረደች ልጃገረድ ድንግል ሳለች፣ እርስዋን በመምረጡ፣ “ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።” (1፥54-55) ብላ እንደ ተናገረችው፣ ምሕረት እንደ ተደረገላት አስባ ፍጹም እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ ምክንያቱም ለዚህ ምስጢር ብቁና ንቁ ኾና አልነበረም፤ ይኹንና ምሕረት ተደርጎላት እንጂ፤ ምሕረት ደግሞ “እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ የማይገባንን ነገር እንዳደረገልን የሚያመለክት” ውብ ዐሳብ የያዘ ቃል ነው።

ጌታ ለእኛ የተወለደው ምሕረት አድርጎልን ነው፤ ማለትም የማይገባን የነበርነውን እንዲገባ አድርጎን ራራልን፤ ማረን፤ ባሮች ሳለን እንደ ልጆቹ ከተዋረደው መሲሕ የተነሣ ተቀበለን፤ ኀጢአተኞች ሳለን ከክርስቶስ ጽድቅና ቅድስና የተነሣ እንደ ጻድቃንና ቅዱሳን ተቀበለን፤ ባሮቹን የወደደ፤ ጌታ ልዑል ሲኾን፣ ባሮቹን ልጆቹ ሊያደርግ ከባሪያዪቱ የባሪያን መልክ ይዞ  ለተወለደ ጌታ ክብርና ኃይል ይኹን፤ አሜን ወአሜን።   

1 comment:

  1. እውነቱ እጅግ በጣም ያስደስታል ልክ እንደዚህ በርታ ቀጥል

    ReplyDelete