ካለፈው የቀጠለ …
ባለፈው “የመድሎተ
ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ (Exegesis) ሳይኾን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ (Eisegesis) እንደሚተረጕም አንድ ምሳሌ አንስተን
ነበር። ዛሬ በድጋሚ ኹለተኛ ምሳሌ በማንሳት በዚህ ርዕስ ሥር ያለውን ዐሳብ እንቋጫለን።
1.5.2.
ስለ ሥጋ ወደሙ ለማስተማር
ሲፈልግ፣ ጌታችን ኢየሱስ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ያልተናገሩትን ልክ እንደ ተናገሩ አድርጐ ሲያቀርብ እንመለከተዋለን። ለምሳሌም፦
1ቆሮ. 10ን በመጥቀስ ምሳሌውን እንዲህ ይፈታዋል።
·
በቀይ ባህር መካከል ማለፍ - በውኃ ጥምቀት መጠመቅ
·
መናውና የዓለቱ ውኃ - የክርስቶስ ሥጋና ደም
·
ከግብጽ መውጣት - ከሲዖል የመውጣት
· መናውን መብላት ዓለቱን መጠጣት - ሥጋና ደሙን መብላትና መጠጣት
በሚል ምሳሌዎች ለማቅረብ ይሞክራል፤ ከዚህ ጋር አጣምሮ ዮሐ. 6፥48-51 ያለውንም አዛምዶ ያነሳቸዋል። ነገር ግን ሥጋውና ደሙን
መብላትና መጠጣት የሚለው ትርጕም፣ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጕሞ እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመ አይደለም። ይህንም ከዚህ በታች
በምናቀርበው ዐውዳዊ ትርጕም ማቅረብ እንችላለን።
· ጌታችን ከተናገረው ብንነሣ፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ.
6 ላይ የተናገረውን “ሥጋዬንና ደሜን ብትበሉና ብትጠጡ” ያለውን ቃል፣ በዚያን ጊዜ አይሁድ እንደ ተሰናከሉበት፤ ዛሬም እየተሰናከሉበት
እንዳሉት “ኦርቶዶክሳውያን ካራዎችና እንደ ሌሎች” ዐሳብ የተነገረ ቃል አይደለም።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ. 6
ላይ ሥጋውን ስለ መብላትና ደሙን ስለ መጠጣት የተናገረው፣ “በእርሱ ከማመን ጋር በአንድነት አዛምዶ የተናገረው መኾኑን ክፍሎቹን
ስንመለከት እናስተውላለን”፤
“ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን
ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ
ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።” (ዮሐ. 6፥27)
“ኢየሱስ
መልሶ፦ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ
ነው አላቸው።” (ዮሐ. 6፥29)
“የሕይወት
እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ
የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።” (ዮሐ. 6፥35)
“እውነት
እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም
ሕይወት አለው።” (ዮሐ. 6፥47)
“ሕያው አብ
እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ
ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል።” (ዮሐ. 6፥57)
“ሕይወትን
የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ
የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።
ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም
ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና” (ዮሐ. 6፥63-64)።
በቀደመው ታሪክ ጌታችን ኢየሱስ እንጀራን
አበርክቶ ለሕዝቡ አብልቶ ነበር፤ የሕዝቡ ፍላጐት ጌታችን ኢየሱስ በሙሴ አማካይነት ከመና የላቀ ሌላ አዲስ ተአምር እንዲያሳያቸውና
አሁንም አበርክቶ እንዲያበላቸው ነበር (6፥30)፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ከሰማይ መና የሰጠው ሙሴ ሳይኾን፣ እግዚአብሔር መኾኑን
አረማቸው፤ በተጨማሪም እውነተኛውን መና ወይም ወልድ ያለውን ሕይወት የሚሰጥ አብ እንደ ኾነ ተናገራቸው። ይህን ማመን ራሱ ሥራ
ነው (6፥28)። ሥራውም፣ “ይህ የእግዚአብሔር ሥራ እርሱ በላከው እንድታምኑ ነው” ብሎ ጌታችን ግልጡን ተናገረ። ነገር
ግን ሕዝቡ፣ ኢየሱስ ምን እንደ ተናገራቸው አላስተዋሉም! (6፥34)።
ቀጥሎ ኢየሱስ እንዲህ በማለት በግልጥ
ተናገረ፣ “የሕይወት
እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም።” (6፥35)። በዚህ አገባብ ወደ ኢየሱስ
መምጣት ማለት፣ በኢየሱስ ማመን ማለት ነው። የወንጌል አንድምታ፣ “ወደኔ የመጣ ማለት በኔ ያመነ አይራብም። በኔ ያመነ
ረኃበ ነፍስ ጽምዓ ነፍስ የለበትም።” እንዳለው።[1]
የወንጌል አንድምታ ቍ. 44ን እንዲህ
ይተረጕማል፤ “የላከኝ አባቴ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ካልሰጠ በቀር በኔ ማመን የሚቻለው የለም” ይላል፤[2]
ቍ. 65ንም ሲያብራራ፣ “ዕውቀቱ ካባቴ ካልተሰጠው ስለዚህ ነገር በኔ
ማመን የሚቻለው የለም ብዬ እነግራችኋለሁ።”[3]
እንግዲህ ቅዱሳት መጻሕፍት በዚህ ክፍል የተናገረውን “መብላትና መጠጣት” ከሥጋ ወደሙ ጋር ሳይኾን፣ ኢየሱስን ከማመን ጋር በቀጥታ
ያገናኛሉ።
ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ይህ ክፍል ስለ
ጌታ ዕራት እንደሚናገር ያምናሉ፤ እኛ ደግሞ ጌታን ስለ ማመን እንጂ ስለ ዕራቱ የተነገረ አይደለም ስንል፣ የጌታን ዕራት እንደምንክድ
አድርገው ያቀርባሉ፤ እውነታው ግን ሌላ ነው። እኛ ወደ ፊት በጽሑፍ እንደ ማሰፍረው፣ በአጭሩ የጌታን ዕራት በመቀበል እናምናለን።
ነገር ግን ክፍሉን ስንመለከተው፣ በተደጋጋሚ
የሚናገረው በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን እንጂ የኢየሱስን ሥጋ በቀጥታ ስለ መብላት አልያም ደሙን በቀጥታ ስለ መጠጣት የሚናገር
አይደለም። ጌታችን በእርሱ የሚያምኑትን ኹሉ፣ ከእርሱ
ጋር ባለው ሕይወት ተካፋዮች ይኾኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ሕያው አደባባይ ያስገባቸዋል፤ ይህ እጅግ ታላቅ ምስጢር ነው!
እንግዲህ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ በዚህና ባለፈው ባየነው ኹለት ምሳሌዎች ብቻ ሳይኾን፣ በአያሌ የግል መጽሐፉ ላይ ወደ መጽሐፍ
ቅዱስ ሲተረጕምና በቤተ ክርስቲያኒቱ ያሉትን መጻሕፍት በመቃወም ሲጽፍና ሲያብራራ እንመለከተዋለን።
ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱስ አምላካውያት መጻሕፍት
ወይም እስትንፋሰ እግዚአብሔር ነው። በግልጥ ቃል፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” (2ጢሞ. 3፥16) የተባለው ለመጽሐፍ
ቅዱስ ብቻ ነው። እኒህ መጻሕፍት የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን መጻሕትን ኹሉ ሊያመለክቱና (2ጢሞ. 2፥15፤ 2ጴጥ. 3፥16)
ደግሞም፣ መጻሕፍቱ፣ “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ኹሉ የሚጠቅሙ ናቸው”።
ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር እስትንፋስ ከኾኑ፣ ሊተረጐሙና ሊብራሩ የሚገባቸው በእግዚአብሔር እስትንፋስ በኾነው በመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፤ ይህን ስናደርግም የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን እያከበርንና ለእግዚአብሔር መታዘዛችንን እያሳየን ነው ማለት ነው። ይህ ካልኾነ ለገዛ ራሳቸው ከሚተረጕሙት ሐሰተኞች መካከል መኾናችን አይቀሬ ነው።
እንግዲህ ደግመን እንላለን፤ ኢየሱስን
ማመን የዘላለም መብልና ሕይወት፤ የዘላለም መጠጥና ተድላን ያሰጣል፤ እመኑና በርሱ ዕረፉ!
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment