ካለፈው ቀጠለ …
5. የቅድስት ሥላሴ ትምህርት ምስጢር ነው!
ትምህርተ ሥላሴ ምስጢር ነው ስንል፣ ምን ማለታችን ነው? ብንል፣ ለሰው ያልተገለጠ ብዙ ትምህርት ወይም ብዙ ነገር አለ ማለታችን ነው። ኾኖም ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ሦስቱን አካላት ለማጥናት ብዙ ትምህርት እንዳለ ልንዘነጋ አይገባም። በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ትምህርቶች ምስጢር ተብለዋል፤ ለምሳሌ፦ ጌታችን ኢየሱስ፣ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።” ሲል (ማቴ. 13፥11)፣ ምሳሌዎቹ የተነገሩት በሕዝቡ ኹሉ ፊት ቢኾንም፣ ትርጕማቸው ወይም ምስጢሩ ግን የተነገረው ለደቀ መዛሙርት ብቻ ነው።
በሌላ
ስፍራ፣ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል በድንዳኔ ወይም በድንዛዜ ውስጥ ስለ ማለፏ (ሮሜ 11፥25 እና
16፥25-26)፣ እንዲኹም የሙታን ትንሣኤ ጉዳይ (1ቆሮ. 15፥51)፣ በተጨማሪም “እኔ እስረኛ የኾንኹለትን የክርስቶስን
ምስጢር ማወጅ እንድንችል” ሲልና (ቈላ. 4፥3)፣ “በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር
አስታውቆናልና፤” (ኤፌ.
1፥9) ብሎ ሲናገር ምስጢራት ስለ መኖራቸው መነገሩን እናስተውላለን።
መዘንጋት
የሌለብን እውነት ግን “ምስጢር” ሲል፣ ያልታወቀ ማለት አይደለም፤ ምስጢር የተባለው ነገር ጊዜው ሲደርስ የሚነገርና የሚታወቅ ወይም
የሚገለጥ ነውና። ታዲያ ለምን ምስጢር ተባለ? ተብሎ ቢጠየቅ፣
“… መልሱ በአጭሩ እንደሚከተለው ይኾናል። ከሌሎች ትምህርት
ተለይቶ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ምሥጢር የተባለበት ምክንያት የሰው ውሱን አእምሮ ሊደርስበት ስለሚያዳግተው ስለ እግዚአብሔር
መለኮታዊ ባሕርይና አካል ስለሚያስተምር በተለይም አንድ ሲኾን ሦስት፣ ሦስት ሲኾን አንድ የመኾኑን ረቂቅ ምስጢር ስለሚናገር
ነው። የእግዚአብሔር ባሕርይ ረቂቅ፣ አኗኗሩም ምጡቅ በመኾኑ እንደ ሌላው ትምህርት በቀላሉ ተመራምረን የምንደርስበት ስላልኾነ
ምሥጢር ተብሎአል።”[1]
በቀላሉ ሊደረስበት የማይቻል ነው ቢባልም እንኳ፣ ይህን ትምህርት ማስተማር የሚገባን አቆይተን ወይም
ዕድሜያቸው ከፍ ሲል ነው የሚል አቋም የለንም። ይልቁንም በክርስትና ገና ከጅማሬ ጀምሮ ሰዎች ኹሉ አስቀድመው ሊማሩ የሚገባቸው
የእምነት መሠረተ ትምህርት ነው። “ምሥጢሩ
ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።” (ዘዳ. 29፥29) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ስለ
እግዚአብሔርና ስለ ተግባራቱ ብዙ ያልተረዳናቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ በተገለጠውና በተረዳነው እውነት ላይ እኛና ልጆቻችን ኹሉ
ማተኰር ይገባናል።
ስለ ሥላሴ ልናውቃቸው የሚገቡ ምስጢራት፣
5.1. ሥላሴ ህላዌያዌ ሦስትነት (Immanent
(Ontological) Trinity) አላቸው፦
ሥላሴ
እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነታቸውና ማለትም፣ “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም
በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።” (ማቴ.11፥27) ሲል፣ በአብና በወልድ መካከል ፍጹም
አንድነት መኖሩን ያመለክታል።
ቅድስት
ሥላሴ እኛን በማዳን በሠራው ሥራ፣ ፍጹም አንድነታቸውም ተገልጦአል፤ ወይም ወልድ በመዋረዱ አምላክነትን እንደ መቀማት
አልቆጠረም ወይም መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን በመሰጠቱ አላደፈም። ደግሞ፣ “ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ሲያመጣ የመዳናቸውን ራስ
በመከራ ይፈጽም ዘንድ፥ ከእርሱ የተነሣ ሁሉ በእርሱም ሁሉ ለሆነ፥ ለእርሱ ተገብቶታልና።” (ዕብ. 2፥10) ተብሎ እንደ
ተጻፈ፣ ወልድ መለኮታዊ ክብሩን በመተው እንደ እኛ ሰው ኾኖ፣ መከራን በመቀበል ያዳነንና፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ቤተሠብ ያደረገን
ፍጹም አምላክ ነው።
"ሁሉም
ከእርሱ [ከክርስቶስ]፣ በእርሱ [በክርስቶስ]፣ ለእርሱ [ክርስቶስ] ነውና፤ ለእርሱ [ለክርስቶስ] ለዘላለም ክብር ይሁን፤
አሜን።" (ሮሜ 11:36)፣
“እርሱም የማይታይ
አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር
ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤” (ቆላ. 1፥15-16) ይላል።
ስለዚህ
ወልድ ፍጥረትን ፈጠረ ወይም አዳነ ስንል፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተለይቶ አይደለም፤ ስለዚህ ፍጥረት ኹሉ ለሥላሴ ይገዛል።
በማዳንም ደግሞ ወልድ በተለየ አካሉ መጥቶ ሥጋ ለበሰ እንላለን እንጂ አብም መንፈስ ቅዱስም ለበሱ አንልም። የክርስቶስ ማዳን
ፍጻሜውም የሥላሴን መንግሥት መመሥረትና ማጽናት ነው።
ደግመን
እንዲህ እንላለን፣ “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ 11፥36)
ይቀጥላል
…
No comments:
Post a Comment