ጌታችን ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያት ምን እንደምትመስል በሰጠው ውብ ምሳሌ፣ እግዚአብሔርን የወይኑ እርሻ ባለቤት አድርጎ ያቀርበዋል። የእርሻው ባለቤት በአትክልቱ ስፍራ ሰውን ለመቅጠር ፈልጎ ጥሪ አቀረበ። በጥሪው መሠረት ሠራተኞቹ፣ አንድ ዲናር ሊከፈላቸው ተስማምተው ወደ እርሻው ቦታ መጡ። የሥራው ሰዓትም ከማለዳ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት ነበር።
ሠራተኞቹ ክፍያው ጥሩ በመኾኑ በክፍያው ደስ ተሰኝተዋል። ዳሩ ግን በሦስተኛው፥
በስድስተኛው፥ በዘጠነኛውና በዐሥራ አንደኛው ሰዓት የእርሻው ባለቤት ያልተቀጠሩ ሌሎች ሠራተኞችንም አገኘ። በሚያስደንቅ መንገድም፣
ወደ አትክልቱ ቦታ እንዲህ ብሎ ላካቸው፣ “የሚገባቸሁንም ዋጋ እከፍላችኋለሁ”። ልክ በሰዓቱ የእርሻው ባለቤት ለሠራተኞች እኩል ዋጋ ከፈላቸው፤ የቱንም ያህል ረዥም ጊዜ
የሠሩ ቢኾን ኹሉም አንድ ዲናር አገኙ።
በዚህ ጊዜ ከማለዳ ጀምሮ ሲሠሩ የነበሩት፣ አርፍደው ከመጡት ጋር እኩል ዲናር
ስለ ተከፈላቸው የእርሻውን ባለቤት “ፍትሐዊ አይደለህም” ብለው፣ ሞገቱት። ምሳሌው ፍትሐዊነት የጎደለው ይመስላል። ከማለዳ ጀምሮ
ለለፋውም፣ በሠርኩ ሰዓትም ለመጣውም እንዴት ለኹሉም እኩል ይከፈላል? ይህ ጥያቄ የብዙዎቻችን ይመስለኛል። ወላጆቻችን ልጆች ኾነን
እኩል ነገር ሳያደርጉልን ሲቀሩ የፍትሕ ጥያቄ እናነሳለን።
የጌታ ኢየሱስ ምሳሌዎች አንዳንዴ እንዲህ ያለ ጥያቄ ያጭራሉ። የፍትሐዊነት
ጥያቄ! ግና ዋናው እውነት ፍትሐዊነት አይደለም፤ በወደቀው ዓለም ላይ ምንም እኩልና ያልተጓደለ ፍትሕ የለምና። ትልቁ ቁም ነገር
ግን ከፍትሐዊነት የሚያልፈው እውነት ነው፤ እርሱም ልግስናና ቸርነት። ልግሥናና ቸርነት ከፍትሐዊነት ይበልጣል።
የእግዚአብሔር መንግሥት የኾነው ኢየሱስና የወይኑ እርሻ ባለቤት እግዚአብሔር፣ ልግሥናቸው ወደር የሌላቸው ባለጠጎች ናቸው። “ለዘሪ
ዘርን፥ ለምግብ እንጀራን የሚሰጥ አምላክ የምትዘሩትን ዘር አበርክቶ ይሰጣችኋል፤ የልግሥናችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል።” (2ቆሮ.
9፥10) እንዲል በልግሥናው አበርክቶ፤ አብዝቶ፤ አትረፍርፎ ይሰጣል።
ፍትሐዊ ባልኾነች ዓለም ላይ፣ የፍትሕ ጥያቄ አብዝቶ ከመጠየቅ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር
ለጋሥነት ልባችሁ ይመላ፤ አሜን!
No comments:
Post a Comment