Tuesday 13 February 2024

ነገረ ሥላሴን የምናጠናበት ምክንያት (ክፍል ፰)

Please read in PDF

ካለፈው የቀጠለ …

5.2. ሥላሴ ምግባራዊ ሦስትነት (Economic Trinity) አላቸው

በሌላ ንግግር አብ ከወልድ ወይም ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን ዐይነት ግንኙነት፣ ከፍጥረት ጋርም እንዲያ ያለ ግንኙነት የለውም። በሥላሴ መካከል ያለውን ኅብረትና አንድነት የሚያመለክተው ግንኙነት፣ ምግባራዊ ሦስትነት (Economic Trinity) ተብሎ ይጠራል። በዚህ ረገድ የሥላሴ እያንዳንዱ አካል በመለኮታዊ ማንነቱ ፍጥረትን በመፍጠር፣ በመመገብ፣ በልዕልና በመምራት፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በማዳን በሚሠሩት መለኮታዊ ሥራዎች ያላቸውን ፍጹም አንድነት የሚያመለክት ነው።

ቅድስት ሥላሴ በጋራ ወይም በአንድነት ከፍጥረት ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት፣ እያንዳንዱ አካል የተለያየ ግብር አለው። ይህን ሲያደርጉ ግን ከአንዲት ፈቃዳቸው ሳይለያዩ ወይም ሳይቀዋወሙ ነው። ለምሳሌ፦ ወደ አብ በክርስቶስ በኩል ነው መቅረብ የሚቻለን፤ ለመግባትም ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ በኩል አለን፤ ቅዱስ ቃሉም፣ “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።” እንዲል (1ቆሮ. 8፥6)።   

ፍጥረትንና ማዳንን በተመለከተ በሥላሴ መካከል ያለውን ድርሻ እንዲህ ማስቀመጥ እንችላለን።

  • አብ፦ ቅዱስ ቃሉ፣ “እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው” (1ጴጥ. 1፥1) እንዲል አብ ይመርጣል ደግሞም መዳንን ከዘመናት በፊት የሠራ (ኤፌ. 1፥3-4)፤ እንዲሁም ዓለምን ይወድዳል (ዮሐ. 3፥16)። መልካም ስጦታን መስጠት (ያዕ. 1፥17)፣ ስለ ወልድ መግለጥና መመስከር (ዮሐ. 5፥31፤ ማቴ. 16፥17)፣ የጸሎታችን አድራሻ (ዮሐ. 14፥4)፣ የፍጥረተ ዓለሙ ፈጣሪ ዘላለማዊና የማይወሰን አምላክ (ዘፍ. 1፥1፤ መዝ. 86፥9-10) እግዚአብሔር አብ ነው።

“እኔ ከሰማይ የወረድኩት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም።” (ዮሐ. 6፥38) እንዲል ዓለም በልጁ እንዲድን ወደ ምድር የላከው እግዚአብሔር አብ ነው። የሕይወትና የመዳናችን ዋና እንዲኾን በተወሰነው ዐሳቡና በቀደመው እውቀቱ ሰጠ፤ (ሐ.ሥ. 2፥23)። እጅግ በሚያስደንቅ መንገድም፣ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፥23) እንዲል፣ ከዚህ የተነሣ ሕይወትና መዳን ኾነልን!

  • ወልድ፦ በተለየ አካሉ ሥጋን ከቅድስት የነሣ (ማቴ. 1፥21፤ ዮሐ. 1፥14)፣ መከራ ተቀባይ የሥላሴ አካልም እርሱ ነው (ማር. 8፥31)፣ የአባቱን ፈቃድ በመፈጸምና ደሙን በማፍሰስ፣ ከጨለማ ሥልጣን አድኖ መዳንን ኹሉ የፈጸመው ጌታም እርሱ ነው (ዮሐ. 6፥38፤ 1ጴጥ. 1፥18)፣ ዓለማትን የፈጠረና ደግፎም የያዘ ወይም ተያይዞም የቆመው (ዮሐ. 1፥3፤ ቈላ. 1፥17፤ ዕብ. 1፥3)፣ የምንጸልይበት ስም (ኤፌ. 1፥6፤ 2፥18፤ 6፥18) በአብ ፊት የሠለጠነና የታወቀ ስም ነው።

ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው፣ አንድና ብቻ የእግዚአብሔር ልጅና ኹለተኛው የሥላሴ አካል ነው (ዮሐ. 1፥1፡ 14)። የሰውን ሥጋ በመልበስ ፍጹም ሰው የኾነ (ኢሳ. 7፥14፤ ማቴ. 1፥23፤ ሉቃ. 2፥7፤ 24፥39፤ ሐ.ሥ. 2፥22)፣ ሰው በመኾኑንም ኃጢአት ሳይገኝበት (ዮሐ. 8፥46፤ ማቴ. 27፥23፤ ዕብ. 7፥26) ስለ ሰው ልጆች መዳንና የኀጢአት ሥርየት በሥጋ ሞተ፤ (ማቴ. 27፥50፤ ማር. 15፥44) ለቤዝወትም ራሱንም አሳልፎ ሰጠ፤ (ኤፌ. 5፥25፤ ዕብ. 9፥14)፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መካከል ተነሣ (ማቴ. 28፥6፤ ሐ.ሥ. 2፥24) ወደ ሰማያት በክብር ያረገ፣ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በታላቅ ክብርና ሥልጣን ዳግመኛ ይመጣል፤ (ሐ.ሥ. 1፥9-11፤ 10፥42፤ 1ቆሮ. 15፥3-6 ኤፌ 4፥8-10፤ 2ጢሞ. 4፥1)።

የቤተ ክርስቲያን ራስ (ኤፌ. 2፥20፤ ቈላ. 1፥18፤ 1ጴጥ. 2፥4)፣ ለአባቱ የታዘዘ ልጅ (ዕብ. 5፥8)፣ መዳናችን የሚገኝበት ፍፁም መንገድ (ዮሐ. 14፥6፤ ዕብ. 12፥2)፣ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር (ቈላ. 1፥18)፣ ከሙታን መካከል በመነሣቱና ወደ ሰማያትም በማረጉ በሰማያዊ ስፍራ በግርማው ቀኝ በመቀመጡ (ዕብ. 1፥1) በሰማያዊ ስፍራ ያስቀመጠንና በሰማያዊ በረከት የባረከን (ኤፌ. 1፥3፤ 2፥5-6)፣ የነፍሳችን ምስክር (1ዮሐ. 5፥10) የኾነና ከዘላለም እስከ ዘላለም ምስጋናና አምልኮ የሚገባው ነው።

እንግዲህ ትምህርተ ሥላሴ ምስጢር ነው ስንል፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ  ዘእንዚናዙ እንደ ተናገረው፣ ከተፈጥሮም ኾነ ከአካል አስተሳሰብ ሁሉ የሚያልፍ፣ ብሩህነቱም አእምሮ ሊፀንስ የሚችለውን ሁሉ የሚበልጥ[1] ነው ማለታችንም ጭምር ነው።[2] ለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት፣ “የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ ለመንገዱም ፍለጋ የለውም። የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን፤ አሜን።” (ሮሜ 11፥33-36) በማለት የሚናገሩለት።

ይቀጥላል …



[1] Poemata de seipso I’, P.G., XXXVII, 984–5.

[2] Vladimir Lossky; The Mystical Theology of the Eastern Church. 1957. Cambridge. Published James Clarke & Co., Ltd p. 33

1 comment: