Saturday 19 August 2023

የጻድቅን ነፍስ የሚሹ ደም አፍሳሾች!

Please read in PDF

“ዶክተር” መስከረም ትባላለች፤ በደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ዙሪያ ስለ ተናገረችው “ፈጠራ ክስ” እጅግ ጥቂት ነገር ማለት ወደድኹ። ... ከጥንት ጀምሮ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ላይ የማያባራ የስም ማጥፋትና የዓመጽ ውሸት ይሰነዘራል። ምናልባት ግን እንደ ማኅበረ ቅዱሳንና ተከታዮቻቸው፣ ደቂቀ እስጢፋኖስን የሚፈራና በእነርሱ ታሪክ ራሱን አስገብቶ ጻድቅ ሊያደርግ የሚሻ ያለ አይመስለኝም። እስጢፋኖሳውያን ትምህርታቸው የጠራ፣ ሕይወታቸው የተመሰከረ ለመኾኑ ለዘመናት ተዳፍኖ፣ እግዚአብሔር በጊዜው በገለጠው ገድላቸው ላይ በትክክል ሰፍሮ አያሌ አጥኚዎችንና ኦርቶዶክሳውያንን እጅ በአፍ አስጭኖ አስደንቆአል።

ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ እስከ ኤልያስ ግርማ፤ ከካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር እስከ ጉንዳጉንዶ ማርያም ገዳም ገድል … ድረስ ትምህርታቸው፣ ሥራዎቻቸውና ገድላቸው ፍንትው ብሎ ወጥቶአል፤ እስጢፋኖሳውያን ከፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ መጀመር በፊት ለመነሳታቸው ዓመተ ምሕረት ለሚቆጥር ሰው አይጠፋውም፤ ማኅበረ ቅዱሳን ግን ሁል ጊዜ እንቅስቃሴውን ከፕሮቴስታንት ጋር ሲያያይዝ ምን ያህል የዓመተ ምሕረት አቈጣጠር ያለመቻል ችግር እንዳለባቸው ወይም ታውረው እውነትን ለመቀበል ድርግም አድርገው መጨፈናቸውን ያሳያል።

  • እስጢፋኖሳውያን ሴሰኞች እንዳልነበሩ፣ ንግሥናን ከቤተ መቅደስ ክህነት ጋር ጨብጫለኹ የሚለው ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ከአንድ በላይ ሚስቶች ያሉት መኾኑን የታሪክ እውነት ይመሰክራል፣
  • እስጢፋኖሳውያን አይሁዳውያን አልነበሩም፤ እንዳልነበሩ የታሪክ ድርሳናት ዋቢ ናቸው፤ ተአምረ ማርያም የተባለው “ድርሰት” እንኳ ይህን አያስተባብልም፣
  • “በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አያምኑም” ብሎ ደፍሮ መናገርም አንድም የታሪክ መዛግብት ካለማንበብ የመጣ ድንቁርና ከመኾኑም በላይ “ዶክተርነት” እንዲህ የሚያጨልም ከኾነ ባፍጢሙ ቢደፋ መልካም ነው ያሰኛል!
  • “እስጢፋኖሳውያን ጠንቋዮች ነበሩ” የሚለው የ”ዶክተሪቱ” ንግግር ያስቃልም፤ ይደንቃልም፤ እውን ዛሬም ድረስ በጥንቈላ የሚታማውና በትክክልም ብዙ ጊዜ የሚገኘው “በመሪጌቶቹ፣ በቀሳውስቱና በመነኮሳቱ” ዘንድ አይደለም ወይ? ወይስ እኛንም ጠንቋዮች ማለት ያምራችኋል?
  • እስጢፋኖሳውያን ከትምህርታቸው አልመለስ ስላሉ ንጉሡ፣ “እንደሚያምኑበት የሙሴ ሕግ በግድያ ቀጧቸው” ብላ የንጉሡን ነፍሰ ገዳይነት መስክራ ስታበቃ፣ ነገር ግን በመግደላቸው ደግሞ መልሳ ንጉሡን ታመሰግናለች። ለመኾኑ አንድ ነገር እንዴት በአንድ ጊዜ እውነትም ውሸትም ሊኾን ይችላል? ንጉሡ በአይሁድ ሕግ እስጢፋኖሳውያንን ከገደለ፣ በሕገ ኦሪት ያለው ከእስጢፋኖሳውያን ይልቅ ንጉሡ ነው ማለት ነው። ንጉሡ የወንጌል አማኝ ነኝ ካለ ግን በምንም መሥፈርት ወንጌል ሰውን ግደል አትልም። እንደው እነርሱ ኦሪታውያን ቢኾኑ ኖሮ፣ ንጉሡ አማኝነቱ የሚታወቀው ለእነርሱ ወንጌል ቢመሰክር “የተሻለ ጽድቅ አደረገ” ሊባል ይችላል እንጂ በመግደሉ በማናቸውም ሚዛን ትክክል ሊኾን አይችልም!

ሴቲቱ “ዶክተር” በጥቂቱ የፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌን “በሕግ አምላክ” ወይም የኤልያስ ግርማን “የደብረ ብርሃን ሸንጎ”ን መጽሐፍ ብታነብብ፣ ምላስዋን በጥቂቱ በገራች ነበር፤ ዳሩ ግን ቅዱስ መጽሐፍ፣ “ደምን ለማፍሰስ የሚሹ ሰዎች ፍጹሙን ሰው ይጠላሉ፥ ደግሞም የቅኑን ሰው ነፍስ ይሻሉ።” (ምሳ. 29፥10) እንዲል፣ ዛሬም ድረስ ንስሐ ከመግባትና ከመጸጸት ይልቅ የዘርዓ ያዕቆብ የግብር ልጆች ደም ማፍሰስን እንደ ኵራት፣ የጻድቅ ሰው ነፍስን በክፉ መሻትን እንደ ጽድቅ ያወራሉ! ጌታ ይገስጻችሁ!

(ስለ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን በዚህ ገጽ የተጻፉ አያሌ ጽሑፎችን ይመልከቱ)

  1. ደቂቀ እስጢፋኖሳውያንና የ“ዲያቆን” ዳንኤል ክብረት የክፋት ሸፍጥ (ክፍል ፩) https://abenezerteklu.blogspot.com/2018/05/blog-post_28.html

እና ሌሎችንም ይመልከቱ።


No comments:

Post a Comment