Sunday, 6 August 2023

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፳፭)

Please read in PDF

በባለፉት ጊዜያት፣ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በተደጋጋሚ የሚቃወምበትንና የሚጥስበትን መንገድ እያሳየን መቆየታችን ይታወሳል። ዛሬም ጸሐፊው እንዴት ባለ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን እንደሚጥስና እንደማያከብር ማሳየት እንቀጥላለን።

1.4.    አዋልድ[1] መጻሕፍትን እንደ መጻሕፍተ መለኮታውያት ማቅረብ ወይም ቅዱሳት መጻሕፍትን በአዋልድ መጻሕፍት ለመተርጐም ማሰብ፦ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ቀደም እንደ ተናገርነው፣ የሕይወት ቃልን በብቻነቱ መያዙን አይስትም፤ ግን ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉት የሕይወት ቃላት ለማዳን፣ የዘላለም ሕይወት ለመስጠት፣ እውነተኛ የቅድስናና የማናቸውም መልካም ነገሮች ኹሉ መለኪያና መመሪያዎች ለመኾናቸው በቂዎች ናቸው ብሎ አያምንም።

መጽሐፍ ቅዱስ የበላይ ባለሥልጣን ነው ይልና መልሶ፣ ቤተ ክርስቲያንን አልያም አዋልድ መጻሕፍትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጐን በማስቀመጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በግልጽ ሲጋፋና ሲንቅ እንመለከተዋለን። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ያለ አዋልድ መጻሕፍት፣ ጎደሎ መልእክት እንዳለው ያለ ፍርሃት ሲናገር እንሰማዋለን።  

የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣንና የአዋልድ መጻሕፍትን ተካካይ በማድረግ ለትምህርትና ለሕይወት መመሪያነት ሲጠቅሳቸው እንመለከታለን። በርግጥ ይህ አቋም የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ ብቻ ሳይኾን፣ የነ“ዲያቆን” ዳንኤል ክብረትም አቋም እንጂ።[2] ይህ አመለካከት ማናቸውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጭ አዋልድ መጽሐፍን፣ ውድቅ ከማድረግ ይልቅ፣ እኩያ ነው ብለን እንድንቀበል ያበረታታናል። በተጨማሪም በቅዱሳት መጻሕፍትና በአዋልድ መጻሕፍት መካከል ግልጽ ልዩነት መኖራቸውን አያመለክትም።

ይልቁን ስለ ጽድቅ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር፣

አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤” (ሮሜ 3፥21-22)

የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ስለ አዋልድ መጻሕፍት ሲናገሩ፣

“ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣ ኃይለ ቃል ያላቸው መጻሕፍተ ታሪክ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተቀብላለች አንልም፤ ከአኹን ቀደም አልተቀበለችም፤ ወደፊትም አትቀበልም እንላለን። … ለምሳሌ፦ አንዳንድ ገድሎችና ድርሳኖች እግዚአብሔርን ክደው ጻድቃንን ቅዱሳንን ወይም እመቤታችንን የተማጸኑትን ሰዎች አማልደው አስማሯቸው ሲሉ ቢገኙ ተቀባይነት የላቸውም።”[3]

ይኹንና የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣

“ … ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።” (ራእ. 22፥18-19)

ከሚለው መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ በተቃራኒ እንድንቆም ያደርገናል።

የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ እንዲህ ያሉ ተግባራትን በግልጥ ሲያከናውን እናየዋለን፤ ለምሳሌ፦

1.4.1.    ምጽዋትን ወይም ቍሳዊ ነገር በልግስና መስጠትን፣ የኀጢአት ማስተሥረያ አድርጎ ለማቅረብ የሚጠቀመው ከሲራክ መጽሐፍ በመጥቀስ ነው።[4]  በቅዱሳት መጻሕፍት ግን ምጽዋት ኀጢአትን እንደሚስተሰርይ የሚደግፍ አንድም ክፍል ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የለም።

1.4.2. እንደ ልቡሳነ ሥጋ ያሉ እንግዳ ፍጡራንን እንደ ትክክለኛ ትምህርትና ፍጥረት አድርጐ የሚያቀርበው እንደ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ ያሉት ፈጠራ ተረቶች እውን ለማድረግ ነው።[5] የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊ፣ ረቂቃንና ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት አሉ ብሎ ማመኑ አያደንቅም። የተክለ ሃይማኖት ገድል፣ ተክለ ሃይማኖት የተባለውን ሰው ክብርና ቅድስና ከፍ ለማድረግ ዐስቦ፣ እኒህን ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት አጥምቋል፣ ቤት አሠርቷል፣ ጠርቶ አዝዞ አመንኩሷል፣ … በማለት ተክለ ሃይማኖትን የልቡሳነ ሥጋ አጋንንት አዛዥ ናዣዥ ያደርጋቸዋል።

ነገር ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እናገራለሁ፣ እሞግታለሁ፣ ተሐድሶአውያንን አሳፍራለሁ የሚል ሰው እንደ የተረት አውራ ይኾናል? ጭራሽ እኒህን ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት እንድንታገል ይመክረናል። እንግዲህ በገድለ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ ያለውን ተራ ተረት እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት አድርጐ ሲያቀርብ አያፍርም።

ይህንና ሌሎችንም አዋልዳዊ ትምህርቶች፣ ልክ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሲያቀርብ እንመለከተዋለን፤ ነገር ግን፦

“ክርስትና ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ሊኖር ስለማይችል የክርስቲያን ስብከት ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሊኾን ይገባል። ስህተት ኹሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊገባ የቻለው መጽሐፍ ቅዱስ በተናቀ ጊዜ ነው።… የተሰቀለውን ክርስቶስን ለመስበክ መጽሐፍ ቅዱስን መያዝ ግድ ነው”[6]

“በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የትምህርት ኹሉ ምንጭና የከበረ የእግዚአብሔር ቃል ነው እንጂ፥ ከሌሎቹ አዋልድ መጻሕፍት ተርታ  የሚሰለፍና ከእነርሱ እንደ አንዱ ኾኖ የሚቈጠር አይደለም፤ ሊኾንም አይችልም፡፡”[7]

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

ይቀጥላል …

 



[1] “አዋልድ” በሴት አንቀጽ የሚነገርና “ወለት” የሚለው የግእዝ ቃል ብዙ ቍጥር ሲኾን፣ ʻሴቶች ልጆች፣ ልጃገረዶች፣ የተዳሩ ሴቶች፣ እንዲሁም ገረዶች፣ ደንገጥሮች፣ ሴት አሽከሮች፣ ብላቴኖች፣ ባሮችʼ ማለት ነው። ቀደም ሲል ቃሉ ለመጻሕፍት ሲቀጸል፥ “የሊቃውንት መጽሐፍ፣ ድርሳናት፣ ተግሣጻት፣ ንባባቸውና ምስጢራቸው እንደ ዐጽቅ (ቅርንጫፍ) ኹኖ ከብሉይ ከሐዲስ የወጣ” ማለት ነው። (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ)፤ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፤ 1948 ዓ.ም፤ ዐዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 391)።

[2] ዕንቍ ወርኃዊ መጽሔት፤ ቍ. 31፤ መጋቢት 2002 ዓ.ም፤ ገጽ 38።

[3] ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ

[4] መድሎተ ጽድቅ፤ ገጽ 236

[5] መድሎ ጽድቅ፤ ገጽ 198

[6] ዮሐንስ ረዳ ጻድቅ፤ መጽሔተ ስብከት፤ 1954 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 18-20

[7] አግዛቸው ተፈራ (መምህር)፤ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እና አባ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ 2015 ዓ.ም፤ ዐዲስ አበባ፤ ርኆቦት አታሚዎች፤  ገጽ 27

2 comments:

  1. God bless you all more!

    ReplyDelete
  2. ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ ጸጋውን ያብዛልህ እድሜና ጤና ይስጥህ

    ReplyDelete