ከሙታን መካከል ስለ መነሣቱ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በምልዓት የሚመሰክሩት ስለ አንዱ
ብቻ ነው፤ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ። ከክርስቶስ በቀር ከሙታን መካከል የተነሣ እንደ ሌለ ከቅዱሳት መጻሕፍት ባሻገር፣ ሌሎችም
መጻሕፍትም በድፍረት ይመሰክራሉ፤ “ስለዚህም ጌታ … በፈቃዱ ሞተ፤ ከተነሣም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም፤
ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታ ይህን አልተናገረም፤ ከሰውም ወገን ማንንም ተነሥ፤ ከመቃብር ውጣ አላለም፤ ዳግመኛ እስከሚመጣባት
ቀን ድረስ ለሰዎች ኹሉ አንድ ኾነው በሚነሡበት ቀን ሙታን ይነሣሉ አላቸው።”
(ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ፤ 1988 ዓ.ም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ምዕ. 59
ክፍል 13 ቊ. 49 ገጽ 209)።
ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተነሥቶአል ስንልም፣ የመዳናችንና የዘላለም ጉዳያችን
የተያያዘውም ከእርሱ መነሣት ጋር ላይነጣጠል የተቈራኘ ነው። መጽሐፍ እንደሚል፣ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤” (1ቆሮ. 15፥14)።
እንግዲህ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ስንመስክር፣ ለምን ጥቅም ተነሣ? ቢባል የሚከተሉት
ጥቅሞች በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘናቸው ናቸው ብለን እንመሰክራለን።
- ክርስቶስ ከሙታን መካከል በመነሣቱ ክርስትና
አሳዛኝ እምነት ከመኾን ተርፎአል፤ ክርስቶስ መከራ መቀበሉን፣ መሰቀሉን፣ መቀበሩን ብቻ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚመሰክሩ
ቢኾኑ፣ ክርስትና እንዴት እጅግ አሳዛኝ ሃይማኖት ይኾን ነበር?! ነገር ግን ክርስቶስ ከሙታን መካከል በመነሣቱ
ክርስትና የድል እምነት ኾኖአል! “ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤” (1ቆሮ.
15፥17) እንደ ተባለ፣ በመነሣቱ ግን ክርስትና ምዕራፉ ዕረፍትና ድል ኾኖአል፣
- ክርስቶስ ከሙታን መካከል ባይነሣ ኖሮ፣ እስከ
ዛሬ ድረስ በጨለማ ውስጥ ነበርን፤ የኃጢአታችንን ዕዳ ማንም ከፍሎ ነጻ ሊያወጣን ባልቻለ ነበር፤ “ክርስቶስም ካልተነሣ … እስከ
አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ።” እንዲል (1ቆሮ. 15፥17)፤ ክርስቶስ ከሙታን መካከል “እኛን ስለ ማጽደቁም ተነሣ” (ሮሜ 4፥25)፣
- ከዚህም የተነሣ ኹላችን በእርሱ በማመናችን አዲስ
ሕይወት ማግኘት ችለናል፤ ይህንም በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በሕይወታችን መከናወኑን ሐዋርያው እንዲህ ይመሰክራል፤ “ … እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር
ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ
ጋር ተቀበርን።” (ሮሜ 6፥4)፤ ለዚህም ነው፣ “በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት መሆን ይጠቅማል” (ገላ. 6፥15)
ተብሎ የተነገረው፣
- ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤
የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤” (ዮሐ. 11፥25)፤ ክርስቶስ ከሙታን መካከል በመነሣቱ አምነውበት ለሚሞቱት
ኹሉ የተረጋገጠ ሕይወትን በመስጠት ተስፋ ሰጥቶአል፤ (1ተሰ. 4፥13)፣
- ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ በአብ ዘንድ ብርቱ ጠበቃን
ወይም ሊቀ ካህናትን አጊኝተናል፤ “እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን
ሃይማኖታችንን እንጠብቅ።” (ዕብ. 4፥14)። እርሱ ከሙታን መካከል በመነሣት ወደ ሰማያት ባያልፍ(ባያርግ)
ኖሮ፣ በድካማችን ሊራራልንና በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋን ሊሰጠን የሚችል ሊቀ ካህናት አይኖረንም ነበር። ዛሬ ግን እርሱ ወደ
ሰማያት በማረጉ ግን በአብ ዘንድ ሊቀ ካህናትና ጠበቃ አለን (1ዮሐ. 2፥1-3)፣
- እርሱ ከሙታን መካከል በመነሣቱ እነሆ፣ ሞትና ሲዖል
ድል ተነሥተዋል፤ የኃጢአት ኃይል ተሰብሮአል፤ የገሃነም ደጆች ፈርሰዋል፤ “ … እንዲሁም፥ “ሞት ሆይ! ድል መንሣትህ
የት ነው? ሞት ሆይ! ሰውን የምትጐዳበት ኀይል የት ነው?” ተብሎአል። የሞት መንደፊያ ኀይል ኃጢአት ነው፤ የኃጢአትም
ኀይል ሕግ ነው። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና
ይሁን!” (1ቆሮ. 15፥55-57)
እንግዲህ እኒህ በክርስቶስ ኢየሱስ ትንሣኤ ያገኘናቸው ጥቂት ጥቅሞች ናቸው፤ ክርስቶስ
ኢየሱስ ከሙታን ተነሥቶአል ብለን ስንናገር፣ ከፍጡር ወገን የተነሣ አንዳችም ሌላ የለም ማለታችንም ጭምር ነውና፤ እርሱ ብቻ ከሙታን
መካከል ተነሥቶአል።
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ
ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment