Wednesday 23 August 2023

አጵሎሳውያንም፤ ጳውሎሳውያንም ወደ ኢየሱስ ኑ!

 Please read in PDF

በዘመናችን አገልጋዮችን ማበላለጥ፣ አንዱን አገልጋይ “ጌታ” ሌላውን “ምንዝር” አድርጐ ማቅረብ ልክ እንደ ጳውሎስ ዘመን ያገጠጠ እውነት ነው። አማኞች የማንም እንዲኾኑ አልተጠሩም፤ በክርስቶስ የተዋጁ አማኞች የክርስቶስ ብቻ እንዲኾኑ የእግዚአብሔር የዘለዓለም ፈቃዱና ዕቅዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፤ ቀና በሚመስል አመለካከት “እኔ የእገሌ ነኝ” የሚሉትን “እሰይ አበጃችሁ” ሲል አንመለከትም።

እንዲያውም ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ የጳውሎስ ነኝ” እና “እኔ የክርስቶስ ነኝ” በሚሉት ላይ ታላቅ የተግሳጽ ዝናብ ያዘነበባቸው ይመስለኛል። በጳውሎስ ዘመን፣ “እኔ የእገሌ ነኝ”  የሚሉ ወገኖች የሚፎካከሩትና የሚከራከሩት እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ “እኔ የክርስቶስ ነኝ” ከሚሉት ወገን እንኳ ራሱን ሳያካትት፣ ከኹሉም ቡድን ጋር ራሱን ሳይወግን በቀጥታ የክርስቶስ ተከታይ ብቻ መኾኑን አጽንቶ ይናገራል።

“ድነናል” የሚሉ የዚህ ዘመን አያሌ አማኞች፣ የቆንቶስ ቤተ ክርስቲያን በወደቀችበት ውድቀት የተያዙ ይመስላል። እንደ ጐበዝ አለቃ ዘመን፣ ኹሉም የራሱ “ሰባኪና ነቢይ” አለው። መጽሐፍ፣ “ሰዎች ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት ለመስማት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ ነገር ግን ለወሬ በመጐምጀት እነርሱ ራሳቸው የሚወዱትን ነገር የሚነግሩአቸውን አስተማሪዎች ይሰበስባሉ።” (2ጢሞ. 4፥3) እንደሚል።

እንዲህ ዓይነት ተከታዮች መብዛታቸውን የተመለከተ “ሰባኪና ነቢያት”፣ ከኢየሱስ ይልቅ ልቀው ለመታየት ሁልጊዜ ራሳቸውን “የመነጋገሪያ አጀንዳ” አድርገው እያቀረቡ ይኖራሉ። ሲታዩ፣ “ስለ ኢየሱስ የሚናገሩ” ይመስላሉ፣ ነገር ግን በሰዎች ልብ ተልቀው ወይም ገዝፈው ይኖራሉ። ለዚህ በዋቢነት ዮናታን አክሊሉ፣ ኢዩ ጩፋና ዳዊት ፋሲልን መጥቀስ ይቻላል።

በዚህ ሰሞን፣ ከኢየሱስ ይልቅ በብዙዎች ዘንድ “ዋና አጀንዳ” የነበረው “ዳዊት ፋሲል” የተባለው ሰው ነው። እርሱ በጅማ “የእውነት ቃል አገልግሎት” አማኝና ያገለግል የነበረ፤ በኋላ “ከቡድኑ” ራሱን አግልሎ የራሱን “ሚኒስትሪ” የከፈተ ሰው ነው። “የእውነት ቃል አገልግሎት” ስለ ተባለው ቡድን፣ የጻፍኹት መጽሐፍ ስላለ ከዚያ ላይ ሰፊውን ነገር ማየት ይቻላል። ግን ስለ ቡድኑና “የዳዊት ሚኒስትሪ” አገልግሎት ጥቂት ልበል።

  • የዳዊት ሚኒስትሪ “የጸጋ” ትምህርቱ አደገኛና የተመረዘ ነው። በርግጥ የሥፍረ ዘመን አማኝ እንደ መኾኑ፣ የጳውሎስ መልእክታት ላይ በማተኰር ሌሎችን ክፍሎች ያኰስሳል (ኹሉም የሥፍረ ዘመን አማኝ ይህን ባያደርግም)። በዚህ የጸጋ ትምህርቱ የተነሣ በሐረር ግብረ ሰዶማውያንን ጭምር አፍርቶአል፣ በናዝሬት ትዳራቸውን የበተኑና ሌላ ጋብቻ የመሠረቱ፣ ጫት ቃሚ አለማውያንን በፍሬ አፍርቶአል፣ በቡሌ ሆራ በዚህ ትምህርት ራሱን ያጠፋ ወንድም አለ፣ በጅማ፣ በአዋሳ፣ በአዲስ አበባ ተመሳሳይ እውነታ አለ፣
  • ኹለቱም ስለ መንግሥቱ ወንጌል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተለየ አስተምኅሮ አላቸው፣
  • የጌታ እራት ከሌለ መዝሙር፣ የቃል ንባብ፣ ስብከት፣ ጸሎት፣ ንስሐ መግባት … አምልኰ አይደለም የሚል ሙግታቸው ደረቅና ጉንጭ አልፋ ነው። ስለዚህም ስትጸልዩ ከጐናችሁ ቁጭ ብለው “ሙድ” ቢይዙ አትደነቁ!

እናም እንደ ቡድንተኛ ሳይኾን በትክክል የክርስቶስ እንድትኾኑ እለምናችኋለሁ፤ የመንፈስ አንድነትን ማጣት ወይም እንዳይኖር ማበላሸት ጤና ቢስነትና ከሐዋርያዊ ትውፊት የማፈንገጥ ሥርዓት አልበኝነት ነው! ከምንም በላይ ደግሞ ከግለሰቦች ደጋፊነት የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ወደ ማክበር እንመለስ! የቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን በግለሰቦች “የአገልግሎት ብቃት” አንተካ!

በምድር ላይ ከከበረ ዕንቁ፣ አልማዝና የከበረ ድንጋይ ይልቅ እግዚአብሔር የሚወድደውና የሚያከብረው በክርስቶስ የመንፈስ አንድነት ያሸበረቀችን ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። እናም አካሉ ውስጥ ነን ካላችሁ፣ ብልቶችን በማበላለጥ “ከእገሌ እገሌ ይበልጣል” በሚል ክርክር ውስጥ አትጠመዱ።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

 

No comments:

Post a Comment