Monday, 31 July 2023

ቅልወጣ የማይርቀው “ሃይማኖታችን”ና ፖለቲካ

 Please read in PDF

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሐዳስያን ከምትወቀስባቸው “ወቀሳዎች” አንዱ፣ ከፖለቲካው ወይም ከቤተ መንግሥት ጋር የነበራት ግንኙነት ነው። ላለፉት 1600 ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱና ቤተ መንግሥቱ ሊነጣጠሉ እስከማይችሉ በሚመስል መንገድ አንድ ላይ ነበሩ። ይህ ሊስተባበል የማይችል ሐቅ ነው፤ በረጅም ዘመን ታሪኳ ሳትከፋፈልና ወንጌልና “በመስበክ” መቆየትዋ እየደነቀን፣ ለብዙዎቻችን እግዚአብሔርን ለማክበርም፤ ብሎም ብዙ ዕድፏን እያየን ደግሞ አንገት ለመድፋት፤ ለመተከዝ የተገደድንበት ብዙ ጊዜም አለ!

አዎን፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰፊው የታሪክ ክፍል፣ መንግሥትንና ቤተ ክርስቲያኒቱን በሽርክና ይዞ ያራምድ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ እጅ “የቤተ መቅደስ መሥዋዕት ከመሠዋት” እስከ ቤተ መንግሥት እልፍኝ ድረስ ሰተት ብሎ የገባ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ “ከቀኖናዬና ከዶግማዬ” አፈነገጡ የምትላቸውን ኹሉ በቤተ መንግሥት በትርና ሰይፍ ትፎንንና ታግዝ፤ ታሳድድና ደም ታፈስስ የነበረ ለመኾኑ አይካድም። አዎን! ቤተ ክርስቲያኒቱ ወንጌል የሰበከች ብቻ ሳትኾን፣ የተቀየመችውን ንጉሥ ከመንበር ታፈልስ፣ ደስ ያሰኛትንና ወደደችውን ደግሞ ታነግሥም ነበር።

ዛሬ ላይ የታሪክ ተራ ፊቱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያዞረ፤ በቀደሙት ዘመናት በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ፣ “ልዕለ ኃያል” የነበረ አቅምና የመወሰን ችሎታዋ የፈዘዘና የደበዘዘ ይመስላል። ይህን ያደረገው ደግሞ አያሌ ምክንያት አለ፤ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል በዘመናችንና በዕድሜያችን ያየነው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ “የብሔር ፖለቲካ ሚናዋን” አለመለየትዋ እንደ ኾነ እሙን ነው።

ለዚህም ገና ያላለቀውን የኦሮሚያንና አኹን ደግሞ በአዲስ መልክ እየተደራጀ ያለውን የትግራይን ቤተ ክህነቶችን ማንሳት ይቻላል። ከዚህም ባለፈ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት፣ አንዳንድ ጳጳሳት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት የተናገሩት ንግግር “ከነውር ያለፈ ተግባር” ከመኾኑም ሌላ፣ አኹን ደግሞ በኹለቱም ክልሎች “ሊቃነ ጳጳሳትን” ለመሾም የሚደረገው “ግብግብ” ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራትን “ተሰሚነት ስጋት” ውስጥ መክተቱ ጥያቄ የሚነሣበት ጉዳይ አይደለም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖትና የፖለቲካን መስመር ማስመር ተስኗት፣ በዚህ መንገድ የምትቀጥል ከኾነ፣ መብት በሚል ስም “ብሔርተኛ ልጆችዋ” የማያልቁ የቤት ሥራዎችን ገና እንደሚያበዙባት ነቢይ መኾን አያሻም!   

በዚሁ ትይዩ ግን፣ ዛሬ ላይ በመሪነት “የተቈናጠጡት ወንጌላውያን ነን የሚሉ መሪዎች” ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጥልቅ “ውድቀትና ግድፈት” መማር ካልቻሉ፣ በጠሉትና በነቀፉት በዚያው ነውር ለመያዛቸው ምንም ጥርጥር የለኝም። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ “ወንጌላውያን የኾኑትንና ያልኾኑትን” በአንድ አዳራሽ ሰብስበው፣ “አንድ ኹሉ” ካሉባት ሰዓት ጀምሮ፣ በአዋጅና በካውንስል እስከ መደራጀት የተኼደበት መንገድ የቤተ መንግሥቱና የወንጌላውያኑ መሪዎች “ከኦርቶዶክስ ላለመማር የጨከኑ” ናቸው ማለት ያስደፍራል።

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የደረሱባትን ውድቀቶች፣ ያስገባቻቸውን እንግዳ ትምህርቶች፣ ድፍርስ አምልኮአዊ ልምምዶች፣ ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ዝቅጠቶችን፣ በሰሜኑ ጦርነት በቤተ ክርስቲያኒቱ አንዳንድ ጳጳሳትና መሪዎች ብሔር ተኰርና ጥላቻ አዘል የነበሩ አድሎዓዊ ንግግሮችዋን … በእውነተኛና ፍሬው በሚታይ ንስሐ ብታርቃቸውና ለወንጌል በእውነትና በቅንነት ጸንታ ብትቆም የማያቋርጥ ናፍቆትና መሻቴ፤ ምልጃዬም ነው። ወንጌላውያንም “መንግሥት በካውንስል ካዳበላቸው”፣ ደስ ከማያሰኝና አጉል ከኾነ ባልንጀርነት ሸሽተው፣ በነጠረና እንደ “ሶላዎቻቸው” ፀዐዳ መስለው በመቆም፣ እየተንደረደሩበት ካለው ጥፋት ቢመለሱ፣ ከኦርቶዶክሳውያንም ጥፋትና ውድቀት ተምረው ለእግዚአብሔር ክብር በሚያመጣው በክርስቶስ ኹሉን አቀፍ ወደ ኾነው የድኅነት ወንጌል ፍጹም ቢያደሉ መልካም ነው ብዬ አምናለሁ። 

አልያ ግን፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ሩቅ፣ ብልጽግናዋም ሕልም ነው!

1 comment:

  1. ጎበዝ በጣም ግሩም መልዕክት ነው።

    ReplyDelete