ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከሰጣቸው “ሥርዓታዊ ትእዛዞች” አንዱ፣ “ሴትም ራስዋን
ባትሸፍን ጠጉርዋን ደግሞ ትቆረጥ፤ ለሴት ግን ጠጉርዋን መቆረጥ ወይም መላጨት የሚያሳፍር ከሆነ ራስዋን ትሸፍን።” (1ቆሮ. 11፥6) የሚል ነው። “ሥርዓታዊ ትእዛዙ”፣ በአምልኮ
ሰዓት ሴቶችም “ኾኑ ወንዶች” ተገቢውን ልብስ ለብሰውና የባሕርይ ሥርዓትን መከተል እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነው።
አንዳንዶች፣ ይህ ሥርዓታዊ ትእዛዝ ለቆሮንቶስ ብቻ የተጻፈ እንጂ የእኛን ዘመን ቤተ ክርስቲያን አይመለከትም ቢሉም፣
ሌሎች ግን የእግዚአብሔር ቃልና ሐዋርያዊ ትውፊቶች ዘመን ዘለቅ
ናቸውና የእኛንም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ይመለከታታል በሚል ጐራ መሳ ለመሳ ቆመው ይሟገታሉ። ይህ አጭር ጽሑፍ እነዚህ ኹለቱ
ሙግቶች መልስ ለመስጠት የተጻፈ አይደለም፤ ይልቁን የታዘዘበት ዓላማ ላይ በማተኰር ለእኛ ያለውን መልእክት ለማስታወስ እንጂ።
በአዲስ ኪዳን ጅማሮ ላይ ከነበሩት አብያተ ክርስቲያናት፣ እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ያለ በችግርና በታወቁ
ኀጢአት የተመላ አልነበረም፤ የዚያኑ ያህል እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በጸጋ የተምነሸነሸና ጸጋን የታደለ የለም ብሎ
መናገር ይቻላል። በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ከነበሩት ችግሮች ወይም ለጳውሎስ ከቀረቡለት ጥያቄዎች አንዱ የአለባበስ ጉዳይ ነበረ።
ለዚህ ችግር ምንጩ ደግሞ፣ በተለይ “ረጅም ጸጉር” የነበራቸው ሴቶች፣ ፀጉራቸውን ሳያስይዙ ወይም ሳይሸፍኑ አዘናፍለው በቤተ
ክርስቲያን ውስጥ መገኘታቸው ነው። በዘመኑ ኹለት ዓይነት ሴቶች ነበሩ፣ አንደኛዎቹ ባሎቻቸውና ልጆቻቸው ላይ ትኵረታቸውን
ያደረጉ፣ ራሳቸውንም በመሸፈን የሌሎችን ትኵረት የማይስቡ ሲኾኑ እኒህ “ማትሮን” ይባላሉ፤ ብዙ ከበሬታም ነበራቸው። ኹለተኛዎቹ
ግን “ሔታይራይ” የሚባሉት ሲኾኑ፣ ሳያገቡ ወይም ነጻ ኾነው ብዙ ወንዶችን በቤታቸውን የሚያስተናግዱና በውጭ ሲታዩም
የማይሸፋፈኑ፣ ፀጉራቸውን ቀለም የሚቀቡ ወይም እጅግ ባጌጠ ሹርባ በመሠራት የወንዶችን ትኵረት በመሳብ የአመንዝራነት ጠባይ
ያላቸው ናቸው። በርግጥም በዚያ ዘመን አለመሸፋፈን፣ የአልቃሽነት ወይም የዘማዊነት ምልክት ነበር።
በሌላ ንግግር በወንጌል ያመኑ አንዳንድ ሴቶች፣ መሸፈኑን ያልወደዱት ልክ አንዲት አመንዝራ ወይም ጋለሞታ ሴት
በመጋላለጥዋ የሌሎችን ወንዶች ትኵረት ለመሳብ እንደምታደርገው እነርሱም የሌሎችን ትኵረት ለመሳብ መሸፋፈንን ወይም መከናነብን
ተዉ። ነገር ግን አማኝ ሴቶች የሚገባቸው፣ እንደ አመንዝራ ሴቶች የሌሎች ትኵረት እነርሱ ላይ እንዲኾን ከመፈለግ ይልቅ፣
በማናቸውም መንገድ ሰዎች ትኵረታቸው ኹሉ ወደ ክርስቶስ እንዲኾን መሥራትና መትጋት ነበረባቸው።
ቅዱስ ጳውሎስ የሴትን ልጅ መሸፋፈን በመደገፍ፣ መደገፉንም በጥቂቱ በኹለት ምክንያቶች ያስረግጣል፤ አንደኛው የሴት
ልጅ መሸፈን ተፈጥሮአዊ ነው፤ በሌላ መልኩ ግን ሴት ስትሸፈን፣ “እኔ ትኵረት ልኾን አይገባም፤ ክርስቶስ ብቻ እንጂ!”
ማለትዋም ነው። የሚገላለጡና የማይሸፋፈኑ ሴቶች፣ ባጌጠ ሹርባና በደመቀ ቀለም የሚዋቡ ሴቶች “እኛ ትኵረት ልንኾን ይገባል”
እያሉ ነው፤ በወንጌል ለሚያምኑ ሴቶች ይህ የተገባ አይደለም፤ ቅዱስ ጴጥሮስም፣ “ለእናንተም
ጠጕርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናጸፍ በውጭ የኾነ ሽልማት አይሁንላችሁ፥” (1ጴጥ. 3፥3) በማለት መክሮአል።
ለአማኞች ኹሉ ትልቁ ትኵረትና ድምቀታቸው ክርስቶስ ሊኾን ይገባል፤ ክርስቶስን በማላቅና በማተለቅ አገልግሎት ውስጥ
እኛ ልንሰወርና ልንጠፋ ይገባናል። ነፍሱን ስለ ክርስቶስ የሚያጠፋ እርሱ ያገኛታል፤ ነፍሱን ከክርስቶስ ይልቅ ለማተለቅ፣ ሳስቶ
ለማኖርና መኖርዋንም ለሌሎች ለማሳየት የሚጥር ነፍሱን አያያትም! አገልጋዮች ሆይ! እናንተ ወይስ ክርስቶስ ትኵረት እንዲኾን
ትፈልጋላችሁ? እናንተ ተሸፋፍናችሁና ተደብቃችሁ ክርስቶስ ግን
እንዲታይና እንዲገለጥ፤ ከፍ እንዲልም ትፈልጋላችሁ? ከዝማሬያችሁ፣ ከስብከታችሁ፣ “ከተናገራችሁት ትንቢት”፣ ካመጣችሁት
መልእክት በኋላ … ራሳችሁን ፈጥፍጣችሁ መጣል ይሻላችኋል ወይም በኹሉ ነገራችሁ ክርስቶስ ዋና ትኵረትና ድምቀት እንዲኾን
ትፈልጋላችሁ? … የቱ ይሻላችኋል? ክርስቶስ ብቻ ቢደምቅ ወይስ እናንተ ብትሸፈኑና ብትሸፋፈኑ?!
“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)
No comments:
Post a Comment