Friday 21 April 2023

ኀጢአትን ይቅር የማለት ጉዳይ! (ዮሐ. 20፥23)

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጣቸው ሥልጣን መካከል አንዱ፣ “ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል” (ዮሐ. 20፥23) የሚል ነው፤ ብዙዎች የዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ዓውዳዊ ትርጕም ለሌላ ነገር ሲጠቀሙበት ብንመለከትም፣ በቀጥታ ሲተረጐም የሚሰጠን ትርጕም ግን፣ “እናንተ ኀጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ኀጢአታቸው ይቅር ተብሎአል፤ ያላላችኋቸው ግን ይቅር አልተባለም” የሚል ነው።

ይህ የሚያመለክተው ቅዱሳን ሐዋርያት በቀጥታ ይቅር የማለትና ያለማለት ሥልጣን እንዳላቸው የሚያመለክት አይደለም፤ ነገር ግን ሥልጣኑ ከእነርሱ የሚመነጭ ሳይኾን ወይም ደግሞ እግዚአብሔር የሐዋርያትን ወይም የአማኞችን ይቅር ማለት ተከትሎ ይቅር ይላል፣ ይቅር ሳይሉ ሲቀሩ ይቅርታ ይነፍጋል ማለት ሳይኾን፣ ወንጌልን በእውነትና በጽድቅ የሚመሰክሩ ኹሉ፣ ኀጢአትን ይቅር የማለትና ያለማለት ሥልጣን እንዳላቸው የሚያመለክት ነው።

ይኸውም፣ ሰዎች አንድ ሐዋርያ ወይም አማኝ የሚነግራቸውን ቅዱስ ወንጌል ሰምተው ቢያምኑና መታዘዝ ቢጀምሩ ኀጢአታቸው ይቅር ይባላል፤ ነገር ግን የሰሙትን ወንጌል ባያምኑና ባይታዘዙ ኀጢአታቸው ፈጽሞ ይቅር አይባልላቸውም ማለት ነው። ምክንያቱም፣ “በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ያላመነ አሁን ተፈርዶበታልና።” (ዮሐ. 3፥18)። ይህም የኀጢአት ይቅርታና ፍርድ የሚያገኘን፣ ክርስቶስን በማመንና ባለማመን የሚመጣ እንጂ ክርስቶስ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር እንዲሉ ወይም እንዳይሉ ፍጹም ሥልጣን እንደ ሰጣቸው አያመለክትም።

ሐዋርያት ወንጌልን ለመላው ፍጥረት ሲያውጁ፣ የይቅርታና የፍርድ አዋጅን ነው የሚያውጁት። ይህን የማወጅ ሥልጣንን የሰጣቸው ጌታችን ኢየሱስ ነው። ይህን የወንጌል አዋጅ ለሚሰማና ለሚታዘዝ ኹሉ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ ይቅርታ አለ፤ በማያምን ኹሉ ላይ ግን ኀጢአቱ በእርሱ ላይ አለ፤ በእግዚአብሔር ልጅ አለማመን ሕይወትን አለማየት ነውና (ዮሐ. 3፥36) የደቀ መዛሙርት ትልቁ ሥልጣን፣ ይቅርታው የሚገኝበትን የመዳን ወንጌል ለሰዎች ኹሉ ማወጅ ነው፤ የኀጢአትን ይቅርታ የሚሰጠው ደግሞ አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ (ማር. 2፥7)።

እንግዲህ እንዲህ ማለት እንችላለን፤ ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ፥ ይቅርታን እንዳላገኙ ለማወጅ ሥልጣን አለን፤ ከዚህ ውጭ ግን በጌታችን ኢየሱስ በማመን ለኀጢአቱ ሥርየት ይኾን ዘንድ፣ የመዳን ንስሐ ያልገባውን ሰው ትድናለህ፣ በጌታችን ኢየሱስ አምኖ ንስሐ የገባውን ሰው አትድንም እንል ዘንድ አንችልም። “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ የሚችል ሌላ የለም” ስንልም፣ እኛ በመዳን ወንጌል ላይ ቆመን፣ ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ የመዳንን ወንጌል ማወጅና በደስታ ሲቀበሉ እንደሚድኑ የተስፋውን ቃል መናገር፣ ብሎም ደግሞ አልቀበልም ሲሉና ሲክዱ ወይም ሲገፉ ግን ይቅርታን እንደማያገኙና ሕይወትን እንደማያዩ ልናስጠነቀቅ ተጠርተናል።

በኢየሱስ በማመን የዘላለም ሕይወት አለ፤ የኀጢአት ይቅርታም ይገኛል፤ በማያምኑና ኢየሱስንና የመስቀል የማዳን መንገዱን በሚገፉ ላይ ግን ኀጢአታቸው ተይዞባቸዋል፤ የኀጢአት ይቅርታም አያገኙም። ከዚህ በዘለለ የኀጢአት ይቅርታ በማናቸውም ሌላ መንገድ አይገኝም! የለምም!

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

No comments:

Post a Comment