Thursday, 30 March 2023

“እርሱ ሊልቅ እኔ ላንስ ይገባል” (ዮሐ. 3፥30)

 Please read in PDF

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኪደተ እግሩ ተመላልሶ ባስተማረበት ወቅት፣ ስለ ራሱ የሰጠውን ምስክርነት የተቀበሉ ጥቂቶች ናቸው። ምስክርነቱን ያልተቀበሉት እርሱ እውነተኛ ስላልኾነ ሳይኾን፣ ብዙዎች ከኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ይልቅ የጨለማ ሥራን በመምረጣቸው ነው፤ (ዮሐ. 1፥6-11)። መጽሐፍ እንደሚል፣ ኢየሱስን የደኅንነታቸው ምንጭ አድርገው የተቀበሉ ሰዎች፥ እግዚአብሔር ለዘላለም ለልጆቹ የሚሰጠውን ልዩ ሕይወት ያገኛሉ። ይህን የማይቀበሉ ግን ለዘላለም ፍርድና ቍጣ የሚጠብቃቸው ናቸው።

መጥምቁ ዮሐንስ በዚህ ረገድ ስለ ኢየሱስ የተናገረው ምስክርነት ግልጽና የማያወላዳ ነው። ስለ ራሱ ሲናገር፣ ራሱን በመካድና በኢየሱስ ፊት ፍጹም በማሳነስ ነው። የመሪዎችና የአማኞች ትልቁ ችግር ራስ ወዳድነት ነው። ሰው ራሱን ካልካደ በቀር ኢየሱስን ማላቅና ከፍ አድርጎ ማክበር አይችልም።

ራስ ወዳድነት ፈርጀ ብዙ ነው፤ አንዳንዶች የራስ ወዳድነት ምንጫቸው ራሳቸውን ከማተለቅና ከገንዘብ መውደድ ሊመነጭ ይችላል። ሌሎች ደግሞ የእግዚአብሔርን ሥራ ለማበላሸትና ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ ከሚሠሩት ሥራ የተነሣ እጅግ ራስ ወዳድ ሊኾኑ ይችላሉ። እኒህና በሌሎች መንገዶች የሚንጸባረቁ ራስ ወዳድነቶች እጅግ አደገኛና መራዥ ናቸው።

መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ ዘመድና የቅርብ ወዳጅ ነው፤ በአገልግሎትም ኾነ በዕድሜ ጌታችን ኢየሱስን ይቀድመዋል፤ በአይሁድ ማኅበረ ሰብና በሮማውያን ባለሥልጣናት ዘንድም ከፍተኛ ተደማጭነት ነበረው።

በተደጋጋሚ ሰዎች ከኢየሱስ ይልቅ ክብሩን በእነርሱ ፊት እንዲገልጥ ዮሐንስን ጐትጉተውታል፤ እንዲያውም ከመጥምቁ ዮሐንስ ይልቅ፣ ኢየሱስ ሊልቅ፣ ዮሐንስ ደግሞ ዝቅ ዝቅ ሊልና ሊያንስ እንደሚገባ ተናገረ እንጂ በመቅናት የኢየሱስን አገልግሎት ሊያደናቅፍ ፈጽሞ አልፈለገም።

አገልጋዮች በሰዎች ልብ ሲገንኑና ሲተልቁ፣ ኢየሱስ በአገልግሎታቸው ይደበዝዛል፤ መሪዎችና አገልጋዮች ዝቅ ዝቅ ሲሉና ኢየሱስን እጅግ ሲያተልቁ ከክርስቶስ የተነሣ በሰዎች ልብ እግዚአብሔር ይከብራል፤ መንግሥቱም ትሰፋለች። መጥምቁ ዮሐንስ ይህን በሚገባ ያስተዋለ የጌታ አገልጋይ ነው።

ፍሬያማ አገልጋይ ለመኾን ዮሐንስ፣ ኢየሱስን ባገለገለበት መንገድ ልናገለግል ይገባናል፤ እንዴት?

1.   ኢየሱስ ከሰማይ ነውና ዘወትር ሊገንና ሊከብር ይገባል፤ እኛ ኹላችን ከምድር ወይም ፍጡራን ነን፤ እርሱ ግን ታላቅና ገናና ከሰማይ የኾነ አምላክ ነው።

2.   እግዚአብሔር የላከው የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራልና፤ እግዚአብሔር መንፈሱን ሰፍሮ አይሰጥምና።” (ዮሐ. 3፥30) የተባለለት ኢየሱስ ብቻ ነው። የእግዚአብሔርን ቃል ሲናገር እንከን የማይገኝለት፣ የታመነና የታተመ ምስክርነት ያለው ኢየሱስ ነው።

ከዚህም የተነሣ እውነትን በትክክል መናገር የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው፤ ምከንያቱም እግዚአብሔርን ያየም ሆነ የመንግሥተ ሰማይን እውነቶች ኹሉ የሚያውቅ እርሱ ክርስቶስ ብቻ ነው። የኢየሱስ ቃል የእግዚአብሔር ቃል በመኾኑ ልንታዘዘው ይገባል። እግዚአብሔር ለማንም የሰው ልጅ ያልሰጠውን መንፈስ ቅዱስን በምልአት ለክርስቶስ ሰጥቶታል። እግዚአብሔር ክርስቶስን ስለሚወደው በምድር ላይ ሥልጣንን ሰጥቶታል። እናም ዘወትር ሊልቅና ሊገንን የሚገባው፣ ትኵረት ሊሰጥም የሚገባው ለክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው!

3.   ኢየሱስ ኹሌም ትኵረት የሚገባው ሙሽራ ሲኾን፣ መጥምቁ ዮሐንስ ደግሞ ሚዜ ነው። የዮሐንስ ደስታ የኢየሱስ ፈቃድና ዐሳብ በትክክል ሲፈጸም ነው። ዮሐንስ ከዚህ በቀር ሌላ ደስታ የለውም። በኢየሱስ አገልግሎት ብዙ ተከታይ ሲገኝ፣ የዮሐንስ ተከታዮች ደግሞ እየቀነሱ መኾኑን ቢያውቅም ዮሐንስ ግን በዚህ እጅግ ደስተኛ ነበር።  ለዚህም ነው “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባኛልና” በማለት የተናገረው።

የአደባባይ ጉባኤያትን የሚያደርጉ መሪዎችና አገልጋዮችን ከምንመዝንበት መመዘኛ ውስጥ አንዱ፣ “በአገልግሎታቸው ይበልጥ አነጋጋሪና ታዋቂ እየኾነ ያለው ማን ነው?  ትኵረት እየሳበስ ያለው ማን ነው? … “ የሚሉና ሌሎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥያቄዎች ናቸው።

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

 

No comments:

Post a Comment