Saturday 15 April 2023

የጴጥሮስ ጌታ ዛሬም ይራራል! (ማር. 14፥66-72)

 Please read in PDF

ቅዱስ ማርቆስ፣ ወንጌሉን ሲጽፍ በቅዱስ ጴጥሮስ ላይ ያተኵራል፤ ነገር ግን ከኢየሱስ በላይ አያልቀውም ወይም ከፍ ከፍ አያደርገውም። ኢየሱስ በተያዘበት ሌሊት ስለ ነበረው ኹኔታ ሲናገር፣ “ጴጥሮስንም፦ ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?” (ማር. 14፥37) ሲል፣ ሌሎቹ ወንጌላት ግን ኢየሱስ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ለኹሉም ደቀ መዛሙርት እንደ ነበር ይናገራሉ (ማቴ. 26፥40፤ ሉቃ. 22፥46)።

በተመሳሳይ መንገድ ጌታችን ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱን በገሊላ እንዲጠብቃቸው መልእክት ሲናገር፣ ማርቆስ አኹንም በተመሳሳይ መንገድ ከሌሎቹ ወንጌላውያን በተለየ ኹኔታ፣ “ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስም፦ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ እንደ ነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው አላቸው።” (ማር. 16፥7) በማለት ትኵረት ሲያደርግ እንመለከተዋለን።

ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ሲገረፍ አይቶታል፤ እንዲሁም የኢየሱስ ተከታይ መኾኑ በብዙዎች ዘንድ ታውቆአል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ስምዖን ጴጥሮስ፣ እንደሚክደው ጌታችን ኢየሱስ በተደጋጋሚ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ጴጥሮስ ምንም እንኳ ኢየሱስን እስከ መጨረሻው ግቢ “የተከተለውም ቢኾን እንኳ”፣ ነገር ግን መንገዶቹ ኹሉ በቅጥፈት፣ በውሸትና ስለ ኢየሱስ “ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም በማለት በመራገምና በመማል” (ማር. 14፥71) በክህደት የተሞላ ነበር።

ስምዖን ጴጥሮስ፣ እንደ ጌታችን ኢየሱስ ትንቢት በአደባባይ በሴቶችና በተወሰኑ ሰዎች ፊት ክዶአል፤ ልክ እንደ ካደ ግን፣ ኢየሱስ “ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ ሲለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።” (14፥72)። ይህ እጅግ አስደናቂ ተግባር ነው፤ የሠራውን ኀጢአት ሊናዘዝበትና አልቅሶ ሊመለስ መውደዱ ለእኛ የሚያስተምር ብርቱ መልእክት አለው።

ብዙዎቻችን ኀጢአት ሠርተን ከመናዘዝና ለመተው ከመጨከን ይልቅ ለመደበቅ እንሞክራለን። ምናልባት ብዙዎቻችን እንደ ጴጥሮስ፣ በጌታ ዘመን ኖረን ልክ ጴጥሮስ ኢየሱስ ሲገረፍ እንዳየው እኛም ተመልክተን ቢኾን፣ ኢየሱስን ደጋግመን ልንክደው እንችላለን። ነገር ግን ማርቆስ እንደሚነግረን ኢየሱስ ጴጥሮስን በልዩ ፍቅር ወደደው፤ ይቅርም አለው፤ ራራለትና ወዶ ተቀበለው።

ይልቁን የክርስቶስን ወንጌልና ክርስቶስ ስለ እኛ የከፈለውን ታላቅ የመስቀል ሥራ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ገበታ፣ በታክሲ ስፍራ፣ በቤተሰብ መካከል፣ በባልንጀሮቻችን ፊት ለመመስከር ብዙ ጊዜ የምናፍርና የምንክድ ነን። የምንፈራውና የምንክድበት ምክንያታችንም ብዙ ነው፣ አንዳንዶቻችን አፍረን፣ ሌሎቻችን ፈርተን፣ ሌሎቻችን ደግሞ ሰዎች እንዳይሳለቁብንና እንዳያሸማቅቁን ብለን የትንሣኤውን ወንጌል ከመመስከር ቸል ያልንባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው።

በዚህ ረገድ ኹላችንም በካድንባቸው፣ በበደልንባቸው፣ በክርስቶስ ባፈርንባቸው፣ ችላ ባልንባቸው ጊዜያት ኹሉ ኢየሱስ የማይለወጥ ታማኝ ወዳጅና አባት ነው፤ እስክንመለስ የሚጠብቅ እረኛም ነው፤ መካዳችንን ረስቶ በፍቅር ሊቀበለንና ሊምረን የታመነ ሊቀ ካህናት ነው። ስለዚህም እንደ ጴጥሮስ በኀጢአታችን ልንናዘዝና ይቅርታ ልንለምን ይገባናል እንጂ መሸፋፈንና መደበቅ አይገባንም። ጴጥሮስን ይቅር ያለው ጌታ ዛሬም መሐሪ ነው!

ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበለ በኋላ፣ በሙሉ ድፍረት በሕዝብ ኹሉ ፊት መሰከረለት። እናንተም፣ ያላፈረባችሁን አትፈሩበት፤ በአደባባይ ለክብራችሁ የተዋረደውን እርሱን በሰዎች ኹሉ ፊት ስሙን በመመስከር ፍቅራችሁን ግለጡለት።

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

No comments:

Post a Comment