ቦረንቲቻ፣ በዋቄፈና አስተምህሮ መሠረት፣ በዓመት ኹለት ጊዜ ዋቃን ለማመስገንና ምልጃ ለመጠየቅ (መስከረምና ግንቦት
አከባቢ) በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚከናወን ባህላዊና አምልኮታዊ ሥርዓት[1]
ወይም የሚከበር በዓል ነው። በአርሲ ኦሮሞዎች ዘንድም በቤተሰብ፣ በከብቶቻቸው ላይ የሚመጣቸውን ማናቸውንም ክፉ ነገር
ለማስወገድ ከሚከበሩ በአላት አንዱ ቦረንቲቻ ነው።[2]
ቦረንቲቻ ክብረ ብኵርና ነው፤ የኦሮሞ ኹለቱ የትውልድ ሥርወ ግንዶች ቦረናና በሬንቱ ናቸው። ቦረና ታላቅ እንደ መኾኑ፣ በኦሮሞ
ዘንድ ብኵርና ታላቅ ክብር ስላለው፣ ለቦረና ልዩ ክብር “ቦረንቲቻ” የሚባል በአል ይከበርለታል።[3]
በበአሉ ዕለት የዋቃ ምሳሌ
በኾነው፣ ጥቁር ጥለት የተጌጡ ልብሶችን በተለይም ወንዶቹ ቡልኮ፣ ሴቶቹ ደግሞ ቆሎሰበታን ለብሰው ይታያሉ። በተለይም በአሉ
ከክረምት ዝናም ጋር በመያያዙ፣ የክረምት ዝናም ደግሞ ከጥቁር ደመና ጋር በመምጣቱ፤ ታላቅ ክብር ነው። ስለዚህም ጥቁር ኮርማ
በማረድ አቀባበል ይደረግለታል፤ ይህም ማለት፣ ለክረምት ዝናም የሚደረገው አቀባበል “ቦረንቲቻ” ይባላል።[4]
Ayyaanni Afraasaa-Gannaa kun Ayyaana Boorantichaa jedhama.[5]
ይህ በአል የሚከበርበትም
ምክንያት፣ የሰላም ዝናም ዝነምልን፣ ውሽንፍር፣ ነፋስ፣ በረድ፣ መባርቅት፣ ጎርፍና አደጋው አያግኘን! በማለት ጥቁር ኮርማ
በማረድ፣ “ዋቃ ሆይ፤ እባክህን ሊመጣ ካለው መጸው አድርሰን” በማለት ይለማመናሉ። በክረምት ወቅት ወደ ወንዝ ወርዶ ኢሬቻ
አይደረግም፤ ምክንያቱም የክረምት መልካ ድፍርስና ሕያዋንና ሙታንን ተሸክሞ ስለሚሄድ። ሙት ደግሞ አያና የለውም፤ ዋቄፈታ ደግሞ
ሙት ወደ ኾነው ወይም ሙት ባለበት ኢሬቻውን አያደርግም።[6]
በሰላሌ አከባቢ በቦረንቲቻ በአል አከባበር ማለትም በጥቅምትና በግንቦት ወቅት ላይ መጠጥ ይደፋል፤ እህል ይበተናል።
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶለሳ እንዲህ
ይላል፣
“የቦረንቲቻ አምልኮ ክርስቲን
በኾኑም ባልኾኑም ኦሮሞዎች እንዲሁም በአማሮች እና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን በግንቦት ወር የቅድስት ማርያም ልደት (ልደታ) ተብሎ
በሚታመንበት ዕለት ይከበራል። ይህን በአል ለማክበር ሰዎች “አድባር” በሚሉት እንደ ቅዱስ በሚታሰብ ዛፍ ስር ይሰበሰቡና ምግብ
(ንፍሮ) ይቀቅላሉ፤ የያዙትን ስጦታም ከቅድስት ማርያም ጋር ለሚያምታቱት ለቦረንቲቻም ይሰጣሉ።”[7]
እናም በግንቦት ልደታ ወቅት
በአብዛኛው ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ፣
- ማርያም በሊባኖስ ተራራማ አገር ከቤት ውጭ ተወልዳለችና፣ እርሱን ለማሰብ ተብሎ የግንቦት ልደታ በአል ከቤት ውጭ (በወንዝ
አከባቢ፣ በዛፍ ሥር፣ በመንገድ ላይ … ይከበራል፤
- በአሉ ሲከበር የበሰለ እህል የመበተን ወይም ቆርሶ የመጣል ልማድ በብዙ አከባቢዎች ዘንድ አለ፣
- ታቦቱ በሚነግሥበት አከባቢ፣ ከብት ታርዶ ታቦቱ እንዲራመደውና አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ደሙን ረግጦ የመግባት ልማድ አለ፤
እንዲሁም ታቦቱ አከባቢ ወንዝ ካለ ወደ ወንዝ ወርዶ በዚያ አከባቢ የመመገብ ልማድና ሌሎችም ልማዶች አሉ።
እንግዲህ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ
ተሐድሶ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ስላደረገ እውነተኛ ተሐድሶ ስናወራ፣ እኒህ ኹሉ ነገሮች በእግዚአብሔር ቃል እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ
ከሚፈልግ እውነተኛ ጥማት የተነሣ ነው።
ይህ ጽሑፍ “ስለ ኢሬቻና አምልኮአዊ
ልምምዱ” ከጻፍኹት መጽሐፌ ገጽ 76-78 የተወሰደ ነው።
[1] ዓለማየሁ ኃይሌ፤ 2007 ዓ.ም፤ ዝክረ
በዓላት፤ ገጽ 71
[2] ሰሎሞን ተሾመ። 2002 ዓ.ም፤ የግድያ
ግጭት ባህላዊ አፈታት በስሬ ኦሮሞዎችና አማራዎች- ንጽጽራዊ ጥናት። ያልታተመ የኹለተኛ ድግሪ ማሟያ ጥናት፤ አዲስ አበባ
ዩንቨርሲቲ፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሁፍና ትምህርት ክፍል፤ አዲስ አበባ። ገጽ 15
[3] ተሊላ
ቡልቡላ እና መርሰን ቦባሳ፤ “DUUDHAA”፤
2001 ዓ.ም፤ በኦሮሚኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ ልዩ የኢሬቻ እትም። ገጽ 9
[4] Dirribii Damusee Bokkuu;
Ilaalcha Oromoo; ገጽ 79
[5] Dirribii Damusee Bokkuu;
Ilaalcha Oromoo; ገጽ 64
[6] Dirribii Damusee Bokkuu;
Ilaalcha Oromoo; ገጽ 79
[7] ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶለሳ፤ የኦሮሞ እና የአማራ
እውነተኛ የዘር ምንጭ፤ 2008 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 24
በዙፋኑ ላይ ሆኖ በለበሰው የእኛነቱ ያለ ማቋረጥ የእለት ተእለት በደላችንን በአስታራቂነት ሀይሉ የሚያስወግደው ጌታ የመንፈስ ቅዱስን ሐብት በዘመንህ ሁሉ ያብዛልህ። ስለ አለሙ መዳን የታረደው የነጩ በግ (የኢየሱስ) ማዳን እንኩዋንስ በእነዚህ መጨረሻቸው ጥፋት፤ ሆዳቸው አምላካቸው፤ ክብራቸው በነውራቸው ሀሳባቸውም ምድራዊ በሆኑና አማልክቶቻቸው በበዙ ወሮበሎች ቀርቶ አለሙን በምድራዊ ስልጣናቸው ባንቀጠቀጡትም ቄሳሮች ሊገታና ሊቆም አልቻለም። ክብር ለብቸኛው መድሀኒት በጸጋ ላይ ጸጋን ላበዛልን ከመለኮቱ ሳይለይ በፈቃዱ እኛን ሆኖ ከሁለት ሞት ወደዘለአለም ሕይወት ላሸጋገረን ይሁን። ይህን ላልተረዱትና መድሀኒት ፍለጋ አማልክቶቻቸውን ላበዙትም የተስፋን(የማስተዋል) ልብ ይስጣቸው እላለሁ።
ReplyDelete