Friday 27 January 2023

የአዳዲሶቹ ጳጳሳት ሹመት ስጋት፣ ተስፋዬና ትዝብቴ

Please read in PDF

ጌታ እግዚአብሔር በሉዓላዊ አምላክነቱ፣ ክፉውን ነገር ኹሉ ለክብሩ ሊጠቀምበት፣ ወደ በጎ እንደሚያመጣው እናምናለን፤ ኀጢአት እንኳ ከእግዚአብሔር የሉዓላዊነት ወሰን አልፎ አያውቅም፤ እናም በምድራችን ላይ የምንሰማውን መለያየትና ጥቅመኝነትን ጌታ እግዚአብሔር አጥፍቶ፣ ለሕዝባችን መታነጽና ለክብሩ ታላቅነት እንዲሠራ ከኹሉ በፊት አስቀድመን እንማልዳለን።

አዎን! እግዚአብሔር የፈርዖንን ልበ ደንዳናነት፣ ለሕዝቡ ጥበቃና ትድግና እንደ ተጠቀመበት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው ስንል፣ በመላለሙ ላይ መጋቢና ሠራዒ፤ አስተዳዳሪና ጌታ ነው እያልን ነው፤ ስለዚህ የምድራችን ነገር የሚገደውና የሚያስብልን ተንከባካቢና ጻድቅ ጌታ አለን ማለታችንም ነው!



የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ፣ በዚህ ሳምንት “ሕገ ወጥ ናቸው” ባሉት የጳጳሳት ሹመት ላይ ውግዘት አስተላልፈዋል። አዲሶቹ የተሾሙት ጳጳሳት ደግሞ፣ በዚህ መንገድ የሄዱበትን አካሄድ ምክንያቱን ሲናገሩ፣ “በቋንቋዎቻቸው ሕዝቦች ወንጌል ሊሰሙ ይገባል” የሚል ማጠንጠኛ አለው።

በቋንቋቸው ሕዝቦች መገልገል አለባቸው መባሉ እውነት ቢኾንም፣ ይህን ግን በስህተት መንገድ በመጠየቅ የሚፈጸም አይደለም፤ ስህተት በስህተት መንገድ አይስተካከልምና። ወንጌልን መስማት በገዛ ቋንቋ መኾኑን ማንም የማይክደው እውነት ነው፤ ይህን ለማድረግ ግን በሰው ሥርዓትና የፖለቲካን በትር መጠቀም፣ የዓመጽን መንገድ መምረጥ፣ ሰዎችን ለጥፋትና ለደም ማፋሰስ መጋበዝ፣ ኅብረትን በሚንቅና በሚንድ መንገድ መሄድ … አግባብ ነው ብዬ አላምንም።

ለዚህ ውጤት ማሳያ፣ በምዕራብ ወለጋ ከምትገኘው ጊምቢና ሌሎችም አንዳንድ ከተሞች ላይ የሚደረገው እንቅስቃሴና ቅስቀሳ አሉታዊ ነገሩ ያመዝናል። በተለይም የወለጋ መስመር በብዙ መልኩ በብዙ ደም የተነከረ፣ በሰቆቃ የተዋጠ፣ አያሌ ውድመት የደረሰበት … መስመር ነው። እናም “አዳዲሶቹ ተሿሚዎች ጳጳሳት” በገዛ ቋንቋው እናስተምረዋለን ያሉት ሕዝብ፣ ደሙ እንዳይፈስ፣ በሞት እንዳይቀጠፍ፤ ምድራዊና ሰማያዊ ኑሮው እንዳይጐሳቆል ሊጠነቀቁለት ይገባል። ሰዎች ኹሉ ወንጌልን እንዲሰሙ መትጋት እንጂ፣ የዘረኝነት ፖለቲካ በደቆሳትና ድህነት ባደቀቃት ምድር ላይ ሌላ ሃይማኖታዊ ጥላቻን መዝራት አይገባም፤ እንኳን ሃይማኖታዊ ግጭት ተጨምሮበት፣ የዘረኝነቱን ጦስ ገና አልተላቀቅነውምና፤ ይህ ጽኑ ስጋቴ ነው።

ሌላው ተስፋዬ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ይህን እንደ መልካም ዕድል ከተጠቀመችበት የሚፈነጥቅ አንድ ተስፋ እንዳለ አስተውላለሁ። በርግጥ አዳዲሶቹ ተሿሚ ጳጳሳት “ለቅዱስ ወንጌል ትምህርትና ሕይወት ሩቅ” መኾናቸውን አውቃለሁ፤ እንዲሁም ከጥቂቶቹ በቀር፣ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ውስጥም ያሉት ጳጳሳት እንዲሁ። ዳሩ ግን እውነተኛ የወንጌል እሳት በምድሪቱ ላይ እንዲቀጣጠል ይህ ምክንያት ይኾንን? የሚል ተስፋ አጭሮብኛል፤ ይህ እንዲጭርብኝ ያስገደደኝ፣

1.   የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሲኖዶስ ባስተላለፉት ውግዘት ውስጥ፣ ሌሎች መንፈሳዊ ኅብረቶችን ወይም የእምነት ተቋማትን አዎንታዊና አጋራዊ በኾነ መንገድ የመቀበል ትክክለኛ አዝማሚያ አሳይተዋል። እንደ እኔ ግምት ይህን በኦርቶዶክስ ውስጥ የታየ አዲስ ፍንጣቂ ተስፋ ነው።

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ በአብዛኛው የምትታወቀው ሌሎችን በማግለልና ራስዋን ብቸኛ የመዳን መንገድ አድርጋ በማቅረብ ነበር፤ አኹን ግን ከዚህ ፈቀቅ ብላ ሌሎችን እንደ አጋር መቁጠርዋ ይበል የሚያሰኝ እውነት ነው። የተሐድሶ አንዱ እርምጃ ልበ ሰፊነትና እውነትን በትክክል መፈተን ነውና!

2.   በቋንቋዎች ማገልገል የሚለው ዐሳብ፣ ቀለል ብሎ ቀርቦአል፤ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከግዕዝ ቋንቋ የበላይነት ይልቅ (በግሌ ግዕዝ ጠል አለመኾኔ ይታወቅልኝ) ወንጌል ለኹሉ ደግሞም በሚሰሙት ቋንቋ እንዲሰበክ በር ይከፍታል የሚል ጽኑ ተስፋ አለኝ። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ምናልባት ለአስተዳደራዊ ተሐድሶ ምክንያት ይኾንን?

ከዚህ ባሻገር በውስጤ የተፈጠረ ትዝብትም አለ፤ ሲኖዶሱ፣ ለአዲሶቹ ጳጳሳት ምላሽ የተፋጠነውን ያህል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መሪዎች ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ ላደረጉት የእርስ በርስ ጦርነት አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠታቸውን ሳስብ እጅግ እንድታዘብ አድርጎኛል። ኹለቱም አካላት ከሥልጣናቸው ይልቅ የሕዝቡ እንደ ቅጠል መርገፍ ምነው አላሳሰባቸው?

እንዲሁም የትግራይ አብያተ ክርስቲያናትም ጉዳይ ተያይዞ ቢታይና መፍትሔ፤ እልባት ቢያገኝ ምናለበት? አልያ ግን የአንድ ወገን ብቻ ሳይኾን፣ መንታ በኾነ መንገድ በኹለት ቡሃቃ የተቀመጠ፣ የኃጢአት እርሾ እንዳይኖር ፍርሃቴ ነው! ጌታ ለምድሪቱ ምሕረት ያድርግ፤ አሜን።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment