Wednesday 18 January 2023

የመንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ መውረድ

Please read in PDF

በጥምቀት ወራት ከሚነሡት ዐሳቦች መካከል አንዱ፣ “ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤” (ማቴ. 3፥16) የሚለው ቃል ይታወሳል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በጌታችን ላይ ወረደ።

ጌታችን ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ነው፤ ደግሞም ፍጹም ሰው ነው፤ በአምላክነቱ መታዘዝ የሌለበት ጌታ በፍጹም ሰውነቱ ለመንፈስ ቅዱስ ታዘዘ፤ ደግሞም ተገዛ። መሲሑ በመስቀል ሞት በመታዘዝ ተሰቅሎ ያድነንና በጽድቅ መንገድም በመታዘዝ የሕግ ፍጻሜ እንዲኾን ለመቀባቱ ምልክት ይኾን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ ወረደ።

በነቢይ መጽሐፍ፣ ስለ መሲሑ እንዲህ ተብሎ ተነግሮለታል፤ “የእግዚአብሔር መንፈስ፥ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ፥ የምክርና የኃይል መንፈስ፥ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” (ኢሳ. 11፥2) መሲሑ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱ፣ በሰውነቱ ፍጹም ለእግዚአብሔር መታዘዙን የሚያመለክት ነው። የእግዚአብሔር ወልድ ትህትና እጅግ አስደናቂ ነው።

ስለ እግዚአብሔር ባሕርያት በተደጋጋሚ ስናጠና፣ ስለ ትህትናው እምብዛም ተነግሮን አናውቅም፤ ዳሩ ግን ስለ መዳናችን ዘወትር ስናወሳ ትዝ የሚለን እውነት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍጹም ትሁትነትና የእኛን ሥጋ ከመልበሱ ጀምሮ እስከ ውርደት ሞት የታዘዘው መታዘዝ ፍጹም ትህትናን ማዕከል ያደረገ መኾኑ ነው።

ይህን እውነት ማዕከል አድርገን፣ ስለ ርግብ ስንናገር፣ ርግብ በአይሁድ ማኅበረ ሰብ ዘንድ የገርነትና የሰላም ምልክት ናት። መንፈስ ቅዱስ ወደ መሲሑ ሲመጣ፣ እንደ ርግብ በመውረድ ነበር ስንል፣ መጥምቁ ዮሐንስን ጨምሮ ኢየሱስ ይመጣል ብለው ጠብቀው የነበረው፣ ታላላቅ መንግሥታትን ድል በመንሣት፣ ከሮም ቅኝ ግዛት አይሁድን ነጻ በማውጣት፣ መሲሐዊ ድል ነሺ መንግሥትን በመመሥረት … በኃይል እንደሚመጣ ጓጉተው ነበር።

ነገር ግን መሲሑ የተገለጠው፣ “ሕዝቡም ሁሉ ከተጠመቁ በኋላ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ።” (ሉቃ. 3፥21) እንዲል፣ እንደ ማንኛውም ኀጢአተኛ ኢየሱስ ተሰልፎ፣ ከታላቅ ትህትናው የተነሣ ሰው ኹሉ ከተጠመቀ በኋላ ኢየሱስ በመጨረሻ ተጠምቆ ነው። ፍጹም ትሁቱ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲታይ፣ ከኀጢአተኞች እንደ አንዱ ተቆጥሮ፣ እኛ ኀጢአተኞችን ከትዕቢት ከፍታ አውርዶ በትህትና ወደ እግዚአብሔር እግር ሥር ይወስደን ነው።

ቤተ ዘመዶቹ ሳይቀር እንኳ፣ ኢየሱስ በኃይልና በሥልጣን፣ በአስፈሪ ግርማ እንዲገለጥ ደጅ ቢጠኑትም እርሱ ግን በፍጹም ትህትና ተገለጠ። በድጋሚ፣ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ ስንል፣ ትሁቱንናን በትህትናውም እጅግ አስደናቂ የኾነውን ጌታ በማስተዋል እንድንከተለው መንፈስ ቅዱስ እያስተማረን ነው። እንዲህ አለ መሲሑ፣ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤” (ማቴ. 11፥28-29) አለ፤ ሸክማችንን የሚሸከምልን ጌታ በትህትናው እጅግ፤ እጅግ ትሁት የኾነው ጌታ ነው፤ ስሙ ይባረክ፤ አሜን!

No comments:

Post a Comment