Sunday 5 February 2023

ለዮናስ ነነዌ፤ ለዮናታን አክሊሉ ኦርቶዶክስ፣ ግድ አይደሉም!

Please read in PDF

 እግዚአብሔር፣ ታላቅ ኀጢአት ሠርታ ስለ ነበረችው ነነዌ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “እኔስ ቀኛቸውንና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሀያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ ለነነዌ አላዝንምን?” (ዮና. 4፥11)። ዮናስ ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ነቢይ የነበረ ቢኾንም፣ ለነነዌ ግን እንጥፍጣፊ ርኀራኄና ሃዘኔታ አለማሳየቱ እጅግ አስደናቂ ነገር ነው። ነቢይነት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ በግልጥ የእግዚአብሔርን ዐሳብና ፈቃድ የመናገርን ያህል፣ ስለ ኀጢአት ደግሞ ሲገስጹና ሲቈጡ የእግዚአብሔርን የርኅራኄ ልብ ሳይጥሉና ፍጹም እየሳሱ መኾን ነበረበት።

ዮናስ በተደጋጋሚ የነነዌን ጥፋት የተመኘበት ምክንያቱ፣ ራሱ ውሸተኛ እንዳይኾን ተገብዞ ነው፤ ሲናገርም እንዲህ ይላል፣ “በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህ አልነበረምን? አንተ ቸርና ይቅር ባይ፥ ታጋሽም፥ ምሕረትህም የበዛ፥ ከክፉው ነገርም የተነሣ የምትጸጸት አምላክ እንደ ሆንህ አውቄ ነበርና” (4፥2)፤ ዮናስ ለነነዌ ፍርድን እንዲናገር የላከው እግዚአብሔር ነበረ፣ እምቢ አለ፤ እግዚአብሔር መልሶ በተአምራት ወደ ነነዌ ላከው፣ አኹንም ሊናገር አልወደደም፤ ልክ እርሱ ፍርድ ሲናገር፣ እግዚአብሔር ወዲያው ይቅር ብሎ፣ ለራሱ ሐሰተኛ እንዳይኾን ተገበዘ፤ ራሱን ከእግዚአብሔር ይልቅ ዐሳቢና ዐዛኝ አድርጎ አቀረበ።

በተደጋጋሚ እንደምናስተውለው ለነነዌ የዮናስ ልብ ጨካኝ፤ እግዚአብሔር ግን አዛኝ ነበር። እግዚአብሔር ርኅረኄውን ለነነዌ ያሳየው፣ የነነዌን ኀጢአት ችላ ብሎ አይደለም፤ በንስሐ አልያ ቀጥቶ ሊመልስ ወድዶ ነው። ዮናስ ሳይተክላት፣ ውኃ አጠጥቶ ሳያሳድጋት በአንዲት ቀን በቅላ ለደረቀች ቅል ያሳየውን ርኅራኄ ያህል፣ በነነዌ ላሉ አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሰዎች አለማሳየቱ፣ “ምን ዓይነት አገልጋይ ነው?” ያስብላል። የትንቢቱ መጽሐፍ የሚያበቃው ነነዌን እንድትጠፋ እንደ ተመኘና እንደ ጐተጐተ ነው።

የዚህ ትንቢት መጽሐፍ በተመሳሳይ መልኩ፣ ለኦርቶዶክስ ከኹለት ቦታ መሰንጠቅ፣ ትንቢት ሰምቼ ተናገርኹ ከሚለው ከዮናታን አክሊሉ ጋር መመሳሰሉ አስደንቆኛል። ዮናታን ትንቢቱን የሚናገረው በታላቅ ድፍረትና በትዕቢት፣ ጨርሶ በማይራራ ልብ ነው። አንዳችም መልካም ነገር እንደማይገኝባት ጭምር ለኦርቶዶክስ አንዳችም ግድ በማይሰጥ ልብ! ምንም ያህል ኦርቶዶክስ አያሌ ተሐድሶ የሚያስፈልጋት ነገር እንዳለ ባምንም “ፍጻሜዋን እንደ ዮናታን ትንቢት” እንዲያደርገው ለቅጽበት በግሌ ተመኝቼ አላውቅም። ዮናታን አክሊሉ፣ እንዲህ ያለውንም ትንቢት “የቤተ መንግሥት ቅልጥም ሲቀለጥም የሰማው” እንጂ ከእግዚአብሔር የሰማው ነው ብዬም አላምንም!

ደግሜ እላለሁ፤ በተሰቀለው ክርስቶስ የማምን ክርስቲያን ነኝ፤ እናም የሌሎች መከፋፈል፣ መለያየት፣ መባላት፣ መሰነጣጠቅ … በዚህም ምክንያት ደም መፍሰስና የሰዎች ሞት የሚያስደስተኝ አስመሳይ፤ ግብዝ አይደለሁም! ኦርቶዶክስን በዚህ ልክ ማዋከብና ማዋረድ በፍጹም ትክክል አይደለም፤ ዮናታን በዮናሳዊ ርኅራኄ አልባ ልብ በኦርቶዶክስ ላይ እንዲህ መዘበቱ ኢ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው!

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኒቱን በቃሉና በመንፈሱ እንዲጐበኛት ምልጃዬ ነው፤ ዘር ተኰር ክፍፍሉም ከመካከልዋ እንዲነቀል፤ አንድ ኾና በክርስቶስ ወንጌል ዳግም ትዋጅና በዚህም የእግዚአብሔር መግቦት ይበዛላት ዘንድ ዘወትር መሻቴ ነው! ቅዱስ ጳውሎስ ለአዲስ ፍጥረት አማኞች በታላቅ ጸሎት እንደ ተናገረው፣ “በዚህም ሥርዓት በሚመላለሱ ሁሉ ላይ በእግዚአብሔር እስራኤልም ላይ ሰላምና ምሕረት ይሁን።” አሜን። 

No comments:

Post a Comment