Sunday, 22 January 2023

“ጳጳሳቱ”ም እንደ “ጐበዝ አለቃ”

Please read in PDF

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ለቍጥር በሚታክቱ የጐበዝ አለቆች ሥር ወድቃ ታውቃለች፤ እኒህ የጐበዝ አለቆች “ለሕዝባቸው” ዘለላ ርኅራኄ የላቸውም፤ ሕዝባቸውን ቆራርሰው ከማስጨነቅ፤ የራሳቸውን ልድልድና ምቹ የዙፋን ሠረገላ ከማመቻቸት የዘለለ፣ ሕዝቡን ሲፈይዱ አልታዩም። እንዲያውም “የሰኞ ገዳይ”፣ “የማክሰኞ መጋቢ” ተባብለው በሳምንቱ ቀናት ላይ ተሿሹመው አስጨናቂ አስገባሪዎች እንደ ነበሩ ዛሬም ድረስ የምናስተውለው እውነታ ነው።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እንዳለመታደል ከዚህ ዕጣ ፈንታ አላመለጠችም። ለዘመናት ቤተ ክርስቲያኒቱ “በአንድ ቋንቋ ብቻ ከማስተማር ተቆጥባና የአስተምኅሮ ዝንፈቷን አስተካክላ” ለምድራችንና ለአኅጉራችን ብሎም ለመላለሙ “የፍሬ በረከት ትኾን ዘንድ” የተለያዩና በየዘመናቱ ያላቋረጡ የተሐድሶ ጥሪዎች ሲደረጉላት ነበር። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያቱ ለዘመናት ከመስማትና እንከኖቿን ከማስተካከል ይልቅ በግብዝነት የእልኸኝነት መንገዷን ገፍታበት ቆይታለች።

ነገር ግን “አዲሱና ሥልጣን በእጁ ከጨበጠው መንግሥት ጋር ያበረውና የተባበረው ትውልድ” ጉዞዋን ከእባብ ወደ ዘንዶ አፋጥነው አሳደጉላት እንጂ በሚሻል ነገር አልፈየዱላትም። ከሰሞኑ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው “የኦሮሞ ጳጳሳት ሹመት” ጉዳይ፣ በአደባባይ በ”ጳጳስ” ሳዊሮስ “ፓትያርክነት” አዳዲስ ጳጳሳት ሹሞ ብቅ ብሎአል። ይህ ተግባር እንደ አገርም፤ እንደ ቤተ ክርስቲያንም ታላቅ ውርደት ነው።

እንደ አገር ሳስበው፣ ካልተዘነጋ በቀር ቤተ ክርስቲኒቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት በአገር ውስጥና በውጭ ሲኖዶስ በሚል ለኹለት ተከፍላ የነበረችበትን ታሪኳን “በዕርቅ ቋጭታ” አንድ ኾና ነበር፤ ነገር ግን የጠብና የመከፋፈሉን ዘመን ያህል እንኳ ሳይቆይ፣ በአጭር ተቋጭቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዳግም “ለኹለት ተከፈለች፤” ለእኔ ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማለት ያለ ሲኖዶሱ ፈቃድ የሚደረገው፣ የጳጳሳት ሹመት የመከፈል ያህል ይሰማኛል። የወሊሶው ጳጳስ ይህን ያህል ድፍረትን ያገኘው ከመንግሥት ጋር ባለው ሽርክና ነው የሚል ጽኑ ጥርጣሬ አለኝ! ይህ ለፖለቲካውም መጠንዛት ዓይነተኛ ማሳያ አይኾንም ግን?!

እንደ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ይህ ከውርደት ያለፈ መርገምም ነው፤ ቤተ ክርስቲያን በማናቸውም መንገድ ከመንግሥት ጋር መሻረኳ ፍጹም ይጎዳት እንደ ኾን እንጂ፣ ዘለላ ታህል የሚፈይዳት አንዳችም ነገር የላትም። የኦርቶዶክስ አዲሱ ተገንጣይ “ባለ ጳጳሳት ቡድን” ይህን እውነት፣ የመከፋፈልን መዘዝ “በአጭር ዕድሜ እየተነካከሰ” ካለው ከወንጌላውያን(ከፕሮቴስታንት) “ኅብረት” ሊማር በቻለ ነበር። ነገር ግን ያልታደለው “የሳዊሮስ ቡድን” በመከፋፈል መንገድ ነጎደ!

ልዩነትን መፍጠርና የራስን ምኞት መከተል የተገለጠ ኀጢአት ነው፤ ክፉ ምሳሌነትም ነው። ይልቅ በዚህ ጊዜ በርን ገርበብ አድርጎ ለውይይት መቀመጥ፣ የሕዝባችንን ሰቆቃ መመልከት፣ በልዩነት ቋፍ ላይ ያሉትን “ትግራይንና ኢትዮጵያን” በሰላም ቃል ማሸማገል፣ ወንጌል ላልደረሰውና በተለያዩ የፍጡራን አምልኮ ለተዋጠው ማኅበረ ሰብ መራራትና ወንጌል ማድረስ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለውን የፍጡራንና የገድላትን ገናናነት ማስወገድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰዎችና ከቤተ ክርስቲያን ቃል በላይ እንዲከበር መሥራት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን መፍራትና ሌሎች እጅግ አያሌ የቤት ሥራዎች እያሉ የጎበዝ አለቆችን መንግሥትን ታምኖ ማሠማራት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ብሎም ለአገር እጅግ ክፉ መንገድ ነው፤ እስራኤልን ለኹለት የከፈለው ኢዮርብዓም፣ በእስራኤል ላይ ያደረገው መቼም መልካም አልነበረም! እናም ሳዊሮስን እግዚአብሔርን ይገስጽህ ከማለት በቀር ምን እንላለን?

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ግን አኹንም ቀኑ አልባጀባትም፤ ፍትሐ ነገሥታዊ አንቀጾችን ጠቅሶ ከመወጋገዝና ከመገፋፋት፤ ለወንጌል እውነት በመሸነፍ ሕዝቡ የሚሻውን ወንጌል ለመናገር መድፈርና ቤተ ክርስቲያኒቱ መልሳ ራስዋን ለማየት ጊዜው አኹን ነው ብለን እናምናለን! ወንጌልን መግፋት፣ ኢየሱስን መተው ኦርቶዶክስን ከዚህ በላይ ዋጋ እንዳያስከፍላት እፈራለሁ፤ የዚህ ኹሉ መፍትሔው ኢየሱስን ማክበር፣ የተገፋው መስቀሉንና የመስቀሉን ሥራ በቦታው መመለስ፣ ዕድፈትና ኀጢአተኝነትን መጠየፍ ይገባታል!

ጌታና እውነተኛ እረኛው ኢየሱስ ለሕዝባችን ይራራ! አሜን።

1 comment: