Saturday 27 February 2021

ኢየሱስ ጣዖት አይደለም!

Please read in PDF

ዘጠነኛ ክፍል እንግሊዘኛ ያስተምሩን አስተማሪያችን ይኅደጐ ይባላሉ፣ ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ጥቊር ሰሌዳውን በሚገባ ደጋግመው ያጸዱት ነበር፤ አንድ ቀን አንዱ ተማሪ፣ “ቲቸር ለምን እንዲህ ውልውል አድርገው በሚገባ ያጸዱታል?” ብሎ ጠየቃቸው፤ እነርሱም፣ “በሚገባ ባልታጠበ ትሪ ምግብ ትበላለህ?” ብለው ጥያቄውን በጥያቄ መለሱለት። እኔም ዛሬ ሳስተምር፣ እንደ ቀደመው አስተማሪዬ በሚገባ መወልወልን ልማዴ አድርጌ አስቀርቼዋለሁ። ወደ ክርስትና ስመጣ የእኒህ አስተማሪ “መርህ” በዋዛ የሚታለፍ አይደለም።

ክርስትና ከምናቀርበው አገልግሎት ይልቅ የምናቀርብበትን ልብና ሕይወት ቅድስና ይሻል። ከሰሞኑ ቊጥራቸው ቀላል ያይደለ የቅርብ “አማኝና አገልጋይ” ወጣት ትውልዶች  እየሞዘቁ “ስለሚዘምሩ” አንዳንድ ዘፋኞች “ኢየሱስን ካገለገሉ ምን ችግር አለው?” ሲሉን፣ የዚያኛው ትውልድ ነባር “አማኝና አገልጋይ” ጐልማሶች “እየጶተለክን መንፈሳዊነትን ማን ከልክሎን?” ሲሉ በተደጋጋሚ ሰምተናቸዋል። እነርሱ እንዲህ ሲሉ ባያፍሩ፣ እኛ ማፈራችን አይቀርም። ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ የሚማርከውና የሚያድነው ሕይወታችንን ነው፤ በወንጌል ውስጥ ያነበብነው ኢየሱስ፣ አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱን በሕይወት ሲለውጣቸው ነው። ኢየሱስ ያልተለወጡ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት አላሰማራም።

የምናገለግለው ወንጌል ያልተሸቀጠ ከኾነ፣ የምናገለግለው ለኢየሱስ ክብር ብቻ በቆመና ባልተሸቀጠ ሕይወት ነው። ድካምንና ኀጢአተኝነትን “መጽሐፍ ቅዱስን አንብበናል” ለሚሉቱ መለየት አለመቻላቸው እጅግ ምስኪንነት ነው። ያለፈውን ሕይወታችንን “የነበረ ወይም ነበርኩበት” ብለን ካላፈርንበት፣ በእርግጥ የመዳን ወንጌል እንደገና ሊታወጅልን ይገባል፤ ምክንያቱም የሚያውቅ በሚመስል የአለማወቅ ጨለማ ውስጥ ነንና። ኢየሱስ ቅዱስ ነው፤ ወንጌሉና ሕይወቱም እንከን የሌለባቸው ፍጹማን ናቸው፤ ስለዚህ አገልጋዮቹም በተገለጠ ነውር የማይመላለሱ፣ በስውር ዕድፈትም የማይልከሰከሱ መኾን አለባቸው።

ስብከታቸው አስደማሚ  ሰዶማዊ “ሰባክያን”፣ ዘፈን ያልተዉ “ዘማሪያን”፣ ሴሰኛ “ምርጥ ጸሐፍት” … እና አጋፋሪዎቻቸው ሊያስተውሉ የሚገባቸው ታላቅ እውነት፣ ኢየሱስ ጣዖት አይደለም፤ ካልጠራ ሕይወት የቱንም ቢቀበል የማይጠየፈው ጣዖት ነው። ኢየሱስ ግን ቅዱስ ነው፤ ካዳነው፣ ከዋጀው፣ ከተቤዠው፣ የራሱ ገንዘብ ከኾነው፣ ከጸጋው ዙፋን ሥር ከማይጠፋው… ሕይወትና ኑሮ ነው አገልግሎት የሚሻው። በቅድስናና ኢየሱስን በሚያስከብር ኑሮ መኖር ካላቻልን ወደ ጸጋው ዙፋን ሥር በእምነት እንቅረብ እንጂ እንደ ጠንቋይ ቤት በአገልግሎት ብዛት ኢየሱስን ለማርካት አንጣደፍ፤ እርሱ ጣዖት አይደለምና!

ከአገልግሎት በፊት ቅድስናና ኢየሱስን ራሱን ማስደሰት ይቅናን! አገልግሎት በትክክል ከዳነ አማኝና አገልጋይ የሚወጣ ምስክርነት እንጂ የክርስትና መገለጫ አይደለም! እንደ ሙሽሪት ደስታችን የሙሽራችን ደስታ ከኾነ፣ ከሕይወታችን ያነሰ ስጦታ አናቅርብለት! አቤቱ ማስተዋላችንን መልስ፤ አሜን።

2 comments:

  1. GOD bless you for sharing. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete