Tuesday 16 February 2021

ራቪ ከሞት ወዲያ፤ እኛ ከወዲህ ኾነን!


Please read in PDF

ራቪ ዘካርያስ፣ “የገዛ ሚኒስትሪያቸው” ያረጋገጠባቸው አስቀያሚው የዝሙት ገመና ብዙ ነገሮችን እንዳብሰለስል አድርጎኛል። በርግጥ ከደካማው ሥጋ ለባሽ ይልቅ፣ ቅዱስ ቃሉ የማይለወጥና ብርቱ አስተማሪያችን፣ የሚረባንንና የሚጠቅመንን የሚነግረን ኹነኛ መምህራችን ነበረ፤ እንዳለመታደል በትክክል ከመስማትና ከመታዘዝ ቸል አልን እንጂ። አዎን መጽሐፍ ቅዱስ “የብርቱዎችን” ድካም ያራቆተው፣ እንማርበትና እንታነጽበት ዘንድ እንጂ እንገበዝበት ዘንድ አይደለም።



በምዕራቡ ዓለም እጅግ ርካሹ [በቀላሉ የሚገኙ] ኀጢአቶች፣ አውቃለሁ የሚል የአለማወቅ ጨለማ፣ ዝሙትና ጥንቆላ ናቸው። መዝናናትን ከዝሙትና ከአመንዝራነት ለይቶ የማይመለከትና የወሬ ማጣፈጫው ዝሙት የኾነለት ትውልድ ምንጩ ምዕራብ ብቻ ባይኾንም። በእኔ ዘመን ባሉ አገልጋዮችም ዘንድ [እኔን ጨምሮ] ያሉብን ያልተገለጡ ገመናዎች፣ እንደ ምዕራቡ ዓለም አነፍንፎ የሚዘግብ፣ መርማሪ ጋዜጠኛ የለም እንጂ ጉዳችን ብዙ መኾኑን አልጠራጠርም።

በደጋፊ ብዛት መቆምና በእውነተኛው የኢየሱስ ሕይወት መቆም አንድ አይደሉም። እናም፦

1.   የብዙ አገልጋዮች የገንዘብ አያያዛችን ምን ይመስላል? መቁረስ እንችልበታለን? ከሩቅ ስንታይ፣ ስብከታችን የሚጥመውን ያህል ሲቀርቡን ከአጋምና ቀጋ የምንሻል ነን?

2.   የ“ርካሹ” የአገራችን ፖለቲካ ደጋፊና ተቃዋሚ ኾነው ፓርቲ ማቋቋም የቀራቸው የሚመስሉት የአገራችን አገልጋይና አማኞች ይቅሩና፣ በቅርብ በአገልግሎት ውስጥ ያለን ከሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት ንጹሕ ነን? በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ያለውን ኅብረት ኹሉ አክባሪና አፍቃሪ ነን? አንዳንድ አገልጋዮች የተከሉብን የሃይማኖታዊ ብሔርተኝነት እሾኽ በቀላሉ የሚነቀል አይመስለኝም!

3.   አኹን በቁመተ ሥጋ ቆመው፣ በዝሙት ቅሌት ውስጥ የሚገኙ አእላፍ አገልጋዮች፣ ከራቪ “ቢማሩና” ነውራቸውን በንስሐና በይቅርታ ቢከድኑ እንዴት በታደሉ?

አንዳንዶቹ[እኔን ጨምሮ] ምናለ ራሳቸውን ምሳሌ ባለው የጋብቻ "ቀንበር ቢጠምዱ"? በጋብቻ የተጠመዱ አንዳንዶች ደግሞ፣ ምናለ ከአደባባዩ ዓውደ ምሕረት የገዛ ቤተ ሰባቸውን አስቀድመው ቢያገለግሉና አደብ ቢገዙ? ቤተ ክርስቲያን "አመንዝራችኋልና ንስሐ ግቡ" ብላቸው፣ አኩርፈውና ተገብዘው የግላቸውን ቤት(ቤተ ክርስቲያን ማለት ይቸግረኛል) ከፍተው አእላፍ ደጋፊ ያስከተሉ ቊጥራቸው ቀላል ነውን?!

የአንዳንዶቹ አገልጋዮች የነውር ገመና ደግሞ፣ የምንጣፍ ሥር እንዳለ ቆሻሻ ነው፤ ውበታቸው እንጂ ዕድፈታቸው አይታይም። ነገር ግን ዐለም እንዲህ በውርደት ከሚያወራው፣ አኹን ዕድል አለንና ከደጋፊዎቻችን ገለል ብለን፣ እልህና ትዕቢት ትተን ንስሐ ብንገባ፣ በኢየሱስ ፊት እንደ ዘኬዎስና የመግደሎም ሴት ማርያም ብንሰበር እጅግ መልካምና የሚሻለን ነገር ነው። አልያ ግን የማይለወጠው ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፤

መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና።” (2ቆሮ. 5፥10)

ደግሞ የወለደን ልጆቹ እንኳ ታማኝ ባንኾን፣

“አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።” (ዕዝ. 9፥15)

ብለን አምላካችንና መድኀኒታችን ሕያው እግዚአብሔርን በፍርሃት እንባርከዋለን

ለቃሉ በእውነት መሰበርና መታዘዝ፤ ከሰው ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን መጠየፍና መጥላት ይኹንልን፤ አለነቀፋ የምታገለግሉ ወንድሞችና እህቶቼ ጸጋው ይትረፍረፍላችሁ፤ ኹላችን ወደ ተናቀውና ወደ ስቁሉ ኢየሱስ ዘወትር የምንመለስበት ጸጋ ይብዛልን፤ አሜን


3 comments:

  1. GOD bless you. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come.

    ReplyDelete
  2. May The Heavenly God bless u more.

    ReplyDelete
  3. strong messages

    ReplyDelete